1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመስከረም 30 ቀን 2015 ዓ/ም የስፖርት ዝግጅት

ሰኞ፣ መስከረም 30 2015

ኢትዮጵያውያን እና ኬንያውያን በሁለቱም ጾታዎች የነገሱባቸው የማራቶን ውድድሮች በሊዝበን ፖርቻጋል እና በአሜሪካ ቺካጎ ተደርገዋል። በጉጉት ይጠበቁ ከነበሩ የእግር ኳስ ውድድሮች ሰሜን ለንደን ቀይ ሆኖ ያመሸበት አጋጣሚ ተጠቃሽ ነው። ክሪስትያኖ ሮናልዶ ደግሞ ሌላ አዲስ ታሪክ ጽፏል።

Großbritannien Fussball Premier League l Ronaldo jubelt, Manchester United
ምስል Dave Thompson/AP/picture alliance

የመስከረም 30 ቀን 2015 ዓ/ም የስፖርት ዝግጅት

This browser does not support the audio element.

ኢትዮጵያውያን እና ኬንያውያን በሁለቱም ጾታዎች የነገሱባቸው የማራቶን ውድድሮች በሊዝበን ፖርቻጋል እና በአሜሪካ ቺካጎ ተደርገዋል። በጉጉት ይጠበቁ ከነበሩ የእግር ኳስ ውድድሮች ሰሜን ለንደን ቀይ ሆኖ ያመሸበት አጋጣሚ ተጠቃሽ ነው። ክሪስትያኖ ሮናልዶ ደግሞ ሌላ አዲስ ታሪክ ጽፏል፤ በቡንደስ ሊጋ የሁል ጊዜ ተቀናቃኝ ኃያላን ክለቦች  ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል። ላሊጋም  አስደማሚ ውድድሮንች አስተናግዷል።  

ሰላም ጤና ይስጥልን አድማጮች በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት በዓለማቀ,ፍ የውድድር መድረኮች የተስተናገዱ የማራቶን  ውድድሮችን ጨምሮ አጓጊ ሆነው ያለፉ የእግር ኳስ ውድድሮችን የምንቃኝበት የዕለተ ሰኞ የስፖርት ዝግጅታችንን ይዘን ቀርበናል ፤ ታምራት ዲንሳ ነኝ ፤ አብራችሁን ቆዩ።

አትሌቲክስ

አድማጮች ዝግጅታችንን ትናንት በሊዝበን ፖርቹጋል  በተካሄደ የማራቶን ውድድር ስንጀምር፤ በወንዶች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ጣልቃ ሳያስገቡ ከአንድ እስከ ሶስት ተከታትለው በመግባት አንጸባራቂ ድል ተጎናጽፈዋል። ውድድሩን አንዷለም በላይ የቦታውን ክብረ ወሰን በማሻሻል ጭምር  አሸናፊ ሲሆን የገባበት ሰዓትም 2 ሰዓት ከ 5  ደቂቃ ከ45 ሰከንድ ሆኖ ተመዝግቦለታል ። ሃብቱ ተክሉ በ 2 ሰዓት ከ6 ደቂቃ ከ33 ሰከንድ እንዲሁም  ብርሃን ነበበው 2 ሰዓት ከ7 ደቂቃ ከ4 ሰከንድ በሆነ ሰዓት ሁለተኛ እና ሶስተኛ ሆነው መግባት ችለዋል። በሊዝበን ማራቶን ኬንያዊው ጁልየስ ኪፕኮሪር አራተኛ ላይ ጣልቃ ባይገባ ኢትዮጵያውያኑ እስከ ሰባተኛ ያለውን ደረጃ መቆጣጠር የሚችሉበት እንደነበራቸው ከውድድሩ ውጤት በቀላሉ መገመት አያዳግትም። ጽዳት አበጀ ፣ መኳንንት አየነው እና ደበቆ ዴከሞ ከአምስተኛ እስከ ሰባተኛ ያለውን ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል። በዚያው በሊዝበን ማራታን በሴቶች ምድብ በተደረገው ውድድር ሶሮሜ ነጋሽ ፣ብዙነሽ ጌታቸው እና ኡርጌ ዲሮ ከሁለት እስከ አራት ተከታትለው መግባት ችለዋል። ውድድሩን ኬንያዊቷ ቦርነስ ጄፕኪሩይ አሸናፊ ሆናለች። ቦርነስ የገባችበት ሰዓት 2 ሰዓት ከ24 ደቂቃ ከ17 ሰከንድ ሆኖ ተመዝግቧል።

በወንዶች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ጣልቃ ሳያስገቡ ከአንድ እስከ ሶስት ተከታትለው በመግባት አንጸባራቂ ድል ተጎናጽፈዋልምስል Hilda Weges/Zoonar/picture alliance

ከማራቶን ዜና ሳንወጣ አሜሪካ ቺካጎ ትናንት በተደረገው የማራቶን ውድድር በወንዶች ምድብ ቱራ አብዲ ዋቅ 2 ሰዓት ከአራት ደቂቃ ከ49 ሰከንድ በሆነ ጊዜ ሁለተኛ ወጥቷል። ውድድሩን በሁለቱም ጾታ ኬንያውያን አሸናፊ ሆነውበታል። በሴቶች ምድብ የተወዳደረችው ኬንያዊቷ ሩት ቼፕጌቲች 2 ሰዓት ከ14 ደቂቃ ከ18 ሰከንድ በመሮጥ ለዓለም ክብረወሰን የቀረበ የምንጊዜም ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ አሸናፊ ሆናለች።አሜሪካዊቷ ኤሚሊ ሲዘን ለሀገሯ አዲስ ክብረ ወሰን ሆነ በተመዘገበ ሰዓት 2 ሰዓት ከ18 ደቂቃ 29 ሰከንድ ሁለተኛ ስትሆን ሌላዋ ኬንያዊት ቪቫን ውድድሩን በሶስተኛነት አጠናቃለች። ኢትዮጵያውያኑ ሩቲ አጋ እና ዋጋነሽ መካሻ አራተና እና አምስተኛ ሆነው አጠናቀዋል።  በወንዶች ምድብ የነበረውን ውድድር ቤንሰን ኪፕሩቶ 2 ሰዓት ከአራት ደቂቃ ከ24 ሰከንድ በሆነ ጊዜ አሸናፊ ሆኗል። በውድድሩ የተሳተፈ ሌላው ኢትዮጵያዊ ሺፈራው ታምሩ አምስተኛ በመሆን አጠናቋል።

እግር ኳስ

በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ተጠባቂ ከነበሩ እና የእግር ኳስ አፍቃሪያንን ቁጭ ብድግ ያደረጉ ውድድሮች በአውሮጳ የተለያዩ ተስተናግደዋል። ከእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ስንጀምር ትናንት እሁድ አርሴናል በኤሜሬትስ ሊቨርፑልን አስተናግዶ 3 ለ 2 አሸንፎ ወደ የሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ መሪነት የተመለሰበት ውድድር በበርካቶች ዘንድ እጅጉን ተጠባቂ ነበር። ሊቨርፑሎች ሁለት ጊዜ ከመመራት አቻ የመሆን እድሎች መፍጠር ቢችሉም የማታ ማታ አ,ርሴናሎች ጣፋጭ ድል መጎናጸፍ ችለዋል። አርሴናል ከማችስተር ዩናይትድ የ 3 ለ 1 ሽንፈት በኋላ በተከታታይ የሚገጥሟቸው ቶተንሃም እና ሊቨርፑል ብርቱ ፈተና እንደሚጠብቀው ተገምቶ የነበረ ቢሆንም ሁለቱንም በአሳማኝ ብቃት ማሸነፍ ችሏል። ይህም በተለይም አሰልጣኙ ሚኬል አርቴታ በአንድ ወቅት ቡድኑን በወጣት ተጫዋቾች እያወቀረ መሆኑ ባስተቸው አጋጣሚ ለሰጠው «trust the process» «ሂደቱን እመኑ» ምላሹ በአንጋፋ የእግር ኳስ ተንታኞች ዘንድ ጭምር ተቀባይነት እና ሙገሳ እስገኝቶለታል። አርሴናል የትናንቱን ድል ተከትሎ ፕሪሚየር ሊጉን በ24 ነጥቦች ይመራል።

አርሴናል የትናንቱን ድል ተከትሎ ፕሪሚየር ሊጉን በ24 ነጥቦች ይመራልምስል Andre Boyers/AP/picture alliance

በሊጉ ትናንት ምሽት በተደረገ ሌላ ጫወታ የማንችስተርዩናይትዱ ክሪስትያኖ ሮናልዶ አዲስ ታሪክ በጻፈበት የጎዲሰን ፓርኩ ምሽት ማንችስተር ዩናይትድ ወደ አሸናፊነት ተመልሶ የላምፓርዱን ኤቨርተንን 2 ለ 1 ማሸነፍ ችሏል። ሁለተኛውን እና የማሸነፊያ ጎሉን ያስቀጠረው ክርስትያኖ ሮናልዶ ከተከታታይ ጫወታዎች በኋላ ከተቀያሪ ወንበር ተነስቶ ለራሱ ታሪካዊ እና 700ኛ የሊግ ጎሉን ማስቆጠር ችሏል። የውድድር ዓመቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በአቋም መውረድ ከቋሚ አሰላለፍ ውች ሆኖ ለሰነበተው ሮናልዶ በአለማቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ዘንድ ስሙ እንደገና ከፍ ብሎ እንዲጠራ አድርጓል። 38ኛ ዓመት የልደት በዓሉን ለማክበር የተቃረበው ክርስትያኖ ሮናልዶ በአራት የአውሮጳ የተለያዩ ሊጎች 700 ጎሎች ማስቆጠር ችሏል። በቀዳሚ ቤቱ የፖርቹጋሉ ስፖርቲንግ ሊዝበን 5 ጎሎችን በማስቆጠር የጀመረው ሮናልዶ በሪያል ማድሪድ 450 ጎሎችን፣ ለጁቬንቱስ 101 ጎሎችን እንዲሁም ለማንችስተር ዩናትድ በጠቅላላ 144 ጎሎችን አስቆጥሯል። በዚህም 700 የክለብ ጎሎችን በማስቆጠር አዲስ የዓለማችን ክብረ ወሰን ሆኖ ተመዝግቦለታል።  

ምስል Patricia de Melo Moreira/AFP

በሌሎች የእንግሊዝ ፕሪሚየርሊግ የሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ከተስተናገዱ ጫወታዎች መካከል ትናንት እሁድ በተደረጉ ጫወታዎች ክሪስታል ፓላስ ሊድስ ዩናይትድን 2 ለ 1 ፣ ፉልሃምን ያስተናገደው ዌስትሃም 3 ለ 1 በሆነ ውጤት አሸንፈዋል። ቅዳሜ ዕለት በተደረጉ ውድድሮች ደግሞ ብራይተንን በሜዳው የገጠመው ቶተንሃም ከሳምንቱ የአርሴናል ሽንፈት አገግሞ በዘንድሮው የሊግ ተሳትፎው ጥሩ አጀማመር አሳይቶ የነበረውን ብራይተንን 1 ለ 0 አሸንፏል። በተጨማሪም ቼልሲ ዎልብስን በሜዳው አስተናግዶ 3 ለ 0 በሆነ ውጤት ሲያሸንፍ ማንችስተር ሲቲም የጎል ማሺኑ ሃላንድ ተጨማሪ ጎል ባመረተበት ውድድር ሳውዝ  አምፕተንን 4 ለምንም በሆነ ውጤት አበሳጭቶ መልሶታል። በዚህ አጋጣሚ የሃላንድ የጎል ማስቆጠር ሁኔታው ምናልባትም በፕሪሚየር ሊጉ በዓመቱ ዓዲስ ጎል የማስቆጠር ክብረወሰን ይሰብር ይሆን የሚል ግምት አሰጥቶታል። ሊጉን አርሴናል፣ ማንችስተር ሲቲ ፣ቶተንሃም እና ቼልሲ በ24፣23፣20 እና 16 ነጥቦች ከአንድ እስከ አራት ያለውን ደረጃ ይዘዋል። ኖቲንግሃም ፎረስት ፣ ሌስተር ሲቲ እና ዎልቭስ ደግሞ በ4፣4 እና ስድስት ነጥቦች ወራጅ ቀጣና ውስጥ ለመቀመጥ ተገደዋል።

ቡንደስሊጋ

በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት በቡንደስ ሊጋው በጉጉት ይጠበቁ ከነበሩ ጫወታዎች መካከል ዶርትሙንድ ባየር ሙንሽንን ያስተናገደበት የቅዳሜ ዕለት ቁጭ ብድግ ያስደረገው ጫወታ ተጠቃሽ ነው ። በድራማዊ ትዕይትን የተሞላው ውድድሩ ባለሜዳው ዶርትሙንዶች  2 ለ 0 ከመመራት ተነስተው ሁለት አቻ ማጠናቀቅ ችለዋል።  በጫወታው ማገባደጃ ላይ የባየርኑ ኪንግስሌይ ኮማን በቀይ ካርድ ከሜዳ መሰናበቱ ደግሞ ጫወታው ምን ያህል በውጥረት የተሞላ እንዲሆን አድርጎታል። በ9 ጫወታዎች ባየርሙንሽን በጎል ብዛት በልጦ በእኩል የ16 ነጥቦች  በ3ኛ እና አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። በሌሎች ጫወታዎች ትናንት እሁድ በተደረጉ ጫወታዎች የሊጉ መሪ  ዩንየን በርሊን ሽቱትጋርትን ከሜዳው ውች ገጥሞ 1 ለ 0 ሲያሸንፍ ፤ ሞንቼግላድባህ ኮለንን አስተናግዶ 5 ለ 2 በሆነ የሰፋ ልዩነት አሸንፏል። ኮለኖች አንድ ተጫዋቻቸውን በቀይ ካርድ አጥተዋል። ሄርታ ከፍራይቡርግ ያደረጉት ጫወታ ደግሞ 2 አቻተጠናቋል። በቅዳሜ ጫወታዎች አውስቡርግ ከዎልቭስቡርግ 1  አቻ ሊቨርኩሰን ሻልከን አስተናግዶ 4 ለባዶ ሲሸን ቦሁምም እንዲሁ ኢንትራ ፍራንክፈርትን 3 ለ0 ማሸነፍ ችሏል። ቨርደን ያስተናገደው ሆፈንሃየም ደግሞ በሜዳው እና በደጋፊው ፊት 2 ለ 1 ሽንፈት አስተናግዷል።

ምስል Leon Kuegeler/REUTERS
የዶርትሙንድ እና ባየር ሙንሽን ግጥሚያምስል Leon Kuegeler/REUTERS

ላሊጋ

ትናንት እሁድ  በተደረጉ የላሊጋ የሳምንቱ መጨረሻ ጫወታዎች መሪው ባርሴሎና በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ የሚያቆየውን የ 1 ለ 0 ድል ሴልታ ቪጎ ላይ ተጎናጽፏል። ቪያሪያልን በሜዳው ያስተናገደው ሪያል ሶሴዳድም እንዲሁ በተመሳሳይ 1 ለ 0 ሲያሸንፍ ኤስፓኞልን ያስተናገደው ካዲስ2 አቻ ተለያይቷል። ቅዳሜ በተደረጉ ውድድሮች ሊጉን ከመሪው ባርሴሎና በ ነጥብ ዝቅ ብሎ የሚከተለው ሪያል ማድሪድ ጌታፌን ገጥሞ 1 ለ 0 ሲያሸንፍ ነጥቡን 22 ማድረስ ችሏል። በዚህም ሁለቱ የስፔን ሃያላን ገና ከአሁኑ አንገት ለአንገት ተናንቀው የውድድር ዓመቱን አጓጊ አድርገውታል። አትሌቲኮ ማድሪድም ጊሮናን 2 ለ1 አሸንፎ በሊጉ አራተና ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል።

ባርሴሎና በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ የሚያቆየውን የ 1 ለ 0 ድል ሴልታ ቪጎ ላይ ተጎናጽፏልምስል Joan Monfort/AP Photo/picture alliance

በካፍ የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የሁለተኛ ዙር ማጣሪያ የመጀመሪያ ጫወታውን በባህርዳር ስቴዲየም የቱኒዚያውን ሴፋክስየን ያስተናገደው ፋስል ከነማ ያለምንም ጎል አቻ ተለያይቷል። ጫወታው በአቻ ጎል መጠናቀቁ ለእንግዳው ቡድን የተሻለ ዕድል ሲፈጥርለት በአንጻሩ ለፋሲል ከነማ ሳይከበድው አይቀርም።  የመልሱ ጫወታ የፊታችን ቅዳሜ በቱኒዚያ ይደረግ እና ሃላፊው ቡድን ይታወቃል።

በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው የምስራቅ አፍሪቃ ሃገራት ሴካፋ ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር አዘጋጇ ኢትዮጵያን በጊዜ አሰናብቶ ቀጥሎ እየተካሄደ ነው። ኢትዮጵያ ከሶማሊያ እና ታንዛንያ ጋር በተከታታይ ባደረገቻቸው ጫወታዎች 1 ለ 0 እና 3 ለ 2 በመሸነፏ ያለምን ነጥብ በጊዜ ተሰናብታለች። ውድድሩ ቀጥሎ ወደ ግማሽ ፌጻሜ ያለፉ ሃገራት ታውቀዋል። በዚህም የፊታችን ረቡዕ ዩጋንዳ ከሶማሊያ ሲጫወቱ ፤ ታንዛኒያ ደግሞ ደቡብ ሱዳንን ትገጥማለች ።

መሸጋገሪያ

እንግዲህ አድማጮቻችን ለዛሬ ያልነው የስፖርት ዝግጅታችንም የእስካሁኑን ይመስል ነበር ፤ ሳምንት በሌሎች ስፖርታዊ መሰናዶዎች እንጠብቃችኋለን ጤና ይስጥልን ።

ታምራት ዲንሳ

ነጋሽ መሐመድ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW