1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ 1.5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በቆሎ ለማቅረብ መስማማቷ ተነግሯል

ሰኞ፣ የካቲት 13 2009

በዝናብ እጥረት ድርቅ ያጠቃት ኬንያ የበቆሎ ምርቷ ክፉኛ አሽቆልቆሎበታል፡፡ በሀገሪቱ ያለውን እጥረት ለማቃለል ኢትዮጵያን ጨምሮ ከተለያዩ ሀገራት በቆሎ ለመግዛት ጥረት እያደረገች ትገኛለች፡፡ ስድስት ሚሊዮን የሚጠጋው ህዝቧ በድርቅ ምክንያት የምግብ እርዳታ እንደሚፈልግ ያሳወቀችው ኢትዮጵያ በቆሎ በርካሽ ለኬንያ ለማቅረብ መወሰኗ ጥያቄ አስነስቷል፡፡

Kenia Dadaab-Flüchtlingslager USA Aid
ምስል Getty Images/AFP/P. Moore

Amidst appeal for food aid Ethiopia to export maize to Kenya - FINAL - MP3-Stereo

This browser does not support the audio element.

በኢትዮጵያ በየ10 ዓመቱ እያሰለሰለ ይከሰት የነበረው ድርቅ በየዓመቱ ሀገሪቱን ያስቸግር ከያዘ ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ የአየር ጸባይ ለውጥን ተከትሎ በተከሰተው የዝናብ እጥረት ምክንያት ሚሊዮኖች በየዓመቱ የምግብ እርዳታ ፈላጊ እንደሆኑ አሉ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት እና ለጋሾች ባለፈው ጥር ወር ይፋ ባደረጉት የሰብዓዊ እርዳታ መጠየቂያ መሰረት 5.6 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ድርቁ የበረታው በምስራቅ እና ደቡብ የሀገሪቱ ክፍል ነው፡፡ በዚሁ አቅጣጫ ኢትዮጵያን የሚጎራበቷት ሶማሊያ እና ኬንያም በተመሳሳይ ሁኔታ በድርቅ መጠቃታቸውን አውጀው የዓለም አቀፍ ለጋሾችን እርዳታ ተማጽነዋል፡፡ በሁለቱ ሀገራት ያለው ሁኔታ አሳሳቢ እና ወደለየለት ረሃብ ሊለወጥ የሚችል እንደሆነ የረድኤት ድርጅቶች አስጠንቅቀዋል፡፡

በኬንያ ብቻ ሶስት ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ የምግብ እርዳታ እንደሚፈልግ የሀገሪቱ ቀይ መስቀል አስታውቋል፡፡ ድርቁ በምስራቅ አፍሪካዊቷ ሀገር የበቆሎ ምርት ላይም ጠባሳውን አሳርፏል፡፡ የኬንያ ጋዜጦች እንደዘገቡት ሀገሪቱ ስምንት ሚሊዮን ኩንታል በቆሎ እጥረት አለባት፡፡ አሁን በመጠባበቂያነት ያስቀመጠችውን ሊያስጉዛት የሚችለው እስከ ሰኔ ወር ድረስ ብቻ ነው፡፡

ይህን ችግር ለመፍታት ያለመው 10 ሀገራት አባል የሆኑበት ቀጠናዊ ድርጅት “ከፍተኛ ምርት አምርቼያለሁ” ባለችው ኢትዮጵያ እና በቆሎ ለመግዛት በሚሹ ሀገራት መካከል አገናኝ በመሆን ድርድር እያካሄደ ይገኛል፡፡ የምስራቅ አፍሪካ የእህል ማህበር የተሰኘው የእዚህ ተቋም ዋና ዳይሬክተር ጄራልድ ማሲላ ባለፈው ሳምንት ወደ ኢትዮጵያ ተጉዘው ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መነጋገራቸውን ለዶይቸ ቨለ ገልጸዋል፡፡

ምስል picture-alliance/dpa/S. Morrison

“ከኢትዮጵያ ወገን ትርፍ የእህል ምርት አለ፡፡ በዚህ ወቅት ጥሩ ምርት ተመርቷል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት በቀጠናው ለሚገኙ እና በዘርፉ ላሉ ባለጉዳዩች ጉዳዩን አሳውቆ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ያሉ የህብረት ስራ ማህበራት እና አምራቾች ትርፍ ምርታቸውን በቀጠናው ይሸጡ ዘንድ ዕድሎችን እንዲያመቻቹ ም ጠይቋል፡፡ ይህ ደግሞ እንደ መልካም ዕድል ነው የታየው፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ለረጅም ዓመታት በቆሎ ወደ ውጪ እንዳይላክ ከልክላ ነበር፡፡ ለዚህ ትርፍ ምርት ተገቢውን ገበያ ለማስገኘት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ስንነጋገር ቆይተናል፡፡ በኢትዮጵያ ያሉ አምራቾችና ሻጮችን በማነጋገር የንግድ ልውውጡ በሁለትዮሽ ደረጃ በኢትዮጵያ እና ኬንያ መካከል እንዲደረግ እየሞከርን ነው፡፡ በቀጠና ደረጃ ደግሞ በኢትዮጵያ እና እንደ ኡጋንዳ፣ ታንዛንያ እና ሩዋንዳ ያሉ ሌሎች የቀጠናው ሀገራት ጋር መካከል እንዲሆን ነው፡፡ የሎጀስቲክ ሁኔታ ከፈቀደልን እስከ ማላዊ ለመድረስ ነው የምናስበው” ይላሉ፡፡

እስካሁን ባለው ድርድር መሰረት ኢትዮጵያ 1.5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በቆሎ ለኬንያ ለማቅረብ መስማማቷን ዳይሬክተሩ ይናገራሉ፡፡ ጉዳዩ በሁለቱ ሀገራት መንግስታት በኩል አሁንም በድርድር ላይ ያለ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ በኢትዮጵያ በኩል ድርድሩን የሚያካሄድ የልዑካን ቡድን በዚህ ሳምንት መጨረሻ ወደ ናይሮቢ ኬንያ እንደሚጓዝም ይገልጻሉ፡፡

“በድርቅ ምክንያት ሚሊዮኖች የምግብ እርዳታ በሚፈልጉበት በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ እንዴት በቆሎ ለመሸጥ ተስማማች?” ስንል ላቀረብንላቸው ጥያቄ ተከታዩን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

“በተወሰኑ ክልሎች ድርቅ አለ፡፡ በሌሎቹ ደግሞ የለም፡፡ ጥቂት ክልሎች ጥሩ ምርት አምርተዋል፡፡ ሁለተኛ ደግሞ የምግብ ምርጫ ጉዳይ አለ፡፡ በኢትዮጵያ በድርቅ የተጎዱት አብዛኞቹ ክልሎች በዋነኛነት የሚጠቀሙት ጤፍን እና ስንዴን ነው፡፡ የበቆሎ ዋና ተጠቃሚ አይደሉም፡፡ ይህ የንግድ እድልም መጥቶም ቢሆን እንኳ በሀገር ውስጥ የሚደረገውን የበቆሎ ግብይት አይስቆመውም” ሲሉ መከራከራያቸውን አቅርበዋል፡፡

በኢትዮጵያ ድርቅ ያጠቃቸው በሚል የተለዩ አካባቢዎች በቆላማና በአርብቶ አደር አካባቢዎች ያሉ ናቸው፡፡ በደቡብ አቅጣጫ የኦሮሚያዎቹ ባሌ እና ቦረና፤ በምስራቅ ደግሞ ሶማሌ ክልል የድርቅ ተጎጂዎች በብዛት ያሉባቸው ናቸው፡፡ የብሔራዊ አደጋ ስራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ በእነዚህ አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች በቆሎን በዋነኛነት ባያመርቱም ለምግብነት ግን እንደሚጠቀሙ ይናገራሉለ፡፡ በመስሪያ ቤታቸው በኩል በየወሩ እየቀረበ የሚገኘው እርዳታ ግን 15 ኪሎ ስንዴ፣ ጥራጥሬ፣ አልሚ ምግብ እና ዘይት እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ኢትዮጵያ ለኬንያ በቆሎ ለመሸጥ ስለማሰቧ መስሪያ ቤታቸው መረጃ እንደሌለውና ጉዳዩ የሚመለከተውም የንግድ ሚኒስቴር እንደሆነ ለዶይቸ ቨለ ገልጸዋል፡፡ 

 

ተስፋለም ወልደየስ

አርያም ተክሌ

  

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW