1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያውያን የደመቁበት የኦሪጎን አትሌቲክስ ሻምፒዮና

ሰኞ፣ ሐምሌ 11 2014

ኢትዮጵያውያን በጉጉት ሲጠብቁት በነበረው የኦሬጎን የሴቶች የማራቶን ውድድር ኢትዮጵያዊቷ ጎተይቶም ገብረስላሴ በአስደናቂ ብቃት አሸነፈች። ድንቅ አትሌት ፤ ጎተይቶም ገብረስላሴ ርቀቱን 2 ሰዓት ከ18 ደቂቃ ከ11 ሰከንድ በእንግሊዛዊቷ በራውላ ራድክሊፍ ተይዞ የነበረውን የሻምፒዮናውን ክብረ ወሰን በማሻሻል ጭምር ነው ያሸነፈችው ።

የሐምሌ 11 ቀን 2014 ዓ/ም የስፖርት ዝግጅት

This browser does not support the audio element.

ጤና ይስጥልን አድማጮች ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ምስራቅ አፍራቃውያን እየተካሄደ በሚገኘው የኦሬጎን አሜሪካ 2022 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በመካከለኛው እና የረዥም ርቀት ውድድሮች ገነው ታይተዋል። የዛሬው የስፖርት ዝግጅታችን ትኩረቱን በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በማድረግ በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት በተከናወኑ ዓለም አቀፍ ሌሎች አበይት ስፖርታዊ ዝግጅቶችን አካቷል ፤ ከዝግጅቱ ጋር ታምራት ዲንሳ ነኝ ፤

ከደቂቃዎች በፊት በተከናወነው እና ኢትዮጵያውያን በጉጉት ሲጠብቁት በነበረው የኦሬጎን የሴቶች የማራቶን ውድድር ኢትዮጵያዊቷ ጎተይቶም ገብረስላሴ በአስደናቂ ብቃት አሸነፈች። ድንቅ አትሌት ፤ ጎተይቶም  ገብረስላሴ ርቀቱን 2 ሰዓት ከ18 ደቂቃ ከ11 ሰከንድ በእንግሊዛዊቷ በራውላ ራድክሊፍ ተይዞ የነበረውን የሻምፒዮናውን ክብረ ወሰን በማሻሻል ጭምር ነው ያሸነፈችው ። ጎተይቶም እንደ ታምራት ቶላ ሁሉ የ175 ሺ ዶላር ተሸላሚ ትሆናለች ። በውድድሩ ከጎተይቶም ጋር ብርቱ ፉክክር ያደረገችው ኮሪር ሁለተኛ በመሆን የብር ሜዳሊያ ስታገኝ ፤ ትውልደ ኬንያዊቷ እስራኤላዊት ሶስተኛ ሆና የነሐስ ሜዳሊያ አግኝታለች። ኬንያ ከ10 ሜትር የሴቶች ውድድር በኋላ ሌላ መራር ሽንፈት አጋጥሟታል። ኢትዮዮጵያ በሻምፒዮናው ሶስተኛውን የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘት ችላለች። ኢትዮጵያ በአንድ የዓለም የአትሌቲክስ ሻምፒዮና በሁለቱም ጾታዎች ለዚያውም ክብረ ወሰን በማሻሻል ጭምር ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፤ እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት እንወዳለን።

ምስል Annegret Hilse/REUTERS

ትናንት እሁድ በተደረገ የወንዶች የማራቶን ውድድር የሻምፒዮንውን ክብረወሰን በማሻሻል ጭምር ኢትዮጵያዊው ታምራት ቶላ አሸናፊ መሆን ችሏል። ታምራት ቶላ ርቀቱን 2:05:36 ሰከንድ በሆነ ጊዜ በመግባት አሸናፊ ሆኗል። በውድድሩ ሌላው ኢትዮጵያዊ በአስደናቂ የጨራረስ ብቃት ትውልደ ሶማሊያ ፤ ቤልጂየማዊውን በሺር አብዲን በመቅደም ሁለተኛ ሆኖ የብር ሜዳሊያ አግኝቷል። ሞስነት የገባበትም ሰዓት 2:06:48 ሆኖ ተመዝግቧል። ቤልጅየማዊው በሽር አብዲ የቶክዮ ኦሎምፒክ የነሐስ ሜዳሊያው በኦሪጎን ደግሞታል። በትናንቱ የወንዶች የማራቶን ውድድር ሶስቱም ተወዳዳሪዎች በኬኒያዊው አቤል ኪሩኢ በጎርጎርሳውያኑ 2003 በፈረንሳይ ፓሪስ ተይዞ የነበረውን የሻምፒናውን ክብረ ወሰን 2:06.54 አሻሽለውታል። አሁን ክብረ ወሰኑ የኢትዮጵያዊው ታምራት ቶላ ሆኗል። የትናንቱ ድል ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ከያሉበት አስፈንድቋል። ድሉ በሁለት ተከታታይ ቀናት ሁለተኛ የወርቅ ሜዳሊያ በመሆኑም በርካቶች በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ ደስታቸውን በተለየ ሁኔታ ሲገልጹ ተስተውለዋል። ታምራት ቶላ በሸናፊነቱ እና የክብረ ወሰን ባለቤትነቱ 175ሺ የአሜሪካን ዶላር ተሸላሚ ይሆናል።

ታምራት ቶላ ውድድሩን ካሸነፈ በኋላ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጠው አስተያየት ፤ «በ2017 የሰራሁትን የቴክኒክ ስህተት አስተካክዬ አሸናፊ መሆን ችያለሁ »፤ ብሏል።

ምስል Patrick Smith/Getty Images/AFP

በማራቶን ውድድሩ የተሳተፈው ሴይፉ ቱራ 6ኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ በውድድሩ ትልቅ ግምት ተሰጥቶት የነበረው ሌሊሳ ዴሲሳ ውድድሩን ሳያጠናቅቅ ቀርቷል።

ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ ምሽት ተደርጎ በነበረው የሴቶች የ10 ሺ ሜትር የሩጫ ውድድር ፤ የክብረ ወሰኗ ባለቤት ፤ ክብሯን አስመልሳ እልህ አስጨራሽ በሆነ ሁኔታ ከኬንያውያን አንገት ለአንገት ተናንቃ አሸናፊ ሆናለች ፤ የትራክ ንግስቷ ለተሰንበት ግደይ ።

ለተሰንበት ውድድሩን በ30 ደቂቃ ከ09 ሰከንድ 94 ማይክሮ ሰከንድ በማጠናቀቅ  ስታሸንፍ ኬንያውያኑ ሔሌን ኦቢሪ እና ማርጋሬት ቼሊሞ 2ና እና 3ኛ በመሆን ተከትለዋት ገብተዋል። ለተሰንበት የርቀቱ የክብረ ወሰን ባለቤት ብትሆንም በኦሎምፒክም ሆነ በዓለም ሻምፒዮና ማሸነፍ ሳትችል ቆይታለች። ባለፈው ዓመት ሰኔ ላይ ጃፓን ቶኪዮ ተካሂዶ በነበረው ኦሎምፒክ በትውልደ ኢትዮጵያውያ የኔዘርላንዳዊቷ ሲፈን ሀሰን እና በባህሬናዊቷ ቃልኪዳን ገዛኸኝ ተቀድማ ውድድሩን ሶስተኛ ሆና ለማጠናቀቅ ተገዳ ነበር።  

ምስል Petr David Josek/AP/picture alliance

የኦሬጎኑን ውድድር በፍጹም አስደናቂ የአጨራረስ ብቃት ያጠናቀቀችው ለተሰንበት ፤ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጠችው ቃለ ምልልስ በእጄ ካለው ክብረ ወሰን በላይ የኡምፒዮናው አሸናፊ መሆን ያስፈልገኝ ነበር ብላለች። ከጎርጎርሳውያኑ 2019 ጀምሮ አሸናፊነቱን በናፍቆት ስጠብቅ ነበር ፤ ነገር ግን ሁሌም ኬኒያዊቷ ኦቢሪ ትከተለኛለች ስትል የተፎካካሪዋን ጥንካሬ ገልጻለች። አሁን ግን ኦቢሪን በጥንቃቄ እመለከት ነበር ፤ ሁሉንም በጥንቃቄ እመለከት ነበር ፤ የመጨረሻዎቹን 300 ሜትሮች እጅጉን ማፍጠን እንዳለብኝ በመረዳት ያንንu አድርጌ ህልሜን እውን አድርጌያለሁ ብላለች። ዘግየት ብለን ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ደግሞ የኬንያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለተሰንበት ግደይ ውድድሩን ማጠናቀቂያ ላይ በነበረው ትንቅንቅ ሄለን ኦቡሪን በክርን ተማታለች በማለት ክስ አቅርቦባት ነበር።  ነገር ግን ነገር ግን ዓለማቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን በወቅቱ የነበረውን ሁነት ከተመለከተ በኋላ ክሱን ውድቅ ማድረጉን አስታውቋል። በውድድሩ የተሳተፉት ሎሉቹ ኢትዮጵያውያን እጅጋየሁ ታዬ እና ቦሰና ሙላቴ ስድስተኛ እና ስምንተኛ  በመሆን አጠናቀዋል። በውድድሩ ስድስተኛ ሆና ያጠናቀቀችው እጅጋየሁ ታዬ በተለይ ለተሰንበት ላስገኘችው ውጤት የቡድን ስራ አስተዋጽዖ እንደነበራት ተመልክተናል።

ከኦሪገኑ የዓለም ሻምፒዮና ከኢትዮጵያውያንን የተሳትፎ ውጤት ሳንወጣ ትናንት በተደረገው የወንዶች የ10000 ሜትር የሩጫ ውድድር ኢትዮጵያውያኑ ድል አልቀናቸውም  ። ውድድሩን በርቀቱ የክብረ ወሰን ባለቤት የሆነው ዩጋንዳዊው ጆሺዋ ቼፕቴጊ አሸናፊ ሆኗል። ቼፕቴጊ ርቀቱን 27:27.43 ሲያጠናቅቅ ኬንያዊው  ስታንሌይ ዋይታካ ምቡሩ ሁለተኛ እንዲሁም ሌላው ዩጋንዳዊ ጃኮብ ኪፕሊሞ ሶስተኛ ሆኖ አጠናቋል። በውድድሩ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶት የነበረው እና የቶክዮ አሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊው ኢትዮጵያዊው ሰለሞን ባረጋ አምስተኛ ሆኖ አጠናቋል። ይህም ኢትዮጵያ በርቀቱ አስር ዓመታትን የተሻገረው አሸናፊነቷን ለማስመለስ የነበረው ተስፋ ሳይሳካ ቀርቷል። በውድድሩ  በሪሁ አረጋዊ 7ኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ  ታደሰ ወርቁ ደግሞ 14 ኛ ሆኖ  አጠናቋል።

ምስል Mike Segar/REUTERS

በአራተኛ ቀን የኦሬጎን ዉሎ በሀገሬው አቆጣጠር ምሽት ላይ በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ሊነጋጋ ሲል 11 ሰዓት ከ20 ደቂቃ ጀምሮ  በሚደረጉ የወንዶች የ3000 ሜትር መሰናክል እንዲሁም የሴቶች 1500 ሜትር የፍጻሜ ውድድሮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ይጠበቃሉ።

በተለይ ሌሊት 11፡20 በሚካሄደው የወንዶች 3 ሺህ ሜትር መሰናክል ፍጻሜ ውድድር ኢትዮጵያ ሜዳሊያ ልታገን እንደምትችል አስቀድሞ ግምት ተሰጥቷታል። በተለይ በውድድሩ የሚሳተፈው እና በቶክዮ ኦሎምፒክ የብር ሜዳሊያ ተሸላሚ የነበረው ለሜቻ ግርማ ከሞሮኮው ተቀናቃኙ ሶፍያኔ ኤልባካሊ ጋር ብርቱ ፉክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።  ኤልባካሊ በርቀቱ የቶኪዮ ኦሎምፒክ አሸናፊ ነበር። በውድድሩ ከለሜቻ ግርማ  በተጨማሪ ሃይለማርያም አማረ እና ጌትነት ዋለ ለፍጻሜው ውድድር ተሳታፊ መሆናቸውን ማጣሪያውን በብቃት ካለፉ በኋላ አረጋግጠዋል።

እዚያው ኦሬጎን ቆይተን በአራቱ ቀናት የተመዘገቡ ሜዳልያዎችን እና የደረጃ ሰንጠረዡን  ለመጠቆም ያህል ፤ ዩናይትድ ስቴትስ በ6 ወ,ርቅ 4 የብር እና 4 የነሐስ ሜዳሊያዎች በድምሩ 14 ሜዳሊያዎችን በማግኘት የደረጃ ሰንጠረዡን ስትመራ ፤ ኢትዮጵያ በ2 ወርቅ እና አንድ የብር ሜዳሊያ ፤ በሶስት ሜዳሊያዎች ሁለተኛ ፤ እንዲሁም ፖላንድ በአንድ የወርቅ እና ሁለት የብር ሜዳሊያዎች በሶስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችላለች። ቻይና እና ጃማይካ በእኩል 1 ወርቅ 1 ብር እና 1 ነሐስ 4ና ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። በአትሌቲክስ ዓለም የሁል ጊዜ የኢትዮጵያ ተቀናቃን ኬኒያ በ2 የብር እና 1 ነሐስ 10 ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

በሌላ ስፖርታዊ መረጃ ፤ በእንግሊዝ አዘጋጅነት እየተካሄደ ያለው 13ኛው የአውሮጳ የሴቶች እግር ኳስ ሻምፒዮና ቀጥሎ እየተካሄደ ነው። እንግሊዝ ለንደን የምትገኘው ባልደረባችን ኃይማኖት ጥሩነህን ስለውድድሩ በስልክ አነጋግሬአት ነበር ።

ምስል Haymanot Tiruneh/DW

እንግዲህ አድማጮች ለዛሬ በኦሬጎን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ያተኮረው የዕለቱ የስፖርት መሰናዷችን የእስካሁኑ ነበር ፤ ሳምንት በሌሎች ስፖርታዊ መሰናዶዎች ዳግም እንጠብቃችኋለን ፤ ጤና ይስጥልን።

ታምራት ዲንሳ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW