1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ኢትዮጵያ በሕግ የበላይነት መለኪያ ከ140 ሃገሮች 123 ደረጃ ላይ ተቀመጠች

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 26 2015

የህግ የበላይነት በመላው ዓለም እያሽቆለቆለ መሄዱን የዓለም ፍትሕ ፕሮጀክት አስታወቀ። መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው የዓለም ፍትሕ ፕሮጀክት ማኀበር ዘንድሮ በ140 ሃገራት ባወጣው ደረጃ ኢትዮጵያን ጨምሮ 61 በመቶ በሚሆኑት ሃገሮች የሕግ የበላይነት እየተዳከመ ሄዷል። ኢትዮጵያ በሕግ የበላይነት መለኪያ ከ140 ሃገሮች 123 ደረጃ ላይ ትገኛለች።

Göttin Justitia
ምስል፦ picture-alliance/dpa/U. Baumgarten

ኢትዮጵያ በሕግ የበላይነት መለኪያ ከ140 ሃገሮች 123 ደረጃ ላይ ተቀመጠች

This browser does not support the audio element.

የሕግ የበላይነት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለአምስተኛ ተከታታይ ዓመታት እያሽቆለቆለ መሄዱን ያመለከተው የማኀበሩ ደረጃ ዋነኛ ምክንያቶቹ ደግሞ የአምባገነን አስተዳደር አዝማሚያዎች ማቆጥቆጥና የኮቪድ 19 በሽታ ያመጣው ጫና መሆናቸውን ጠቁሟል።

ማኀበሩ ይፋ ያደረገው ደረጃ እንዳለው የሕግ የበላይነት ማሽቆልቆሉ ከባለፈው ዓመት የዘንድሮው እጅግ የከፋ ሲሆን የኮቪድ መዘጋት በሚያስገርም ሁኔታ የፍትሕ ስርዓቶችን ሲያስተጓጉል መንግስታት የዜጎችን ነፃነት የሚገታ ዘዴዎችን ተጠቅመዋል።

የኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ ከመከሰቱ በፊት፣የነበሩ የፈላጭ ቀራጭ አገዛዝ አዝማሚያዎች፣ለምሳሌ በአስፈጻሚ አካላት ላይ ደካማ ቁጥጥር መኖር፣በመገናኛ ብዙኃን ላይ የሚደርሰው ጥቃት የሕግ የበላይነት መሸርሸሩን እንዲቀጥል አድርጓል ብሏል።

የኢትዮጵያን የሕግ የበላይነት ደረጃ በተመለከተ ዶይቸ ቨለ የጠየቃቸው የዓለም ፍትሕ ፕሮጀክት ተባባሪ ዳይሬክተር አሊሺያ ኢቫንጀሊደስ እንደተናገሩት፣በዚህ ዓመት በሦስት ነጥብ ስድስት በመቶ ቀንሷል። ካለፈው ዓመት አንጻር ሲታይም፣ኢትዮጵያ በአንድ ደረጃ ወደኋላ ተመልሳለች።

"የኢትዮጵያ የዘንድሮው አጠቃላይ ደረጃ፣ከዜሮ እስከ አንድ ባለው መለኪያ 0.39 ነው።ዜሮ ደካማ አንድ ደግሞ ጠንካራ የሕግ የበላይነት ማለት ነው።ከ140 ሃገሮች ደግሞ 123ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።ኢትዮጵያ ከሠሃራ በታች ካሉ 34 ሃገራት 27ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።"

በኢትዮጵያ ለሕግ የበላይነት መዳከም፣ዋነኛ መለኪያ የሆኑት፣የስርዓትና ደህንነት ደረጃዎች እያሽቆለቆሉ መሄዳቸው ነው ይላሉ ተባባሪ ዳይሬክተሯ። "በስርዓትና ደህንነት መለኪያ ሲታይ፣በኢትዮጵያ በጉልዕ መልኩ አሽቆልቁሏል።"

 የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ የሚከታተሉት አቶ አሳምን መኮንን፣በዲሲና ፊላዴልፊያ አካባቢ የሕግ አማካሪና ጠበቃ ሲሆኑ፣ኢትዮጵያ የተሻለ ደረጃ እንዲኖራት ፣የፍትህ አካላት በአዋጅ የተሰጣቸውን ግዴታ በአግባቡ መወጣት አለባቸው ይላሉ።

የዓለም ፍትሕ ፕሮጀክት ተባባሪ ዳይሬክተር አሊሺያ ኢቫንጀሊደስምስል፦ Privat

"የፍትሕ አካላት በአዋጅ የተሰጣቸውን ግዴታ መወጣት፣የአቃቤ ሕግ መስሪያ ቤት፣የፖሊስ መስሪያ ቤቶች፣ ፍርድ ቤቶች እና ሌሎች ሕግ አስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች በሙሉ የሃገሪቱን ሕዝብ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ለማክበር ከዚህ በፊት ከሚሰሩት በተጨማሪ ጠንክረው ሊወጡ ይገባል። በርግጥ በፍትሕ ስርዓቱ ላይ ሪፎርም ተካሄዶ ነበር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከመጣ በኇላ፤ነገር ግን በጦርነቱ የደበዘዘ ይመስለኛል።ስለዚህ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ለማክበር፣እነዚህ መስሪያ ቤቶች ከዚህ በፊት ጠንከር ባለ መልኩ ስራቸውን መስራት ይገባቸዋል የሚል ዐሳብ ነው ያለኝ።" በሙስና ላይ መንግስት ጦርነት ሊያውጅ እንደሚገባውም የሕግ ባለሙያው አመልክተዋል።

"ከኢንዴክሱ ውስጥ፣አሁን ካለው ዋና መስፈርት ውስጥ ሙስናን የሚከላከል መንግስት አለ ወይ? የሚል ነው።እንደምናየው ከሆነ በየቦታው ሃገራችን ውስጥ ሙስና እየንሰራፋ ነው ያለው።በሙስና ላይ መንግስት ጦርነት ሊያውጅ ይገባል የሚል ዐሳብ ነው ያለኝ።ሌላው ሰላምና ደህንነትን የሚጠብቅ ጠንካራ መንግስት ያስፈልገናል።ጠንካራ የሆነ ፌደራል መንግስት የግድ ያስፈልገናል። በተለይ ሚሊተሪው በፖሊስ ላይ በኢሚግሬሽን ላይ ያሉ መስሪያ ቤቶች በደንብ ገንዘብ ተመድቦላቸው ጥሩ ሰራተኛ ይዘው መቀጠል አለባቸው።በተጨማሪም በተለይ ፍርድ ቤቶች የፍትሐ ብሔር ስርዓቱን የፍትሐ ብሔር ክርክሩን በሚገባ ቅድሚያ በመስጠት የማስፈጸም አቅማቸውን ከፍ አድርገው መሄድ አለባቸው የሚል ዐሳብ ነው ያለኝ።"

ከአፍሪቃ አህጉር በሕግ የበላይነት ከፍተኛ አፈጻጸም ያስመዘገበችው ሩዋንዳ፣በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ140 ሃገሮች 42ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘንድሮ ከፍተኛ ነጥብ ያስመዘገበችው ዴንማርክ ስትሆን፣ኖርዌይ ፊንላንድ እና ኔዘርላንድስ ይከተላሉ።

ታሪኩ ደሳለኝ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW