1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያውያን ወጣት ባለሙያዎች በጀርመን በቀሰሙት ልምድ ሀገራቸውን ለመጥቀም ተስፋ ሰንቀዋል

Eshete Bekele
ረቡዕ፣ ጥቅምት 20 2017

አራት ኢትዮጵያውያን አፍሪካ ኮምት (AFRIKA KOMMT) በተባለ ከጎርጎሮሳዊው ከ2023 እስከ 2025 የሚዘልቅ መርሐ-ግብር በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ። ይኸ መርሐ-ግብር አፍሪካውያን ወጣት ባለሙያዎችን ከሥመ -ጥር የጀርመን ኩባንያዎች የሚያገናኝ ነው። ገነት አታክልት እና ጌቱ ታደለ በግዙፍ የጀርመን ኩባንያዎች ውስጥ ለወራት እየሰሩ ሲማሩ ቆይተዋል።

ገነት አታክልት
ገነት አታክልት የአዳማ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ እና የሶፍትዌር ዴቬሎፕመንት ባለሙያ ስትሆን አፍሪካ ኮምት በተባለ መርሐ-ግብር በጀርመን ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ውስጥ ለስምንት ወራት እየሰራች ስትማር ቆይታለች። ምስል privat

ኢትዮጵያውያን የአፍሪካ ኮምት ተሳታፊዎች በጀርመን በቀሰሙት ልምድ ሀገራቸውን ለመጥቀም ተስፋ ሰንቀዋል

This browser does not support the audio element.

አፍሪካውያን ወጣት ባለሙያዎችን ከሥመ-ጥር የጀርመን ኩባንያዎች የሚያገናኘው አፍሪካ ኮምት የተባለ መርሐ-ግብር ኢትዮጵያውያኑ ገነት አታክልት እና ጌቱ ታደለ ከፍ ያለ ተስፋ እንዲሰንቁ አድርጓቸዋል። በጀርመን ኩባንያዎች እና በሀገሪቱ መንግሥት ድጋፍ የሚካሔደው መርሐ-ግብር አራት ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ከ15 የአፍሪካ ሀገሮች የተውጣጡ 41 ወጣቶች የሚሳተፉበት ነው።

ከአራቱ ኢትዮጵያውያን አንዷ የሆነችው ገነት አታክልት የአዳማ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ እና የሶፍትዌር ዴቬሎፕመንት ባለሙያ ናት። በአዲስ አበባ ሳለች መቀመጫቸውን በአሜሪካ እና አውሮፓ ካደረጉ ኩባንያዎች ጋር በርቀት የሶፍትዌር ማበልጸግ እና የማማከር ሥራዎች ትሠራ ነበር።

ገነት የአፍሪካ ኮምት ተሳታፊ ሆና ወደ ጀርመን በማቅናት ኤስኤፒ (SAP) በተባለ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ውስጥ ለ8 ወራት በሙያዋ እየሠራች ቆይታለች። መቀመጫውን በዋልዶርፍ ከተማ ያደረገው ኩባንያ በመላው ዓለም ከ105,000 በላይ ሠራተኞች አሉት።

ኢትዮጵያውያን የሚሳተፉበት የአፍሪካ ጀርመን ወጣት የንግድ ሥራ መሪዎች መርሐ-ግብር አመልካቾችን እየተቀበለ ነው

የኩባንያው “የሥራ ባህል የተለየ ነው” የምትለው ገነት ሠራተኞች ከዓለቆቻቸው ባላቸው የተለየ ግንኙነት መደመሟን ለዶይቼ ቬለ ተናግራለች። በተቋሙ ውስጥ የሚከሰቱ ለውጦች የሥራ እንቅስቃሴውን እንደማያውኩ መታዘቧን የገለጸችው ገነት ኩባንያው ደንበኞችን ለመደገፍ እና ለማስደሰት የሚያደርገው ጥረት “በደንብ አስገርሞኛል” ትላለች።

ገነትን ጨምሮ የአፍሪካ ወጣቶች በመርሐ-ግብሩ ለመሳተፍ ጥብቅ መመዘኛዎችን ማሟላት ይጠበቅባቸዋል። በጀርመን ኩባንያዎች እና ወጣት የአፍሪካ ባለሙያዎች መካከል በዘላቂ አጋርነት ድልድልይ ለመዘርጋት የሚጥረው መርሐ-ግብር በሀገሪቱ ፕሬዝደንት እና ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ትብብር የሚከናወን በጀርመን የልማት ትብብር መሥሪያ ቤት (GIZ) ተግባራዊ የሚደረግ ነው።

መስፈርቶቹ ምንድናቸው?

በመርሐ-ግብሩ መሳተፍ የሚችሉት የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው፣ ከሁለት እስከ አምስት አመታት የሠሩ አፍሪካውያን ናቸው። በጣም ጥሩ የእንግሊዘኛ ቋንቋ ችሎታ ከቅድመ-ሁኔታዎቹ መካከል አንዱ ሲሆን አመልካቾች ዕድሜያቸው ከ35 ሊበልጥ አይገባም። በትምህርታቸው እስከ ማስተርስ ዲግሪ የዘለቁ እና መሠረታዊ የጀርመንኛ ቋንቋ የሚችሉ የተሻለ የመመረጥ ዕድል ይኖራቸዋል።

የመርሐ-ግብሩ ተሳታፊ ጌቱ ታደለ ዓለም አቀፍ አስተዳደር ሥልጠና በጀርመን የልማት ትብብር መሥሪያ ቤት (GIZ) አማካኝነት መሰልጠናቸውን፣ የተለያዩ አጋር ኩባንያዎች መጎብኘታቸውን ለዶይቼ ቬለ አስረድቷል።ምስል privat

በኢትዮ-ቴሌኮም መደበኛ የአክሲዮን ሽያጭ ልብ መባል ያለባቸው ጉዳዮች የትኞቹ ናቸው?

መስፈርቱን አሟልተው በመርሐ-ግብሩ ለመሳተፍ ከተመረጡ ኢትዮጵያውያን መካከል የመቐለ ዩኒቨርሲቲ መምህር የነበረው ጌቱ ታደለ ይገኝበታል። ጌቱ የኮምፒውተር ሳይንስ ባለሙያ ሲሆን ወደ ደቡብ ኮሪያ አቅንቶ የማስተርስ ዲግሪ ሲያጠና በተለይ በሕክምና ላይ አተኩሯል። ሙያው በሕክምና ውስጥ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሥራ ላይ የሚውልበት ነው።

የዓለም አቀፍ አስተዳደር ሥልጠና በጀርመን የልማት ትብብር መሥሪያ ቤት (GIZ) አማካኝነት መሰልጠናቸውን፣ የተለያዩ አጋር ኩባንያዎች መጎብኘታቸውን ጌቱ ለዶይቼ ቬለ አስረድቷል። ዋናው ግን ተሳታፊዎች በመረጡት ኩባንያ በሙያቸው እንደ ገነት እየሰሩ የሚማሩበት ነው። በዚህ ሒደት ተሳታፊዎች ኩባንያውን ያግዛሉ፣ እነርሱም በፈንታቸው ከኩባንያው ክህሎት ይቀስማሉ።

ገነት ኤስኤፒ (SAP) በተባለው ኩባንያ የደንበኞች ፕሮጀክት ላይ በክላውድ ሶፍትዌር ዴቨሎፕመንት ተመድባ እየተማረች እንድትሰራ ስትመደብ “ክህሎቴን በደንብ አዳብሪያለሁ” ስትል ለዶይቼ ቬለ አስረድታለች። በጀርመን እና በሮሜንያ ከሚገኙ ቡድኖች ጋር ስትሰራ መቆየቷን የገለጸችው ገነት “የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን እንዳውቅ ዕድል ሰጥቶኛል” ብላለች።

የኬንያ እና የጀርመን የስደት እና የሰለጠኑ ሠራተኞች የሥራ ዕድል ሥምምነት

ጌቱ ለስምንት ወራት የሠራበት ቦህሪንገር ኢንገልኻይም በዓለም በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ ግዙፍ የመድሐኒት አምራች ኩባንያዎች አንዱ ነው። ቦህሪንገር ኢንገልኻይም ከተመሠረተ 140 ዓመታት ገደማ ያስቆጠረ ሲሆን በ130 ገበያዎች ከ53 ሺሕ በላይ ሠራተኞች አሉት። ለሰው እና ለእንስሳት የሚያገለግሉ መድሐኒቶች የሚያመርተው ኩባንያ የአንድ ቤተሰብ ንብረት ነው።

በቦህሪንገር ኢንገልኻይም “ብዙ ነገር ተምሪያለሁ” የሚለው ጌቱ የጀርመን ኮርፖሬት ኩባንያዎችን እውቀት እና አሰራር ለመገንዘብ ዕድል እንዳገኘ ይናገራል። ከዚህ በተጨማሪ በርቀት ያውቃቸው የነበሩ የግዙፍ ኩባንያዎች የቴክኖሎጂ ሥርዓቶች (systems) በተግባር እንዲረዳ አድርጎታል። የአፍሪካ ኮምት ፌሎውሺፕ አንደኛው ዓላማ ተሳታፊዎች የአመራር ክህሎት እንዲኖራቸው ማድረግ መሆኑን የገለጸው ጌቱ  የተመደቡለት “በጣም ጥሩ  ማናጀር” ኃላፊነት በመስጠት በኮርፖሬሽኑ ውስጥ “እንዴት ወርክ ሾፖች መምራት እንደሚቻል” እንዳስተማሩት አስረድቷል።

በጀርመን ኩባንያዎች እና በሀገሪቱ መንግሥት ድጋፍ የሚካሔደው አፍሪካ ኮምት መርሐ-ግብር አራት ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ከ15 የአፍሪካ ሀገሮች የተውጣጡ 41 ወጣቶች የሚሳተፉበት ነው።ምስል privat

የተማረ ሰው ኃይል ፍልሰት?

ጌቱ ውስብስብ የዳታ ሥርዓቶችን መሥራት እና ማስተዳደር የሚችል ኦንቶሎጂስት (Ontologist) ባለሙያ ሆኖ በባቫሪያ ግዛት በምትገኘው ሙኒክ ከተማ የሥራ ዕድል አግኝቷል። ገነትም በዚያው በኤስኤፒ (SAP) ኩባንያ ተቀጥራ የምትሠራበት ዕድል አግኝታለች። ይኸ አፍሪካ ኮምት የተባለው መርሐ-ግብር የሰለጠነ የሰው ኃይል ፍልሰትን ያበረታታ ይሆን ወይ? የሚል ሥጋት ያጭራል።

ገነት ግን እንደዚያ አይነት ሥጋት የላትም። አፍሪካ ኮምት “በኢትዮጵያ ከሌሉ ከትልልቅ ኩባንያዎች ጋር እንድትሠራ ዕድል ይከፍትልኃል። ለምሳሌ ኤስኤፒን የሚያህል ትልቅ ኩባንያ ኢትዮጵያ ውስጥ የለም” የምትለው ገነት “እነዚህ ትልልቅ ኩባንያዎች እንዴት እንደሚሠሩ፤ የጀርመን የሥራ ባህል ምን ዓይነት እንደሆነ እንድትማር ዕድል ይሰጥኃል” ስትል ታስረዳለች።

ተሳታፊዎች በኩባንያዎች ውስጥ የሚያሳልፏቸው ስምንት ወራት ክህሎቶቻቸውን አዳብረው በኮርፖሬት ተቋማት ውስጥ ያለውን ሁሉንም ነገር ተረድቶ ለመጨረስ እንደማይበቃ የምትናገረው ገነት “ያለውን ነገር ለአንድ ሁለት ዓመት በደንብ በመማር ከዚያ ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ ያሉ ቢዝነሶችን መርዳት፤ እህት እና ወንድሞቼን መምከር (mentor) ነው የምፈልገው” ስትል ተናግራለች።

“የተማረ ሰው ፍልሰት በእርግጥ አለ” የሚለው ጌቱ በአንጻሩ የሀገሪቱ አለመረጋጋት እና ዝቅተኛ ደመወዝ የሚከፈላቸው የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መምህራንን የሚፈታተነው የኤኮኖሚ ሁኔታ ገፊ ምክንያት እንደሆኑ ያስረዳል።  

ገነት በጀርመን የተመለከተቻቸው አይነት ግዙፍ ኮርፖሬት ኩባንያዎች ኢትዮጵያውያን መመሥረት እንደሚችሉ ታምናለች።ምስል privat

ገነት በጀርመን ያገኘችው ክህሎት እና እውቀት በኢትዮጵያ ለምትመኘው ለውጥ ላቅ ያለ ሚና እንደሚኖረው ታምናለች። “ኢትዮጵያ ሔጄ የሰዎችን አስተሳሰብ መቀየር እፈልጋለሁ። ለታናናሽ እህት እና ወንድሞቼ ከሰሩ ምንም ነገር እንደሚቻል ማሳየት እፈልጋለሁ” የምትለው ገነት ከተቀጠረችበት ኤስኤፒ ጋር በመተባበር የቀሰመችውን ክህሎት ወደ ኢትዮጵያ መውሰድ ትሻለች።

የኢትዮጵያ መንግሥት ሠራተኞች ከሚጠበቀው የደመወዝ ጭማሪ ለምን ተስፋ አጡ?

ጌቱ ፊቱን ወደ ሙኒክ ያቅና እንጂ ከመቐለ ዩኒቨርሲቲ ጋር ያለው ግንኙነት ሥራ ስላገኘ፣ ጀርመን ስለሚኖር “የሚበጠስ” እንዳልሆነ ይናገራል። አሁንም በመቐለ ዩኒቨርሲቲ ከሚገኙ ባልደረቦቹ ጋር ምርምር በመሥራት እና ሥልጠናዎች በመስጠት ላይ እንደሚገኝ የገለጸው ጌቱ “እኔ ወደዚህ በመምጣቴ ብዙ ዕድሎች ይከፈታሉ” የሚል አቋም አለው።   

ባለሙያዎች ርቀት ሳይገድባቸው በቴክኖሎጂ አማካኝነት መሥራት የሚችሉበት ዘመን በመሆኑ “እዚህ ሆኜም የማስተማር ዕድሉ ይኖረኛል። በፕሮጀክት የመተባበር ዕድሉ ይኖረኛል” በማለት አስረድቷል።

“ለመድረስ መጀመር አለብን”

ገነት ወደ ጀርመን ከማምራቷ በፊት በኢትዮጵያ የውበት ሳሎኖችን ከደንበኞቻቸው የሚያገናኝ ጀማሪ ኩባንያ ነበራት። በመጀመሪያ በቴሌግራም ገጽ ሥራውን ሲያካሒድ የቆየው “የእኔ ሳሎን” የተሰኘ ጀማሪ ኩባንያ ጸጉር ቤት ተከራይተው መሥራት የማይችሉ ሴት ባለሙያዎች ቤት ለቤት እየተንቀሳቀሱ ከደንበኞቻቸው እንዲገናኙ ጭምር የሚያግዝ ነበር። ገነት ከቴሌግራም ወደ ድረ-ገጽ ያሳደገችው አገልግሎት መዋቢያዎች የሚያመርቱ ሰዎች ለደንበኞቻቸው መሸጥ እንዲችሉ አመቻችቶ እንደነበር ለዶይቼ ቬለ ተናግራለች።

ወጣቷ ባለሙያ በጀርመን የተመለከተቻቸው አይነት ግዙፍ ኮርፖሬት ኩባንያዎች ኢትዮጵያውያን መመሥረት እንደሚችሉ ታምናለች። “ሩቅም ቢሆን በትንሹ መጀመር አለብን” የምትለው ገነት “እኛ እዚህ መጥተናል። ምን ስላደረጉ ነው እዚህ ደረጃ የደረሱት? የሚለውን ተምረን ቀስ በቀስ ተግባራዊ ማድረግ ስንጀምር የሚያጋጥሙንን ችግሮች እየፈታን በሒደት መድረስ እንችላለን” የሚል ዕምነት አላት።

እሸቴ በቀለ

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW