1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ኢትዮጵያ፤ በነዳጅ ምርቶች ላይ የሚደረገው ጉልህ የዋጋ ጭማሪ ቀጥሏል

ሰለሞን ሙጬ
ሰኞ፣ መጋቢት 15 2017

መንግሥት ከትናንት ምሽት፤ መጋቢት 14 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ላይ ጉልህ የሚባል የመሸጫ ዋጋ ጭማሪ አድርጓል። ይህ አዲስ የነዳጅ መሸጫ ዋጋ በዛሬው ዕለት ማደያዎች ላይ ተፈፃሚ መኾኑን ተዘዋውረን ባደረግነው ቅኝት አረጋግጠናል፤ ምርቱን ለመሸመትም ረጃጅም ሰልፎች መኖራቸውን ተመልክተናል።

ኢትዮጵያ፤ በነዳጅ ምርቶች ላይ የሚደረገው ጉልህ የዋጋ ጭማሪ ቀጥሏል
ኢትዮጵያ፤ በነዳጅ ምርቶች ላይ የሚደረገው ጉልህ የዋጋ ጭማሪ ቀጥሏልምስል፦ Solomon Muchie/DW

በነዳጅ ምርቶች ላይ የሚደረገው ጉልህ የዋጋ ጭማሪ ቀጥሏል

This browser does not support the audio element.

የነዳጅ ምርቶች ላይ የሚደረገው ጉልህ የዋጋ ጭማሪ ቀጥሏል

መንግሥት ከትናንት ምሽት፤ መጋቢት 14 ቀን 2017 ዓ.ም  ጀምሮ በነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ላይ ጉልህ የሚባል የመሸጫ ዋጋ ጭማሪ አድርጓል። ይህ አዲስ የነዳጅ መሸጫ ዋጋ በዛሬው ዕለት ማደያዎች ላይ ተፈፃሚ መኾኑን ተዘዋውረን ባደረግነው ቅኝት አረጋግጠናል፤ ምርቱን ለመሸመትም ረጃጅም ሰልፎች መኖራቸውን ተመልክተናል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሐሙስ ዕለት በፓርላማ በሰጡት ማብራሪያ መንግሥታቸው ቤንዚንን ጨምሮ በሌሎች የነዳጅ ምርቶች ላይ እስከ 28 ብር ድጎማ እንደሚያደርግ ገልፀው ነበር። ያነጋገርናቸው የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ይህ "የድጎማ ማንሳት" 'ርምጃ መንግሥት ከዓለም አቀፍ አበዳሪ ተቋማት ጋር የገባው ውል ውጤት መሆኑን ጠቅሰዋል።

በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ ፊርማ የተጻፈው እና በማኅበራዊ መገናኛ ዐውታሮች እየተዘዋወረ ያለው ደብዳቤ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪው "የዓለም የነዳጅ ዋጋን መነሻ በማድረግ" ስለመደረጉ ይጠቅሳል። ከመጋቢት 14 ቀን 2017 ዓ.ም ማለትም ከትናንት ምሽት "12 ሰዓት ጀምሮ በአዲስ አበባ በሥራ ላይ የሚቆይ" የተባለው ይህ የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ፤ "ማስተካከያ" ተብሎ የተገለፀ ቢሆንም፣ ቤንዚን ላይ በሊትር ከ11 ብር በላይ ጭማሪ ተደርጎበት 112.67 እንዲሸጥ ያደረገ ነው።

በተመሳሳይ ኬሮሲን እና ነጭ ናፍጣ በ107.93 ብር እንዲሸጡ እና ጉልህ የዋጋ ጭማሪ እንዲደረግባቸው ያደረገ ነው። ይህንን ጭማሪ ማድረግ ስላስፈለገበት ዋነኛ ምክንያት ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። የነዳጅ ምርቶቹ በተባለው ዋጋ በየማደያው እየተሸጡ ስለመሆኑ ግን ዛሬ ተዘዋውረን ባደረግነው ምልከታ አረጋግጠናል። እንዲያውም የዋጋ ጭማሪው ተደርጎም ረጃጅም ሰልፎች መለያየቸው የሆኑ የነዳጅ ማደያዎች ዛሬም በዚያ ኹኔታ ውስጥ መሆናቸውን ታዝበናል።የነዳጅ ምርቶች ዋጋ መናር

ነዳጅ ከተማው ላይ በዚህ ዋጋ ቢሸጥም በየ ክፍለ ሀገሩ ግን  በጥቁር ገበያ ከመሸጫ ዋጋው በእጥፍ እንደሚሸጥ እና በምርቶቹ እጥረት ምክንያት ሥራ የሚስተጓጎልባቸው ሰዎች ስለመበራከታቸው ከዚህ በፊት ባጠናቀርናቸው ዘገባዎች ለመገንዘብ ችለናል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሐሙስ ዕለት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ፤ መንግሥታቸው ቤንዚንን ጨምሮ በሌሎች የነዳጅ ምርቶች ላይ እስከ 28 ብር ድጎማ እንደሚያደርግ ገልፀው ነበር። በዓለም ገበያ ቤንዚን ኢትዮጵያ በሊትር 129 ብር ትከፍላለች። ኢትዮጵያ ውስጥ ግን 101 ብር እንሸጣለን። 28 ብር በሊትር ድጎማ አለ።"

ኢትዮጵያ፤ በነዳጅ ምርቶች ላይ የሚደረገው ጉልህ የዋጋ ጭማሪ ቀጥሏልምስል፦ Solomon Muchie/DW

ኢትዮጵያ ሀገር በቀል የተባለ የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ መርሐ ግብር መጀመሯን ተከትሎ፣ ለዚሁ መሳካትም ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF) የገንዘብ ብድር ማግኘቷን ተከትሎ የብርን ከዶላር አንፃር ያለውን የመግዛት አቅም ከማዳከም እስከ የነዳጅ እና ለሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶች ይደረግ የነበረ ድጎማን ወደማንሳት ገብታለች።የነዳጅ ዘይት እጥረትና የዋጋ ንረት በአማራ ክልል

በቅርቡ እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ የነበሩት የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF) የበላይ ኃላፊ ክሪስታሊና ጆርጅየቫ ኢትዮጵያውያን የሀገር በቀል የምጣኔ ሀብት ማሻሻያውን ውጤት "በትዕግስት እንዲጠብቁ" ምክር ቢጤ ለግሰዋል። ይህንን በሚመለከት አስተያየታቸውን ጠይቀናቸው የነበረው የገንዘብ ባለሙያው አቶ ኢድሪስ ሰዒድ ይህንን ብለው ነበር።  

"በሚቀጥሉት አራት ዓመታት ብዙዎቹ ድጎማዎች እንደሚነሱ ተመላክቷል።"

ስማቸውንም ድምጻቸውንም ትተን ሀሳባቸውን ብቻ እንድንጠቅስ የጠየቁ ሌላኛው የምጣኔ ሀብት እና የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያ፣ አበዳሪው አይ.ኤም.ኤፍ የኢትዮጵያን መንግሥት "ድጎማ አንሳ" ነው እያለ የሚገኘው ብለዋል። የመንግሥትን ገቢ ማሳደግ በአበዳሪው ዕይታ ግዴታ ነው ያሉት ባለሙያው ይህ የሚሆነው ደግሞ የአበዳርዎችን ብድር ለመመለስ ቁልፍ ጉዳይ በመሆኑ ነው ብለዋል።

መንግሥት ከአበዳሪ ተቋማት ጋር ውል እና ይህን መሳይ የሥራ ትምምን ውስጥ ከገባ በኋላ "ድጎማን አላነሳም ማለት" ይቸግረዋል ሲሉ ክርክር መኖር ካለበትም ይህ 'ርምጃ ከመወሰዱ በፊት እንጂ አሁን ላይ እንዲህ ነው እንዲያ ነው ማለቱ ለውጥ የለውም -ጉንጭ አልፋ ነው ሲሉም ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ፤ በነዳጅ ምርቶች ላይ የሚደረገው ጉልህ የዋጋ ጭማሪ ቀጥሏልምስል፦ Solomon Muchie/DW

ያም ሆኖ ግን ነዳጅ የሚደጎመው "የኑሮ ጫናን ለመቀነስ" መሆኑን በመጥቀስ፣ ይህ "መቀጠል ነበረበት" ብለዋል። ሆኖም መንግሥት ወስኖ ገብቶበታልና የነዳጅን ብቻ ሳይሆን "ለመብራት፣ ለውኃ" የሚደረጉ ድጎማዎችም ቀስ በቀስ "መነሳታቸው ይቀጥላል" ብለዋል። "መንግሥት ከምን አንፃር ነው ይህንን እያነሳ ያለው? የሚለው በራሱ የሚያጠያይቅ ነው" ያሉት ባለሙያው፣ ይህ ግን "ሄዶ ሄዶ ችግር መፍጠሩ አይቀርም" ሲሉም ሀሳባቸውን አጋርተውናል። የነዳጅ ዋጋ ንረትና ሥዉር ገበያ በአሽከርካሪዎች ላይ ያደረሰዉ ችግር

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለፓርላማው እንዳሉት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ መለያ አሠራር ባለመኖሩ ኤምባሲዎች፣ ባለሀብቶች፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙ ስደተኞች እርዳታ የሚያጓጉዙ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቋማት ሳይቀር የነዳጅ ተደጓሚ እንደሆኑና በሀገሪቱ ያለው የነዳጅ ዋጋ በአካባቢው ካሉ ሀገራት አንጻር ሲታይ ከፍተኛ ልዩነት ያለው መሆኑን አብራርተዋል። 

"ከ25 ብር በላይ እየደጎመች [ኢትዮጵያ] የምታሠራበት ዋናው ምክንያት አብዛኛው እጅ አጠር ሰዎች በዚህ ሂደት ጉዳት ስለሚደርስባቸው ያን ለመቀነስ ነው።" በኢትዮጵያ የነዳጅ ግብይት መሠረት መስከረም 28 ቀን 2017 ዓ.ም ተደርጎ በነበረው የነዳጅ የመሸጫ ዋጋ ተመን አንድ ሊትር ቤንዚን በ 91.14 ይሸጥ የነበረ ሲሆን፤ ዛሬ ላይ ስናየው በስድስት ወራት ውስጥ በአንድ ሊትር ቢንዚን የመሸጫ ዋጋ ላይ የ21 ብር ጭማሪ ተደርጓል።

 

ሰለሞን ሙጬ

አዜብ ታደሰ

ፀሐይ ጫኔ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW