1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ኢትዮጵያ "ቁልፍ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች" ርእሠ ብሔር ታዬ አጽቀ ሥላሴ

ሰለሞን ሙጬ
ሰኞ፣ መስከረም 26 2018

ፕሬዝደንት ታዬ "በየቦታው የሚታዩ ግጭቶችን በኃይል ማስተካከል የሚቻል ቢሆንም" መንግሥት ዘላቂ ሰላም የሚረጋገጠው በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንደሆነ ያምናል ሲሉ ተናግረዋል። መንግሥት አንድነትና ሰላምን ለማጽናት ሕዝባዊ ተቋማትን መገንባት፣ ለሕዝብ የቀረበ እና የታመነ ያሉት አስተዳደርን መዘርጋ ላይ አተኩሮ ይሠራል ብለዋል

የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀስላሴ
ርእሠ ብሔር ታዬ አጽቀ ሥላሴ ኢትዮጵያ "ቁልፍ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች" አሉምስል፦ Office of the Prime Minister of Ethiopia

ኢትዮጵያ "ቁልፍ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች" ርእሠ ብሔር ታዬ አጽቀ ሥላሴ

This browser does not support the audio element.

ኢትዮጵያ መንግሥት "የእርቅ እና የሰላም አማራጮችን በመከተል የሀገሪቱን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ እየሠራ ይገኛል" ሲሉ ርእሠ ብሔር ታዬ አጽቀ ሥላሴ ተናገሩ። ርእሠ ብሔር ታዬ ይህንን ያሉት ዛሬ ሰኞ የሕዝብ ተወካዮች እና የፌደሬሽን ምክር ቤቶችን የ2018 ሥራ ዛሬ ሲከፍቱ ነው።
 
"በየቦታው የሚታዩ ግጭቶችን በኃይል ማስተካከል የሚቻል ቢሆንም" መንግሥት ዘላቂ ሰላም የሚረጋገጠው በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንደህነ ያምናል ሲሉም የዚህ ዓመት አንዱ የመንግሥት ቁልፍ የሥራ መስክ ይህ መሆኑን ጠቅሰዋል። መንግሥት አንድነት እና ሰላምን ለማጽናት ሕዝባዊ ተቋማትን መገንባት፣ ለሕዝብ የቀረበ እና የታመነ ያሉት አስተዳደርን መዘርጋት፣ የዜጎችን ፍትሕ የሚያስጠብቅ የፍትሕ ሥርዓት መገንባት ላይ አተኩሮ ይሠራልም ብለዋል።

ከጎረቤት ሀገራት ጋር "ትብብር እና የጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ" ግንኙነት መመሥረት ከመንግሥት ዐበይት ተግባራት መካከል መሆኑን የጠቀሱት ፕሬዝዳንት ታዬ መንግሥት "አለመግባባቶችን በሰላም ይፈታል" ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የዓመቱ ዐበይት ተግባራት ምንድን ናቸው?

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ርእሠ ብሔር ታዬ አጽቀ ሥላሴ 40 ደቂቃ በፈጀው የሁለቱ ምክር ቤቶች የመክፈቻ ንግግራቸው መንግሥት ባለፈው ዓመት አሳክቷል ያሉትን በስፋት ዘርዝረዋል። ሀገሪቱ 8.8 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቧንና በ2018 የ9 በመቶ ዕድገት ለማስመዝገብ ውጥን መያዟንም ይፋ አድርገዋል።

ሀገሪቱ "ቁልፍ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች" ያሉት ርእሠ ብሔሩ ኢትዮጵያ "የህልውና አደጋ" ገጥሟት እንደነበርና "አለመግባባትን በሰላም ለመፍታት" ጥረት እየተደረገ መሆኑን በማብራራት ሰላምን ማጽናት የዚህ ዓመት የመንግሥት አንዱ ጉልህ የሥራ መስክ መሆኑን ጠቅሰዋል።

"ምንም እንኳን በየጊዜው የሚስተዋሉ የኃይል እንቅስቃሴዎችን ለማስቆም መንግሥት ሙሉ ዝግጁነት እና ዘመናዊ አቅም ቢኖረውም የዛሬውን ግጭት በማሸነፍ ለነገው ትውልድ ቂምና ቁርሾ አናወርስም የሚል መርህ በመከተል" ችግሮችን በትዕግስት ማለፍን መርጧልም ብለዋል።

"በየቦታው የሚታዩ ግጭቶችን በኃይል ማረቅ፣ ማስተካከል የሚቻል ቢሆንም ዘላቂ ሰላም የሚረጋገጠው ግን በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንደሆነ መንግሥት ጽኑ ዕምነት አለው።"

የተቋማት ግንባታ ሌላኛው ዐበይት የመንግሥት የሥራ ዘርፍ ይሆናል ተብሏል

ርእሠ ብሔር ታዬ "ከሥርዓት መለዋወጥ ጋር የማይናዱ ነጻ፣ ገለልተኛ እና ሕዝባዊ ብሔራዊ ተቋማትን ለመፍጠር መንግሥት ጽኑ መሠረት በመጣል ላይ ይገኛል" ያሉ ሲሆን ተቋማትን የመገንባት ሥራ ሌላኛው መሠረታዊ ያሉት ጉዳይ ስለመሆኑ የሀገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ጨምሮ የሀገራት ተወካዬች እና እንግዶች በተገኙበት የመክፈቻ ንግግራቸው ላይ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ 6ኛ የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመናቸውን ዛሬ ፕሬዝደንት ፕሬዝደንት ታዬ አፅቀሥላሴ ባሰሙት ንግግር ጀምረዋልምስል፦ Solomon Muche/DW

"አንድነታችን እና ሰላማችንን በማይናወጥ ደረጃ ላይ ለማድረስ መንግሥት በተቋማት ግንባታ ላይ አበክሮ ይሠራል።"

በፕሬዝዳንቱ አንድ ሁለት ተብለው ከተጠቀሱ ሌሎች የመንግሥት የዚህ ዓመት የትኩረት መስኮች "ለሕዝብ የቀረበ እና ለሕግ የታመነ" ያሉት "አስተዳደር እውን ለማድረግ ጥረት ማድረግ" የሚለው ይገኝበታል። "መንግሥት የዜጎችን ዋስትና የሚያስጠብቅ የፍትሕ ሥርዓት ለመዘርጋት በ2018 በጀት ዓመት በትጋት ይሠራል።"

ከጎረቤት ሀገራት ጋር ስለሚኖር ግንኙነት እና የኢትዮጵያን የውኃ ተጠቃሚነት በተመለከተ

ርእሠ ብሔር ታዬ ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲ መስክ "አጀንዳ ተላሚ እና ተጽዕኖ ፈጣሪ" እየሆነች መሆኑን በዚሁ ንግግራቸው ገልፀዋል። "ዜጋን ማዕከል ያደረገ ብሔራዊ ደኅንነት" እንዲሁም ሀገሪቱ በዓባይ እና በቀይ ባሕር መሃል እንደመገኘቷ መጠን ፍትሐዊ ባልሆነ መልኩ ተገልላበታለች ካሉት የውኃ ሀብት "ትብብርን፣ ትስስርን፣ ዲፕሎማሲያዊ እና ሰላማዊ አማራጭን በመከተል" እንድትጋራ ይደረጋል ብለዋል።

"የቀጣናችንን የጋራ የመልማት ፍላጎት ያገናዘበ ትብብር እና ትስስርን ለማጠናከር ዲፕሎማሲያዊ እና ሰላማዊ ጥረቶች ይደረጋሉ።"

7ኛው ዙር ሀገራዊ ምርጫ በኢትዮጵያውያን ተዓማኒ እንዱሆን በኃላፊነት ይሠራል

በዛሬው የሕዝብ ተወካዮች እና የፌደሬሽን ምክር ቤቶች የመክፈቻ ጉባኤ ላይ 511 የሁለቱ ምክር ቤቶች አባላት ተገኝተዋል። የሀገሪቱ ርእሠ ብሔር "በያዝነው ዓመት የሚካሄደው ሰባተኛው ዙር ምርጫ ፍትሐዊ፣ ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊ እና በኢትዮጵያውያን ዘንድ ተዓማኒ ይሆን ዘንድ መንግሥት በኃላፊነት ይሠራል" ብለዋል።

ዶቼ ቬለ ባለፈው ሳምንት አስተያየታቸውን አስቀድሞ የጠየቃቸው የተወሰኑ ሰዌች መንግሥት በዓመቱ ሰላምን እንዲያሰፍን፣ ግጭቶችን እንዲያስወግድ ኃላፊነቱን እንዲወጣ፣ አንድነት ላይ እንዲያተከር እና የዜጎችን ኢኮኖሚ በሚያሳድጉ ተግባራት ላይ እንዲንቀሳቀስ ጠይቀው ነበር።

ሰለሞን ሙጬ

እሸቴ በቀለ

ፀሀይ ጫኔ
 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW