1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪካ ጀርመን ወጣት የንግድ ሥራ መሪዎች መርሐ-ግብር አመልካቾችን እየተቀበለ ነው

Eshete Bekele
ረቡዕ፣ የካቲት 27 2016

ኢትዮጵያ እና ጀርመንን ጨምሮ የስድስት ሀገራት የንግድ ሥራ መሪዎች የሚሳተፉበት ዓመታዊ መርሐ-ግብር ማመልከቻዎች እየተቀበለ ነው። ለአራተኛ ጊዜ የሚካሔደው መርሐ-ግብር ዕድሜያቸው ከ40 ዓመት በታች የሆነ 40 ወጣት የንግድ ሥራ መሪዎችን በበርሊን ከተማ ያገናኛል። በመርሐ-ግብሩ የተሳተፉ ኢትዮጵያውያን በዕድሉ ጠቃሚ ግንኙነት እንዳበጁ ተናግረዋል።

የአፍሪካ ጀርመን የንግድ ሥራ መሪዎች መርሐ-ግብር ተሳታፊዎች
በመስከረም 2024 በበርሊን ከተማ በሚካሔደው መርሐ-ግብር ኢትዮጵያ እና ጀርመንን ጨምሮ በዳኞች የሚመረጡ የስድት ሀገራት 40 የንግድ ሥራ መሪዎች ይሳተፋሉምስል LdI/Bernd Brundert

የአፍሪካ ጀርመን ወጣት የንግድ ሥራ መሪዎች መርሐ-ግብር አመልካቾችን እየተቀበለ ነው

This browser does not support the audio element.

ኢትዮጵያውያን የሚሳተፉበት የአፍሪካ ጀርመን ወጣት የንግድ ሥራ መሪዎች መርሐ-ግብር ማመልከቻዎችን እየተቀበለ ነው። አዘጋጆቹ የጀርመን የንግድ ሥራ እና ልማት ኤጀንሲ (AWE) እና ጀርመንን ለማስተዋወቅ በሀገሪቱ ፌድራል መንግሥት እና ኢንዱስትሪዎች የተመሠረተው ላንድ ኦፍ አይዲያስ (Germany - Land of Ideas) ናቸው።

የጀርመን የኤኮኖሚ ትብብር እና ልማት ሚኒስቴር በገንዘብ በሚደግፈው በዚህ መርሐ-ግብር ለመሳተፍ የሚፈልጉ ወጣት የንግድ ሥራ መሪዎች እስከ መጋቢት 29 ቀን 2016 ማመልከት ይችላሉ።

በምህጻሩ ኤጃይል (AGYLE) ተብሎ የሚጠራው መርሐ-ግብር ኃላፊ ባስቲያን ጋየር “ዕድሜያቸው ከ40 ዓመት በታች የሆነ በሰርኩላር ኤኮኖሚ ዘርፍ የተሰማሩ 40 ወጣቶች እንፈልጋለን። የሚያመለክት እያንዳንዱ ወጣት በንግድ ሥራ (business) ፣ በፖለቲካ እና መገናኛ ብዙኃን ዘርፎች የመሪነት ልምድ ያለው መሆን አለበት” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

በእንግሊዘኛ “ሰርኩላር ኤኮኖሚ” ተብሎ የሚጠራው የምጣኔ ሐብት ሞዴል በዋናነት ብክለት እና ብክነትን ለመቀነስ ያለመ ነው። ይኸ የኤኮኖሚ ሞዴል ምርት እና ግብዓቶችን በማጋራት፣ መልሶ በመጠቀም፣ በመጠገን እና በማደስ አካባቢን ለመጠበቅ፣ የተፈጥሮ ሐብቶች ጥገኝነትን ለመቀነስ፣ ሥራ ለመፍጠር እና የሸማቾችን ወጪ ለመቆጠብ ያስችላል ተብሎ ታምኖበታል።

በዘንድሮው መርሐ-ግብር የኢትዮጵያ፣ ጋና፣ ርዋንዳ፣ ሴኔጋል፣ ቱኒዝያ እና ጀርመን የንግድ ሥራ መሪዎች ለመሳተፍ ማመልከት ይችላሉ። ከአመልካቾቹ መካከል በጀርመን ዋና ከተማ በርሊን ለአንድ ሣምንት የሚካሔደው መርሐ-ግብር 40 ተሳታፊዎች በዳኞች ይመረጣሉ።

“ለአንድ ሣምንት ወጣት መሪዎችን አንድ ጋ እናሰባስባቸዋለን። በመስከረም ከጀርመን ኩባንያዎች፣ የፖለቲካ ውሳኔ ሰጪዎች ጋር አብረው ለመስራት እና ሐሳብ ለመለዋወጥ ወደ በርሊን ይመጣሉ” የሚሉት ባስቲያን ጋየር ተሳታፊዎች “አዳዲስ የአመራር ክኅሎቶች እና የተለያዩ የአሠራር ሥልቶች ይማራሉ። በአውደ ጥናቶች አብረው ይሠራሉ” ሲሉ አስረድተዋል።

በዘንድሮው መርሐ-ግብር የኢትዮጵያ፣ ጋና፣ ርዋንዳ፣ ሴኔጋል፣ ቱኒዝያ እና ጀርመን የንግድ ሥራ መሪዎች ለመሳተፍ ማመልከት ይችላሉ።ምስል LdI/Bernd Brundert

እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር በመስከረም 2024 የሚካሔደው መርሐ-ግብር ወደ ሰርኩላር ኤኮኖሚ በሚደረገው ሽግግር ወጣት መሪዎች ያላቸውን ሚና በመፈተሽ ላይ ያተኮረ ነው። ባለፉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት የአፍሪካ የንግድ ሥራ መሪዎችን ከጀርመን አቻዎቻቸው ያገናኙ መድረኮች ትኩረት ያደረጉባቸው ርዕሰ-ጉዳዮች ነበሯቸው።

“በአፍሪካ ሀገሮች፣ በአፍሪካ ገበያዎች እና በጀርመን መካከል ያለውን የኤኮኖሚ ልውውጥ እና ንግግር ማሳደግ ጠቃሚ ነው ብለን እናስባለን። ምክንያቱም አንዳችን ከሌላው ብዙ ጥቅም ማግኘት እንችላለን” ሲሉ የመርሐ-ግብሩ ኃላፊ ፋይዳውን አስረድተዋል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ ሀገራት የጀርመን ግዙፍ ኤኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሚባሉትን አነስተኛ እና መካከለኛ ተቋማት ቀልብ የመሳብ ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው። “የአፍሪካ አኅጉር የጀርመን ኩባንያዎችን ትኩረት የሚስብ ነው። ወደፊት ደግሞ የበለጠ ሳቢ ይሆናል” የሚሉት ባስቲያን ጋየር ነገር ግን “ቸልተኛ” መሆናቸውን ግን አላጡትም።

“የጀርመን ኩባንያዎች አፍሪካን በተመለከተ በተወሰነ መንገድ ቸልተኛ ናቸው። ብዙዎቹ ወግ አጥባቂ ናቸው” ያሉት ኃላፊው “የስኬት ታሪኮችን በማሳየት እና የጀርመን ኩባንያዎች በአኅጉሩ ከሚገኙ ሀገራት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዲፈጥሩ በመርዳት ይኸንን መስበር እንፈልጋለን” ሲሉ አስረድተዋል።

የአፍሪካ ጀርመን ወጣት የንግድ ሥራ መሪዎች መርሐ-ግብር በጎርጎሮሳዊው 2021 ለመጀመሪያ ጊዜ ሲካሔድ ከተሳተፉ መካከል የቱባ ኢትዮጵያ መሥራች እና ዋና ሥራ አስኪያጅ ቅድስት ተስፋዬ አንዷ ነች። ቱባ ኢትዮጵያ በአዲስ አበባ በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው ሥፍራ በመጋቢት 2009 የደረሰ የቆሻሻ መደርመስ በፈጠረው መነሳሳት የተቋቋመ ነው።

በወቅቱ የምኅንድስና ተማሪ የነበረችው ቅድስት አየርም ሆነ ፈሳሽ የማያሳልፉ የፕላስቲክ ቀረጢቶች ለበርካታ አስርት ዓመታት በተቆለለው ቆሻሻ ውስጥ መገኘት ለአደጋው መፈጠር አንዱ መነሾ እንደሆነ ታዝባለች። ያቋቋመችው ኩባንያ ድሕነት እና ሥራ አጥነት የሚፈታተናቸው የቆሼ አካባቢ ሴቶች የፕላስቲክ ከረጢትን የሚተካ ቦርሳ ለመሥራት የሚያስፈልግ ግብዓት እንዲያመርቱ መንገድ የጠረገ ነው። 

በአዲስ አበባ በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በተፈጠረ የቆሻሻ መደርመስ የበርካታ ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል። ምስል DW/Y. G. Egziabher

“በእጅ እንዴት እንደሚሠራ ስልጠና” በመስጠት እና ጥሬ ዕቃ በማቅረብ ሴቶቹ “በቤታቸው ቁጭ ብለው ጨርቁን ማምረት ጀመሩ” የምትለው ቅድስት የሚሠራው ጨርቅ ከቆዳ ጋር ተቀላቅሎ በቱባ ኢትዮጵያ “በተለያየ ንድፍ ቦርሳውን ሠርተን ለገበያ እናወጣለን። ለእነሱ ደግሞ በሠሩት መጠን እንከፍላቸዋለን” ስትል አስረድታለች።  

ቱባ ኢትዮጵያ የሚያመርታቸው ቦርሳዎች 30 ከመቶ ከጥጥ 70 ከመቶ ደግሞ ጥቅም ላይ ከዋለ ጨርቅ የሚሠሩ ናቸው። የኩባንያው መሥራች ቅድስት በመጀመሪያው የአፍሪካ ጀርመን ወጣት የንግድ ሥራ መሪዎች መርሐ-ግብር በመሳተፏ ከእሷን መሰል የንግድ ሥራ መሪዎች ጋር ዘላቂ ግንኙነት እንድታበጅ ዕድል ፈጥሮላታል።

“እዚያ ያገኘኋቸው ሰዎች በጣም ጠቃሚ ሰዎች ናቸው” ያለችው የቱባ ኢትዮጵያ መሥራች እና ዋና ሥራ አስኪያጅ ከኢትዮጵያውያን ጭምር ግንኙነት መመሥረቷን አስረድታለች። “አሁንም እንደጋገፋለን” የምትለው ቅድስት የመሠረቱት ግንኙነት ጠቃሚ መሆኑን ገልጻለች። በመጀመሪያው ዙር ቅድስትን ጨምሮ ስድስት ኢትዮጵያውያን ተሳትፈዋል።

ከተሳታፊዎቹ አንዱ የሆነው አቤል ኃይለጊዮርጊስ ወደ በርሊን ያጓዘውን ዕድል ያገኘው ከቀርክሀ ለአካል ጉዳተኞች የሚያገለግል ተሽከርካሪ ወንበር የማምረት ሐሳብ በሚያውጠነጥንበት ወቅት ነው። በኢትዮጵያ ከ1.4 ሚሊዮን በላይ አካል ጉዳተኛ መኖራቸውን የሚገልጽ የዓለም ጤና ድርጅት ያሳተመው ጽሁፍ የሐሳቡ መነሻ እንደሆነ ይናገራል። 

በኢትዮጵያ በወቅቱ ዊልቼር የሚያመርት ኩባንያ እንዳልነበር መገንዘቡን የገለጸው አቤል “ለምንድነው በዝቅተኛ ዋጋ ዊልቼሮች ማምረት የማንችለው?” የሚል ሐሳብ ነበረው። ወጣቱ ባምቡ ላብስ የተባለውን ኩባንያ ያቋቋመው የተማረውን የምኅንድስና እውቀት እና ክኅሎት “ሰዎችን ለመርዳት ለምን አልጠቀምበትም?” በሚል ሐሳብ ነው። አቤል ያቋቋመው እና በዋና ሥራ አስኪያጅነት የሚመራው ባምቡ ላብስ ኩባንያ ለአካል ጉዳተኞች የሚሆኑ ተንቀሳቃሽ ወንበሮች እና ሳይክሎች ከቀርክሀ የሚያመርት ነው።

በአፍሪካ ጀርመን ወጣት የንግድ ሥራ መሪዎች መርሐ-ግብር በበርሊን ከተማ ለአንድ ሣምንት ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ከተለያዩ ሀገሮች ከተውጣጡ አቻዎቹ ጋር በአንድ ምድብ ተመድቦ “የትምህርት ጥራት እንዴት የተሻለ ሊሆን ይችላል?” በሚል ርዕሰ-ጉዳይ ላይ የቢዝነስ ዕቅድ አዘጋጅቷል።

“እንዴት አድርገን ቢዝነስ ሞዴል ማዳበር እንችላለን? እንዴት ማሳደግ እንችላለን? የገንዘብ ምንጭ እንዴት እናገኛለን?” በሚሉ ጉዳዮች ላይ የቀሰመው ክኅሎት “ለእኔ እንደ ጀማሪ የንግድ ሥራ መሪ ጠቅሞኛል” በማለት አስረድቷል።

በአፍሪካ ጀርመን ወጣት የንግድ ሥራ መሪዎች መርሐ-ግብር የተሳተፉ ኢትዮጵያውያን ከሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች እና ከጀርመን አቻዎቻቸው ጠቃሚ ግንኙነት ማበጀታቸውን ተናግረዋል። ምስል LdI/Bernd Brundert

ባምቡ ላብስ የምርቶቹን አይነት ለማስፋት የሚረዱ ማምረቻዎች እስከ መጪው ክረምት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚያስገባ አቤል ለዶይቼ ቬለ ተናግሯል። የሠራተኞቹን ቁጥርም የማሳደግ ዕቅድ አለው። “ከአሰልጣኞቹ እና በአሰልጣኞቹ አካባቢ ያሉ ኔትወርኮች በጣም ጠቃሚ ናቸው። በዚያ ኔትወርክ አማካኝነት ድጋፍ አግኝቻለሁ” የሚለው አቤል ሥራውን “ከእጥፍ በላይ በሆነ ፍጥነት” የሚያከናውኑ “ቴክኖሎጂዎችን የሚሠሩ ሰዎች ድጋፍ” እንዳደረጉለት አስረድቷል።

አቤል በበርሊን ቆይታው እንደ ቅድስት ሁሉ ከተለያዩ ሀገራት ከተውጣጡ የንግድ ሥራ መሪዎች ጋር ጠቃሚ ግንኙነት እንደፈጠረ ተናግሯል። እንዲህ አይነቱን ግንኙነት መፍጠር የአፍሪካ ጀርመን ወጣት የንግድ ሥራ መሪዎች መርሐ-ግብር አንድ ዕቅድ እንደሆነ ኃላፊው ባስቲያን ጋየር ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

“በተለይ ለጀማሪ ኩባንያዎች ጥሩ እና ጠንካራ ግንኙነት መዘርጋት በጣም ጠቃሚ ነው። ምክንያቱም የሥራ ማስኬጂያ ገንዘብ፣ እውቀት፣ አቅራቢዎች፣ ገዢዎች እና ምርቶቻቸውን የሚያስተዋውቁላቸው ሰዎች ይፈልጋሉ” የሚሉት ባስቲያን ጋየር “እነርሱ ከሌሎች ይማራሉ፤ እነሱም ያስተምራሉ” ሲሉ ፋይዳው ላቅ ያለ እንደሆነ ጠቁመዋል።

የአፍሪካ ጀርመን ወጣት የንግድ ሥራ መሪዎች መርሐ-ግብር ተሳታፊዎቹ የርስ በርስ ግንኙነት የሚመሠርቱበት፣ እውቀት እና ክኅሎታቸውን ጭምር የሚያበለጽጉበት ዕድል ነው። ባስቲያን ጋየር ግን አፍሪካውያን ኩባንያዎች እና የንግድ ሥራ መሪዎች “ካፒታል እናገኛለን” የሚል ተስፋ እንደሚሰንቁ መታዘባቸውን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

ይሁንና ኃላፊው እንደሚሉት የአፍሪካ ጀማሪ ኩባንያዎችን በቀጥታ በገንዘብ መደገፍ የሚያስል ብዙ መንገዶች በአሁኑ ወቅት የሉም። ለጀማሪ ኩባንያዎች መዋዕለ-ንዋይ የሚያቀርቡ የአውሮፓ የግል የቬንቸር ኩባንያዎች “ስለ አፍሪካ በቂ ባለሙያ እና ልምድ” ስለሌላቸው የአፍሪካ ኩባንያዎችን ፍላጎት እንደማያሟሉ ተናግረዋል። ጉዳዩ መፍትሔ እንደሚያስፈልገው የገለጹት ባስቲያን ጋየር “በርካታ ሰዎች በዚህ ላይ እየሰሩ ቢሆንም መፍትሔ ለማበጀት ብዙ የሚቀር ይመስለኛል” ሲሉ ተናግረዋል።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW