1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ ለካፒታል ገበያ አገልግሎት አቅራቢዎች ፈቃድ መስጠት ልትጀምር ነው

Eshete Bekele
ረቡዕ፣ ጥር 15 2016

ኢትዮጵያ ለካፒታል ገበያ አገልግሎት አቅራቢዎች ፈቃድ ለመስጠት እየተዘጋጀች ነው። የኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ ሥራ ለመጀመር የኢንቨስትመንት ባንኮችን ጨምሮ አስራ አምስት የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪዎች ይፈልጋል። የአክሲዮን ድርሻዎች የሚያሻሽጡ ግለሰቦች እና ድርጅቶች ከኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን አዲስ ፈቃድ መውሰድ አለባቸው

ሜክሶኮ አደባባይ ወደ ብሔራዊ የሚወስደው መንገድ አዲስ አበባ የባንኮች ሕንጻ ይታያል
የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን የኢንቨስትመንት ባንኮችን ጨምሮ ለ15 የአገልግሎት አቅራቢዎች ፈቃድ ለመስጠት ተዘጋጅቷል። ምስል Eshete Bekele/DW

ኢትዮጵያ ለካፒታል ገበያ አገልግሎት አቅራቢዎች ፈቃድ መስጠት ልትጀምር ነው

This browser does not support the audio element.

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን፣ የኢንቨስትመንት ባንኮችን ጨምሮ ለካፒታል ገበያ አገልግሎት አቅራቢዎች ፈቃድ ለመስጠት የመጨረሻው የዝግጅት ምዕራፍ ላይ ደርሷል። ከባለሥልጣኑ ፈቃድ የሚሰጣቸው ድርጅቶች እና ግለሰቦች የኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ ሥራ ሲጀምር አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው።

የገበያውን ፍትኃዊነት፣ ግልጽነት እና ውጤታማነት የማረጋገጥ ኃላፊነት የተጣለበት ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን በአስራ አምስት የሥራ ዘርፎች ለሚሰማሩ የካፒታል ገበያ አገልግሎት አቅራቢዎች ፈቃድ ይሰጣል። አገልግሎት ሰጪዎቹ ተመዝግበው ሕጋዊ ፈቃድ የሚያገኙበት እና ሥራቸውን ሲያከናውኑ የሚገዙበት “የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪዎች ፈቃድ አሰጣጥ እና ቁጥጥር መመሪያ” ባለፈው ሣምንት ጸድቆ ሥራ ላይ ውሏል።

በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ከፍተኛ የሕግ አማካሪ የሆኑት አቶ ሲራክ ሰለሞን “መመሪያችን ያለፈው ሳምንት ጸድቋል። አሁን ማመልከቻዎች ለመቀበል ወደ መጨረሻው ዝግጅት ላይ ነን” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ ሥራ ሲጀምር የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪዎች ፈቃድ ወስደው ሚናቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆን እንደሚገባቸው የገለጹት አቶ ሲራክ ከ45 ቀናት ገደማ በኋላ “ማመልከቻዎች መቀበል እንጀምራለን” ሲሉ ሒደቱ የሚገኝበትን ደረጃ ለዶይቼ ቬለ አብራርተዋል።

መመሪያዉ በባለሥልጣኑ “አግባብነት ያለው የአገልግሎት ሰጭነት ፈቃድ ከተሰጣቸው በስተቀር ማንኛውም ሰው ቁጥጥር የሚደረግበትን የካፒታል ገበያ ሥራ ማከናወን እንደማይቻል” ይደነግጋል። የካፒታል አገልግሎት ሰጪዎችም ቢሆኑ ፈቃድ ለማግኘት የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ያስቀመጣቸውን “ዓለም አቀፍ መስፈርቶች” ማሟላት አለባቸው።

በየዘርፉ የሚሰማሩ የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪዎች ቁጥር ውስን እንደሚሆን ያስረዱት አቶ ሲራክ “ኢትዮጵያ አምስት ስድስት ኢንቨስትመንት ባንክ አላት። ከበቂ በላይ ነው” ሲሉ ተናግረዋል። በመመሪያው መሠረት ፈቃድ ከሚሰጣቸው መካከል የሰነደ ሙዓለንዋይ ደላላዎች፣ የሰነደ ሙዓለንዋይ ገበያ አከናዋኞች፣ የሰነደ ሙዓለንዋይ ዲጂታል ንዑስ ደላላዎች ይገኙበታል።

የኢትዮጵያ ባንኮች በካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪነት ለመሠማራት በስራቸው ተቀጥላ ኩባንያዎች ማቋቋም አለባቸውምስል Eshete Bekele/DW

የፈቃዶቹ ባለቤቶች ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ለግብይት ሲቀርቡ ሻጭ እና ገዢ የሚፈልጓቸውን አገልግሎቶች ያቀርባሉ። ፈቃድ ከሚሰጣቸው የካፒታል ገበያ አገልግሎት አቅራቢዎች መካከል የኢንቨስትመንት ባንኮች ይገኙበታል።

የኢንቨስትመንት ባንክ “በካፒታል ገበያ አንድ ኩባንያ ወይም የመንግሥት አካል ቦንድ ወይም የአክሲዮን ድርሻ መሸጥ ሲፈልጉ ያንን ከሕዝቡ ጋ፤ ከኢንቨስተሩ ጋ የሚያገናኝ፤ በምን ዋጋ፣ መቼ፣ ለማን [ይሸጥ] የሚለውን የማማከር አገልግሎት የሚሰጥ” እንደሆነ አቶ ሲራክ ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።

በካፒታል ገበያ ማቋቋሚያ አዋጅ መሠረት ከደንበኞቻቸው ተቀማጭ ሰብስበው በማበደር በሚያገኙት ትርፍ ሥራቸውን የሚያከናውኑ የንግድ ባንኮች በቀጥታ በኢንቨስትመንት ባንኪንግ የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪነት መሠማራት አይፈቀድላቸውም።

“ከታች ሌላ ተቀጥላ ኩባንያ (subsidiary companies) መስርቶ ነው መስራት የሚችለው” የሚሉት አቶ ሲራክ “ይኸ ባደጉት ሀገራት የሚሰራ አይነት ሥራ ነው” ሲሉ አስረድተዋል። የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ባንኮች “ተቀጥላ ኩባንያ በማቋቋም” በካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪነት እንዲሠማሩ እንደሚያበረታታ ያስረዱት አቶ ሲራክ ዋናው ተቆጣጣሪ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጭምር ሚና  እንዳለው ተናግረዋል።  

በባንክ ሥር በተቀጥላነት የሚቋቋሙ የኢንቨስትመንት ባንኮች ዝቅተኛ የመነሻ ካፒታል 100 ሚሊዮን ብር ነው። ከባንክ ውጪ በተወሰነ የሥራ ዘርፍ ላይ በማተኮር የሚቋቋሙ የኢንቨስትመንት ባንኮች ዝቅተኛ የመነሻ ካፒታል በአንጻሩ 25 ሚሊዮን ብር እንደሆነ አቶ ሲራክ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የፋይናንስ ገበያ ለውጭ ባንኮች ዝግ ቢሆንም ለካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪዎች ግን ክፍት ሆኗል። የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ገበያ እንዲገቡ የሚፈቅደው የፖሊሲ ማሻሻያ እስከ መጪው ሰኔ ባለው ጊዜ ሕግ ሆኖ ይጸድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምኅረቱ ተናግረዋል።

“ከውጪ የሚመጣ ተቋም የትኛውም ዘርፍ ላይ የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪ ሆኖ ፈቃድ መውሰድ ይችላል” የሚሉት አቶ ሲራክ የኢትዮጵያ ድርጅቶች በተለይም ባንኮች በካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪነት እንዲሰማሩ ከፍ ያለ ፍላጎት መኖሩን ጠቁመዋል።

የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ ገበያ እንዲሰማሩ የሚፈቅደው የፖሊሲ ማሻሻያ በሰኔ 2016 ገደማ ሕግ ሆኖ ይጸድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምኅረቱ ከዚህ ቀደም ተናግረዋል። ምስል CC BY 2.0/U.S. Institute of Peace

“የኢትዮጵያን ኢንቨስተር የሚያውቀው፤ የኢትዮጵያን ኩባንያዎች የሚያውቀው የኢትዮጵያ ባንክ እና የኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ ያለ ተቋም ይሆናል በሚል እሳቤ የሀገር ውስጥ ኩባንያዎች እንዲገቡ እናበረታታለን” ያሉት አቶ ሲራክ ነገር ግን “የውጭ ኩባንያዎች እንግባ ቢሉ እንከለክላለን ማለት አይደለም” ሲሉ ዘርፉ ለውጭ ባለወረቶች ክፍት እንደሆነ አረጋግጠዋል።

ዘንድሮ ሥራ እንዲጀምር ዕቅድ የተያዘለት የካፒታል ገበያ ለኢትዮጵያ አዲስ ባይሆንም ጥብቅ ቁጥጥር የሚሻ እና ውስብስብ የአሠራር ሥርዓት የሚከተል ነው። ከኢትዮጵያ መንግሥት ፈቃድ ወስደው የተለያዩ አክሲዮኖች በማሻሻጥ ሥራ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች እና ድርጅቶች በካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪነት ለመቀጠል የተቀመጠንውን መስፈርት አሟልተው አዲስ ፈቃድ መውሰድ ይኖርባቸዋል።

“በዋትስአፕ እና በቴሌግራም የሚያሻሽጡ ሰዎች አሉ። እነሱ በተቻለ መጠን ተደራጅተው፣ ሕጉን አውቀው ፈቃድ እንዲወስዱ እያበረታታናቸው ነው” ሲሉ አቶ ሲራክ አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ መንግሥት 25 በመቶ ድርሻ ሲኖረው የተቀረው 75 በመቶ በግሉ ዘርፍ የሚያዝ ነው። በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ሥር የሚገኙት የመንግሥት ተቋማት በ225 ሚሊዮን ብር ድርሻ ገዝተዋል።

ከግሉ ዘርፍ ዘመን ባንክ በ47.5 ሚሊዮን ብር ከኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ 5 በመቶ ድርሻ በመግዛት ቀዳሚው ሆኗል። አንድ የፋይናንስ ተቋም ከኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ ከ10 በመቶ በላይ ድርሻ መያዝ አይችልም። ገበያው ሲጀመር ባንኮች እና የመድን ኩባንያዎችን ጨምሮ 50 ገደማ ኩባንያዎች ድርሻዎቻቸውን ለሽያጭ እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል።

ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች በኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ በኩል ለግብይት የሚቀርቡበትን መሠረተ-ልማት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሞንትራን ከተባለ የአሜሪካ ኩባንያ ጋር ማዘጋጀት እንደጀመረ ባለፈው ሣምንት አስታውቋል።

ይኸ በእንግሊዘኛ ሴንትራል ሴኪዩሪቲስ ዲፖዚተሪ (Central Securities Depository) የተባለ መሠረተ-ልማት ሙዓለ ንዋዮች በኤሌክትሮኒክ ሰነድ የሚቀመጡበት፣ ግብይት ሲከናወን ከገዢ ወደ ሻጭ የሚዘዋወሩበት ጭምር ነው። ራሱን የቻለ ተቋማዊ ኅልውና የሚኖረውን መሠረተ-ልማት የመቆጣጠር እና የማስተዳደር ኃላፊነት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተሰጠ እንደሆነ አቶ ሲራክ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። 

አቶ ሲራክ የኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅን ሥራ ለማስጀመር የሚያስፈልገውን ዝግጅት ከስድስት እስከ ዘጠኝ ባሉ ወራት የማጠናቀቅ ዕቅድ እንዳለ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። አቶ ሲራክን ጨምሮ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣናት እና የሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ ሹማምንት ገበያው እውን ሲሆን ለሀገሪቱ ኤኮኖሚ ላቅ ያለ ፋይዳ ይኖረዋል የሚል ተስፋ ከወዲሁ ሰንቀዋል።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ

 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW