1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ኢትዮጵያ ለ14 ዓመታት የገነባችው የኅዳሴ ግድብ ተመረቀ

ሰለሞን ሙጬ
ማክሰኞ፣ ጳጉሜን 4 2017

ኢትዮጵያ ላለፉት 14 ዓመታት የገነባችው የኅዳሴ ግድብ ዛሬ ጳጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ. ም ተመረቀ። የመሠረት ድንጋዩ በ2003 ዓ.ም የተቀመጠው ይህ ግዙፍ ግድብ ያልተቋረጠ ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ጫና ያልተለየው ነው።

ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ጳጉሜ 4 ቀን 2017 ተመረቀ
ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ጳጉሜ 4 ቀን 2017 ተመረቀምስል፦ Luis Tato/AFP

ኢትዮጵያ ለ14 ዓመታት የገነባችው የኅዳሴ ግድብ ተመረቀ

This browser does not support the audio element.

 

በግድቡ የምርቃት ሥነ ሥርዓት ላይ ከኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተጨማሪ የጂቡቲ፣ የኬንያ፣ የደቡብ ሱዳን እና የሶማሌያ ፕሬዚዳንቶች፤ የአፍሪካ ሕብረት እና የኢጋድ መሪዎች ታድመዋል። በግድቡ ምርቃት ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ ግድቡ «ለጥቁር ሕዝቦች በሙሉ ታሪክ ሆኖ የሚኖር ታላቅ ገድል ነው» ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ «ኢትዮጵያ ኅዳሴን የሠራችው ለመበልጸግ፣ አካባቢውን በብርሃን ለመሙላት፣ የጥቁር ሕዝብ ታሪክ ለመቀየር እንጂ በፍጹም ወንድሞቿን ለመጉዳት አይደለም» ነው ያሉት።

ግድቡ «ለጥቁር ሕዝቦች በሙሉ ታሪክ ሆኖ የሚኖር ታላቅ ገድል ነው» ጠ/ሚ አብይ 

ለ14 ዓመታት በግንባታ ሂደት የከረመው የኅዳሴ ግድብ  233 ቢሊየን ብር ወጪ ተደርጎበት ተጠናቆ ዛሬ ጳጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ. ም በይፋ ተመርቋል። ይህ በየዓመት «አንድ ቢሊየን ዶላር ገቢ ያስገኛል» የተባለለት ከግብጽ እስከ አረብ ሊግ፣ ከሱዳን እስከ የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት፣ መቋጫ ከሌለው ድርድር እስከ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የግድቡ ገንቢ እኛ ነን ንግግር ለዓመታት ብርቱ ዓለም አቀፍ ጉዳይ፤ ደግሞም መነጋገሪያ የሆነው የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ የመሠረት ድንጋዩን ያስቀመጡት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትርም ሆኑ የመጀመርያው የግድቡ ሥራ አስኪያጅ በሕይወት አልፈው በተተኪ መሪዎች ዛሬ ተመረቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ ግድቡ በዚህ ትውልድ በመሠራቱ «የኢትዮጵያ የልመና፣ የስንፍና፣ የእንጉርጉሮ ዘመን አብቅቶ በልኳ የምትለካበት ዘመን» የመምጣቱ ጉልህ ማረጋገጫ መሆኑን በዚያ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ለታደሙት እና በቴሌቪዥን ለተከታተላቸው ተናግረዋል።

በግድቡ ምርቃት ላይ የተገኙ የሃገራት መሪዎች

በኅዳሴ ግድብ የምርቃት ሥነ- ሥርዓት ላይ ከኢትዮጵያውያን ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በተጨማሪ የጂቡቲ፣ የኬንያ፣ የደቡብ ሱዳን እና የሶማሌያ ፕሬዚዳንቶች፣ የቤርባዶስ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የአፍሪካ ሕብረት እና የኢጋድ መሪዎች እና የተቋማት መሪዎች ታድመዋል። የመገናኛ ብዙኀንም ተመርጠው የተጋበዙ ሲሆን ዶቼ ቬለ በስፍራው ተገኝቶ ለመዘገብ ከወራት በፊት ጥያቄ ቢያቀርብም ፈቃድ ማግኘት አልቻለም።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በኅዳሴ ግድብ ምርቃት ላይ ምስል፦ Luis Tato/AFP/Getty Images

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ ለታችኛው ተፋሰስ ሃገራት ባስተላለፉት መልዕክት «እኛ ተጠቅመን ማንንም የመጉዳት ፍላጎት፣ መሻት ስለሌለን ለወደፊት በምንሠራቸው» ባሏቸው ሥራዎች «በትብብር፣ በጋራ እንድንቆም» ሲሉ አሳስብዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአንድነት ጥሪ ባስተላለፉበት መልዕክታቸው «ለቅርብ እና ለሩቅ ጠላቶቻችን» ላሏቸው ግን በስም ላልጠቀሷቸው ኃይላት «ከእኛ ጋር መጋጨት ሳይሆን መስማማት ብቻ ነው የሚያዋጠው» ብለዋል። በሚቀጥሉት ዓመታትም የ30 ቢሊየን ዶላር መሠረተ ልማቶች እንደሚገነቡ ከዚህም ውስጥ ለሰላማዊ አገልግሎት የሚውል የኒውክሌር ተቋም እንደሚገኝበት ገልፀዋል።

ከግድቡ ተደራዳሪ ቡድን አባላት አንዱ ምን ተሰማቸው?

በግድቡ ላይ ለሚነሱ ጥያቄዎች የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስከበር የተሰየመው ተደራዳሪ ቡድን አባል የሆኑት ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ በግድቡ መመረቅ የተሰማቸውን ከብዙ በጥቂቱ ለዶቼ ቬለ አጋርተዋል። «የሕልውናም፣ የልማትም መሠረት የሆነ ፕሮጀክት ውጣ ውረዱም ቢበዛበት፤ በትዕግስት፣ በትብብር እና ወድቆ በመነሳትም ጭምር እዚህ ደረጃ መድረሱ፤ ትልቅ የሀገራችን በሌላም ጉዳይ ተባብሮ ፀንቶ የመሥራት ምሳሌ የሚሆን ውጤት ስላገኘን በጣም ደስ ብሎኛል።» ብለዋል።

የግድቡ የምርቃት ሥና- ሥርዓት ትናንት ሰኞ ጀምሮ በዋዜማው የተከናወነ ነው። ግድቡ በከፍተኛ መስውልዕትነት የተገነባ መሆኑን ለማሳየት በሚል «የደም፣ የላብ እና የውኃ ጠብታ ምልክት» ነው የተባለ ሐውልትም እዚያው ጉባ ላይ ተመርቋል።

በተመሳሳይ ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ በግድቡ ግንባታ ላይ ለቆዩ የሥራ ኃላፊዎች የአገሪቱ የክብር ኒሻን ሽልማት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተበርክቶላቸዋል። በዚህ ሽልማት ላይ የመጀመርያው የግንባታው ሥራ አስኪያጅ የኢንጂኒየር ስመኘው በቀለ ስም አልተካተተም ወይም ሲጠራ አልተደመጠም።

ተጋባዥ የሃገራት መሪዎች ንግግር ያደረጉ ሲሆን «የኢትዮጵያ ጉሮሮ» የምትባለው የጎረቤት ሀገር ጅቡቲ ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ዑማር ጊሌህ በሚታወቁበት የአማርኛ ቋንቋ ችሎታቸው ሕዳሴ ግድብን «ዓለምን ያስደነቀ፣ የአፍሪካ ፕሮጀክት ነው» ብለውታል።

ሰሎሞን ሙጬ

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW