1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ኢትዮጵያ ሒደቱን ለማደናቀፍ ከድርድር ቀርታለች ስትል ግብፅ ከሰሰች

ሰኞ፣ የካቲት 23 2012

ኢትዮጵያ ሥምምነት ሳይደረስ ታላቁ የኅዳሴ ግድብን በውኃ ለመሙላት መወሰኗ ዓለም አቀፍ ሕግጋትን የሚጣረስ፤ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ ከአምስት አመታት በፊት የተፈራረሙትን ስምምነትም የሚጥስ ነው ስትል ግብፅ ከሰሰች። በአሜሪካ እና በዓለም ባንክ የተዘጋጀው «ፍትኃዊ እና ሚዛናዊ» ሥምምነት ኢትዮጵያ ሙሉ ተሳትፎ ያደረገችበት ነው ብላለች።

BG Grand Renaissance Dam | Der äthiopische Premierminister Abiy Ahmed Ali mit dem ägyptischen Präsident Abdel-Fattah al-Sisi (2018)
ምስል፦ Imago Images/Xinhua

ኢትዮጵያ ከታላቁ የኅዳሴ ግድብ ግንባታ ጎን ለጎን ውኃ ለመሙላት የደረሰችበትን ውሳኔ እንደማትቀበል ግብፅ አስታወቀች። የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የውኃ ሐብት እና መስኖ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች በዛሬው ዕለት ባወጡት መግለጫ ኢትዮጵያ ሥምምነት ሳይደረስ ግድቡን በውኃ ለመሙላት መወሰኗ ዓለም አቀፍ ሕግጋትን የሚጣረስ፤ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ ከአምስት አመታት በፊት የተፈራረሙትን ስምምነትም የሚጥስ ነው ሲሉ ከሰዋል።

ግብፅ በዓለም ባንክ እና በአሜሪካ ግብጽ እንደምትለው በአሜሪካ እና በዓለም ባንክ የተዘጋጀው ሰነድ ከዚህ ቀደም ሥምምነት የተደረሰባቸውን አንቀፆች እና ማሻሻያዎች ያካተተ ነው።

የኢትዮጵያ ግን ሥምምነቱ  «የሶስቱ ሀገራት የድርድርም ሆነ የሕግ እና ቴክኒክ ቡድኖች ውይይት ውጤት አይደለም» ስትል በትናንትናው ዕለት እንደማትቀበለው ገልጻለች። «የቴክኒክ ጉዳዮች ድርድሩም ሆነ የሕግ ማዕቀፍ ዝግጅቱ ላይ የሚደረገው ድርድር አልተጠናቀቀም» ያለችው ኢትዮጵያ ከታላቁ የኅዳሴ ግድብ ግንባታ ጎን ለጎን  «በፍትሐዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀም እና ጉልህ ጉዳት ያለማድረስ መርሆዎች መሰረት» የውኃ ሙሌት እንደምትቀጥል ገልጻለች።

ኢትዮጵያ በአሜሪካ የተዘጋጀውን ሥምምነት እንደማትቀበል የገለጸችበት መግለጫ እርስ በርሱ የሚጋጭ እና የተዛነፉ ሐቆች (facts) ያሉበት ነው ስትል ግብጽ አጣጥላለች። ኢትዮጵያ ከመጨረሻው ድርድር የቀረችው ሒደቱን ለማደናቀፍ ነው ስትል የከሰሰችው ግብፅ አሳዝኖኛል ያለችውን የኢትዮጵያ አቋም እንደማትቀበልም አስታውቃለች።

«የታላቁ የኅዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ሙሌት እና የውኃ አለቃቅ መመሪያ እና ደንብ የሚዘጋጀው በሶስቱ ሀገራት ብቻ ነው» ያለችው ኢትዮጵያ አሜሪካ እና የዓለም ባንክ ለሶስቱ አገራት የሥምምነት ሰነድ ማዘጋጀታቸውን እንደማትቀበል ገልጻለች። 

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW