1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ኢትዮጵያ ለሱዳናዊያን ያቀረበችው የሰላም ጥሪና የአፍሪካ ኀብረት አቋም

እስክንድር ፍሬው
ዓርብ፣ ኅዳር 18 2019

ኢትዮጵያ ለሱዳን ኃይሎች ያቀረበችው የሰላም ጥሪ፣ የቀጠለ ውይይት እንዲኖር ለሚደረገው ጥረት አስተዋጽጾ የሚያደርግ መኾኑን የአፍሪካ ኀብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሐሙድ አሊ የሱፍ አስታወቁ። የሱዳን ባለሥልጣናት በሰላም ጥሪው ላይ ያንፀባረቁትን አቋም መመልከታቸውንም ጠቁመዋል።

የሱዳን ተቀናቃኝ ኃይላት መሪዎች አብዱል ፈታል አልቡርሃን እና መሀመድ ሃምዳን ዳጋሎ
የሱዳን ተቀናቃኝ ኃይላት መሪዎች አብዱል ፈታል አልቡርሃን እና መሀመድ ሃምዳን ዳጋሎ ፎቶ ከማኅደርምስል፦ SNA/IMAGO/Mahmoud Hjaj/IMAGO

ኢትዮጵያ ለሱዳናዊያን ያቀረበችው የሰላም ጥሪና የአፍሪካ ኀብረት አቋም

This browser does not support the audio element.

 

ኢትዮጵያ ለሱዳን ኃይሎች ያቀረበችው የሰላም ጥሪ፣ የቀጠለ ውይይት እንዲኖር ለሚደረገው ጥረት አስተዋጽጾ የሚያደርግ መኾኑን የአፍሪካ ኀብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሐሙድ አሊ የሱፍ አስታወቁ። የሱዳን ባለሥልጣናት በሰላም ጥሪው ላይ ያንፀባረቁትን አቋም መመልከታቸውንም ጠቁመዋል። ሂደቱ አሳታፊና በሱዳናዊያን ባለቤትነት የሚካሄድ መኾን እንዳለበትም ሊቀመንበሩ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለሱዳናዊያን ያቀረቡትን የሰላም ጥሪ በተመለከተ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ያወጡት መግለጫ አህጉራዊው ተቋም በጉዳዪ ላይ ያለው አቋም የተብራራበት ነው።

በጥንቃቄ የተጻፈው የአፍሪካ ኀብረት መግለጫ

የኮሚሸኑ ሊቀመንበር መሐሙድ አሊ ዮሱፍ እንዳሉት፣ በኢትዮጵያ የቀረበው ሐሳብ፣ በሱዳናዊያን መካከል ውይይትን ለማበረታታት እየተደረጉ ላሉ ቀጣይ ሂደቶች አስተዋጽኦ ያደርጋል። የአፍሪካ ኀብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር፣በጥንቃቄ የተጻፈ የሚመሰለውን መግለጫ ያወጡት ከሱዳን ተፋላሚ ወገኖች አንዱ የኾነውና በጄነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን የሚመራው ወታደራዊ መንግሥት፣ ኢትዮጵያ ገለልተኛ አለመሆኗን በመግለፅ ጥሪውን ውድቅ ባደረገ ማግስት ነው። የኮሚሽኑ ሊቀመንበር በመግለጫቸው፣ ይሄንን የሱዳን ባለሥልጣናት አቋም መመልከታቸውንም ጠቁመዋል። በዚህ የሱዳን ወታደራዊ መንግሥት አቋም ላይ ያላቸውን አስተያያት ግን በቀጥታ አላብራሩም። ሂደቱ አካታች፣ በሱዳናውያን የሚመራና ሱዳናውያን ባለቤት የኾኑበት መሆን እንደሚገባው ግን አስታውቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጥሪያቸውን አጠናክረዋል

ወታደራዊና ፖለቲካዊ ቡድኖችን እንደዚሁም የሲቪል አደረጃጀቶችን ጨምሮ ለኹሉም ሱዳናዊያን ወገኖች በሚል የቀረበው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጥሪ ሰፋ ያሉ ሐሳቦችና የውይይቱ አላማዎች የተገለጹበት ነው። ኢትዮጵያ ይሄንን ሐሳብ ስታቀርብ ከኹሉም አካላት ገለልተኛ ለመሆን ዝግጁነቷን ታረጋግጣለች በማለትም አስረድተዋል። ምክክሩ የብሔራዊ የአንድነት መንግሥት ምስረታን ያካተተ ሰፊ ፖለቲካዊ መግባባት ላይ የሚደረስበት እንደሚሆንም ጠቁመዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትናንት ለፓርላማ በሰጡት ማብራሪያም፣ ኹሉም ሱዳናዊያን ወገኖች የውይይት ጥሪውን እንዲቀበሉ በድጋሚ ጥሪ አቅርበዋል።

«ኢትዮጵያ አስተዋጽኦ አድርጋ የሱዳን ጉዳይ ወደነበረበት የሚመለስ ከኾነ፣ እኛ ጊዜያችንን፣ ገንዘባችንን ለማጥፋት ዝግጁ ነን። የሱዳን ኃይሎች ጠቃሚ ውጤት ሊያስገኝ ሰለሚችል ለዚህ የሰላም ጥሪ ምላሽ መስጠት አለባቸው» በማለት ተናግረዋል።

የሱዳን ተቀናቃኝ ኃይሎችን ለማሸማገል ኢትዮጵያ ያቀረበችው ሃሳብ የአፍሪቃ ሕብረትን ይሁንታ አግኝቷል። ፎቶ ከማኅደር ምስል፦ Marwan Ali/AP Photo/picture alliance

 

በጄነራል መሐመድ ሀምዳን ዳጋሎ የሚመራው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይልና የፖለቲካ አጋሮቻቸው በአትዮጵያ የቀረበውን ጥሪ እንደሚቀበሉት ገልጸዋል። ወደ 300 የሚጠጉ ድርጅቶችንና ተሳታፊዎችን ያቀፈውና በቀድሞው የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ የሚመራው የአብዮታዊ ኃይለች ሲቪል ዴሞክራሲያዊ ትብብር የተሰኘው ስብሰብም ጥሪውን ተቀብሏል።  ጄነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን የሚመሩት ወታደራዊ መንግሥት ግን የኢትዮጵያን ጥሪ ውድቅ እንዳደረገ ቀጥሏል። አዲስ አበባ ለሱዳን ፈጥኖ ደረሽ ኀይል ድጋፍ ታደርጋለች በማለትም ወንጅሏል።

በአደራዳሪዎች ላይ የሚነሱ የገለልተኝነት ጥያቄዎች

የሱዳንን የእርስበርስ ጦርነት በሚያደራድሩ ሃገራት ላይ የገለልተኝነት ጥያቄ ሲነሳ የመጀመሪያው አይደለም። በአጭር አገላለጽ «ኩአድ» በመባል ከሚታወቁትና የሱዳንን ግጭት ለመፍታት ከተሰባሰቡት ዩናይትድ ስቴትሰ፣ ዩናይትድ አረብ ኤምሬቶች፣ ሳዑዲ አረቢያና ግብፅ መካከል፣ ሦስቱ ከኹለቱ የሱዳን ተፋላሚ ወገኖች አንዱን ይደግፋሉ በሚል ጥያቄ ሲነሳባቸው ቆይቷል። ግብፅና ሳዑዲ አረቢያ በጄነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን የሚመራውን የሱዳን ጦር  ኃይል በመደገፍ ይጠረጠራሉ። ዩናይትድ አረብ ኤምሬቶች ደግሞ በጄነራል ሃምዳን ዳጋሎ ለሚመራው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ድጋፍ ታደርጋለች በሚል ስትጠረጠር ቆይታለች።

በጀርመን የዓለም አቀፍና የአካባቢ ጥናት ተቋም የሱዳን ጉዳይ ተመራማሪ የኾኑት ሃገር አሊ ለዶይቸ ቨለ እንደገለፁት፣ ዋሽንግተን የሃገራቱን የአደራዳሪነት ሚና በመቀበል በጋራ የምትሠራውም በኹለትዮሽ ግንኙነቷ ያላትን ጥቅም ለማስጠበቅ ነው።

«እነዚህ ሃገራት ተፋላሚዎቹን ወገኖች በመደገፍ በሱዳን ጦርነት ተሳታፊ እንደኾኑ ከመታሰባቸው አንጻር፣ እንዴት ዩናይትድ ስቴትስ እምነቷን በነሱ ላይ ጣለች? የሚለው ጥያቄ በጣም የሚያነጋግርና ጠቃሚ ጥያቄ ነው። ምክንያቱም አሁን ባለው ሁኔታ ሱዳን ስለ ጉዳይዋ ውይይት የሚደረግላት ከመኾን ይልቅ በ "ኩአድ" አባል ሃገራት መካከል ግንኙነቶችን ለማጠናከር፣ ተጨማሪ ስምምነቶችን ለመፈረምና የኹለትዮሽ ግንኙነቶችን ለማሻሻል መጠቀሚያ እየኾነች ነው» በማለት ገልጸዋል።

የተበታተኑ የሰላም ጥረቶችና የተፋለሚዎቹ ምርጫ

የሱዳንን የእርሰበርስ ጦርነት ለመሸምገል በሚል የተጀመሩ የሰላም ሂደቶች፣ የተለያዩና የተበታተኑ መኾናቸው እንደዚሁም የተጠያቂነት አለመኖር፣ ተፋላሚዎቹ ወገኖች ለሰላም ጥረቶች ትኩረት እንዳይሰጡ ማድረጉንም ሀገር አሊ ይናገራሉ።

«የሰላም ጥሪ ላይቀበሉ የሚችሉበት አንዱ ምክንያት ምንድን ነው፣ ይሄኛው ካልኾነ፣ ኩአድ ደግሞ ሌላ የሰላም ሐሳብ እንደሚያመጣ፣ ወይም በሂደት የኾነ ሌላ ነገር እንደሚሞከር ያውቃሉ። እና የፈለጉትን ለመምረጥና ለመውሰድ ፍጹም ነጻ ናቸው። በሰላም ሂደቶች አለመሳተፍ የሚያስከትለው የተጠያቂነት እርምጃም አነስተኛ ነው» በማለት አብራርተዋል።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የዘመን አቆጣጠር በሚየዚያ 2023 የተጀመረው የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት አሁንም ተባብሶ እንደቀጠለ ነው። 14ሚሊየን ሰዎች ከቀያቸው ተፈናቀለዋል- በርካቶችም ሕይወታቸውን አጥተዋል። የአፍሪካ ሕብረትና አለምአቀፍ አጋሮችም በሱዳን ጦር ኃይልና በፈጥኖ ደራሽ ኃይል መካከል ለሚካሄደውና ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ ላስከተለው ጦርነት እስካሁን ሰላማዊ መፍትሔ ማምጣት አልቻሉም።

እስክንድር ፍሬው

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

Edited by: ሸዋዬ ለገሠ Shewaye Legesse
ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW