ኢትዮጵያ በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ለመነገድ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደረሰች
ረቡዕ፣ ሐምሌ 5 2015ኢትዮጵያ ከሁለት ዓመታት ገደማ በፊት ሥራ ላይ በዋለው የአፍሪካ አኅጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠና ለመነገድ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሳለች። አገሪቱ በቀጠናው የምትነግዳቸው ሸቀጦች እና አገልግሎቶች ተለይተው ዝርዝሩ በመንግሥት መጽደቁን የተናገሩት የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ካሳሁን ጎፌ "ኬንያ ናይሮቢ በሚካሔደው የአፍሪካ ንግድ ሚኒስትሮች መድረክ ላይ ኢትዮጵያ ሥራ ለመጀመር የሚያስችላትን ዝግጅት ማጠናቀቋን ታበስራለች" ሲሉ ባለፈው ሰኔ 23 ቀን 2015 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለንግድ እና ቱሪዝም ቋሚ ኮሚቴ አባላት አስረድተዋል።
አቶ ካሳሁን የጠቀሱት የናይሮቢው ስብሰባ 54 የአፍሪካ የንግድ ሚኒስትሮች የሚሳተፉበት በአፍሪካ አኅጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠና አተገባበር ላይ የሚያተኩር ነው። በዚህ ስብሰባ ኢትዮጵያ በቀጠናው የምትነግዳቸውን "ከስድስት ሺሕ በላይ" ሸቀጦች እና አገልግሎቶች ዝርዝር እንዲሁም የምትከተለውን የቀረጥ ሥርዓት ሥምምነቱን ለፈረሙ አገራት ታቀርባለች። "ከስድስት ሺሕ በላይ የዕቃዎች ምርት የስሪት ሀገር ልየታ" መከናወኑን ያስረዱት ሚኒስትር ድኤታው "የትኛው ምርት ነጻ ይሁን? የትኛውን ምርት ለተወሰነ ጊዜ እንያዝ? የትኛው ምርት እስከ ዝንተ ዓለም አንከፍተውም የሚለው ጉዳይ ሰፊ ክርክር ተደርጎበት" መጽደቁን ገልጸዋል።
ይኸ ሒደት የንግድ ቀጠናውን የሚመሠርተውን ሥምምነት በመጋቢት 2011 በሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት በማጽደቅ የተገለጠው የኢትዮጵያ "ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት" ወደ ተግባር የሚያሸጋግር ነው። የአፍሪካ አኅጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠና ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ለ1.3 ቢሊዮን ሸማቾች ወጥ የገበያ ሥርዓት ለመፍጠር የተበጀ ነው። ከኤርትራ በቀር 54 የአፍሪካ አገራት ሥምምነቱን ፈርመዋል።
ሥምምነቱን ካጸደቁ 47 ገደማ አገራት መካከል 39 የሚሆኑት በቀጠናው የሚነግዷቸውን ሸቀጦች እና አገልግሎቶች አቅርበው ተቀባይነት እንዳገኘላቸው የንግድ ፖሊሲ አማካሪው አቶ ብሩህ ገመዳ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። አቶ ብሩህ እንደሚሉት የኢትዮጵያ ቀጣዩ እርምጃ በአፍሪካ አኅጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠና ለመነገድ ከተዘጋጁ ሌሎች አገሮች ጋር የሚደረግ ድርድር ይሆናል። ከሌሎች አገሮች ጋር የሚደረገው ድርድር ሸቀጦች ወደ ኢትዮጵያ ገበያ ሲገቡ የሚከፈልባቸው ቀረጥ ላይ ያተኮረ ነው።
አቶ ብሩህ ለአፍሪካ አኅጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠና ፈራሚዎች የሚከፈቱ የአገልግሎት ዘርፎች ላይ ጭምር ድርድር እንደሚደረግም አስረድተዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት "ይኸን ይኸ እከፍታለሁ፤ ይኸን ደግሞ ለጊዜው ላቆይ እችላለሁ ወይም ቅድመ ሁኔታ ላስቀምጥ እችላለሁ" ብሎ ከሥምምነቱ ፈራሚዎች ይደራደራል። በቴሌኮም እና ፋይናንስ ዘርፎች ተግባራዊ የተደረጉ ማሻሻያዎች ነጻ የንግድ ቀጠናውን ሥራ ለማስጀመር አዎንታዊ እርምጃ እንደሆኑ የሚያስታውሱት አቶ ብሩህ "በእርግጥ ሥምምነቱን ፈርመው ካጸደቁ አገራት አንጻር ትንሽ ዘግይተናል። በርካታ አገራት በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ሥምምነት ውስጥ ንግድ እየጀመሩ ነው" ሲሉ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ሸቀጦች በንግድ ቀጠናው አማካኝነት በሌሎች ገበያዎች ሲሸጡ አሊያም የሌሎች የሥምምነቱ ፈራሚ አገራት ምርቶች ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ የሚከፈልባቸው ቀረጥ ላይ ዝርዝር ድርድር ማድረግ ያሻል። ኢትዮጵያ ለድርድር በምታቀርበው የሸቀጦች እና አገልግሎቶች የቀረጥ ሥርዓት ላይ "ጥያቄ የሚያነሱ አገራት ወደ ኢትዮጵያ ምርቶቻችንን እንልካለን ብለው የሚያስቡ አገራት ናቸው። በኢትዮጵያ ገበያ ላይ ፍላጎት የሌላቸው አገራት ጥያቄ አያነሱም" ሲሉ የንግድ ፖሊሲ አማካሪው አቶ ብሩህ ገመዳ ወደፊት ሊደረግ ስለሚችለው ድርድር ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።
"ድርድሩ ውስብስብ ነው" የሚሉት አቶ ብሩህ በተለያዩ ዘርፎች የተከፋፈሉ ስድስት ሺህ ሸቀጦች እና አገልግሎቶች ታሪፍ ላይ የሚደረግ እንደሆነ ገልጸዋል። "በመርኅ ደረጃ ውስብስብ ቢሆንም ያን ያክል ጊዜ ላይወስድ ይችላል። እስካሁን ያለውን ስንመለከት ጥያቄ ሲነሳ የነበረው ቴክኒካል ጉዳዮች ላይ ነው። ከዚያ አንጻር ብዙ ተግዳሮት ይገጥመዋል ብዬ አልጠብቅም" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት የአፍሪካ አኅጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠና ሥምምነትን በፍጥነት ፈርሞ ቢያጸድቅም በተግባር ወደ ግብይት ለመግባት ግን ከፍተኛ "ጥንቃቄ" ማድረግን መርጧል። ሒደቱ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጽህፈት ቤት፣ ብሔራዊ ባንክ፣ ገንዘብ ሚኒስቴር እና የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር ጭምር የተሳተፉበት ነው።
ኢትዮጵያ በንግድ ቀጠናው ሥምምነት መሠረት ከውጭ በሚገቡ ዕቃዎች ላይ የጣለችውን ታሪፍ ስታነሳ በመንግሥት ገቢ ላይ ሊፈጠር የሚችል ጫና አንዱ የመንግሥታቸው ሥጋት እንደሆነ የንግድ እና ቀጣናዊ ትሥሥር ሚኒስትሩ አቶ አቶ ገብረመስቀል ጫላ ከስድስት ወራት ገደማ በፊት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተናግረው ነበር። የንግድ ቀጠናው ወደ ኢትዮጵያ ከሚገቡ ምርቶች እና አገልግሎቶች 90 በመቶው የሚከፈልባቸውን ታሪፍ ዜሮ እንደሚያደርግ ለምክር ቤቱ አባላት ያስታወሱት አቶ ገብረመስቀል "ስለዚህ ከታሪፍ የምናገኘው ገቢ ዜሮ ይሆናል ማለት ነው። ኤክሳይዝ ታክስ በዚያ ደረጃ ዜሮ ይሆናል። ስለዚህ ገቢ ላይ ጫና አለው" ሲሉ የመንግሥታቸውን ሥጋት ገልጸው ነበር።
የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት ከታሪፍ ከፍተኛ ገቢ እንደሚያገኝ የሚስማሙት አቶ ብሩህ "በእርግጥም ታሪፍ ሲነሳ የመንግሥት ገቢ ይቀንሳል። መስሪያ ቤቱ ያነሳው ሥጋት ትክክል ነው ጊዜም የወሰደው ለዚያም ይመስለኛል" ሲሉ ለንግድ ቀጠናው ተግባራዊነት መዘግየት አስተዋጽዖ ሊኖረው እንደሚችል ጠቁመዋል። ይሁንና በአፍሪካ አገራት መካከል ያለው የርስ በርስ የንግድ ልውውጥ አነስተኛ በመሆኑ ሥጋቱ ብርቱ ላይሆን ይችላል። "ኢትዮጵያ ከታሪፍ የምታገኘው ገቢ ከፍተኛ ቢሆንም ያ ታሪፍ ግን የግድ ከአፍሪካ ከሚመጡ ዕቃዎች የሚገኝ አይደለም። አብዛኛው ከቻይና፣ ሌሎች የእስያ አገሮች ፣ ከአውሮፓ እና ከአሜሪካ ከሚገቡ ምርቶች ላይ የሚጣለው ታሪፍ ነው አብዛኛውን መጠን የሚይዘው" ሲሉ አቶ ብሩህ ይገልጻሉ።
የአፍሪካ አኅጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠና ለፈራሚዎቹ ይዞት የሚመጣው አዎንታዊ ዕድል በራሱ ግን በረዥም ጊዜ የኢትዮጵያ መንግሥት በገቢ ዕቃዎች ላይ ከሚጣል ቀረጥ በሚሰበስበው ገቢ ላይ ተጽዕኖ ሊኖረው ይችላል። ከአፍሪካ ውጪ የሚገኙ ኩባንያዎች "የአፍሪካ አኅጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠናን ከፈረሙ 54 አገራት ወይም ካጸደቁ 47 አገራት ውስጥ በአንደኛው ማምረት ጀምረው ከዚያ ወደ ሌሎች የአፍሪካ አገራት ታሪፍ ሳይከፍሉ ምርቶቻቸውን መላክ" ይችላሉ። ይኸ ኩባንያዎቹ ለሚመርጧቸው አገራት ቀጥተኛ የውጭ መዋዕለ-ንዋይ (FDI) በሌላ በኩል ምርቶቹ በንግድ ቀጠናው አማካኝነት ያለ ቀረጥ ለሚሸጥባቸው ገቢ ያሳጣል። "ይኸ የሚወሰነው በrules of origin ድርድር ነው። ከ80 በመቶ በላይ ተጠናቋል። የተወሰኑ ምርቶች ላይ ነው ከሥምምነት ያልተደረሰው" ሲሉ አቶ ብሩህ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ዘንድ ያለው ሌላ ሥጋት ተዘግቶ የቆየው ኤኮኖሚ ሲከፈት ከሌሎች አገሮች የሚገጥመውን ውድድር የመቋቋም አቅሙ ላይ የሚነሳ ነው። የንግድ እና ቀጣናዊ ትሥሥር ሚኒስትሩ እንዳሉት የኢትዮጵያ ገበያ በአኅጉራዊው የንግድ ቀጠና እንዲከፈት ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ግብጽ እና ኬንያ "ከፍተኛ" ፍላጎት አላቸው። የቴሌኮም እና የባንክ ዘርፎች ለውጭ ኩባንያዎች ውድድር ቢከፈቱም በአመዛኙ አጠቃላዩ ኤኮኖሚ ለውድድር ተዘግቶ ቆይቷል።
ኢትዮጵያም ከአኅጉራዊም ሆነ ዓለም አቀፋዊ ነጻ የንግድ ቀጠናዎች ርቃ ቆይታለች። አገሪቱ የዓለም የንግድ ድርጅትን ለመቀላቀል የምታደርገው ድርድር 20 ዓመታት ቢያስቆጥርም እስካሁን አልተጠናቀቀም። አገሪቱ ከአብዛኛዎቹ የንግድ ቀጠናዎች የራቀችው የግሉ ዘርፍ የመወዳደሪያ አቅም እስኪያፈረጥም በሚል አመክንዮ ነበር። በኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ዘንድ ለረዥም ዓመታት የዘለቀው ሥጋት "ተጨባጭ" እንደሆነ የሚስማሙት አቶ ብሩህ "የሚያመጣቸው ጉዳቶች አሉ። ነገር ግን ያሉትን ዕድሎች ማየት አለብን ብዬ አስባለሁ" ሲሉ ይሞግታሉ። ለዚህም አቶ ብሩህ እንደሚሉት የግሉ ዘርፍ በመንግሥት ድጋፍ በአፍሪካ አኅጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠና ተወዳዳሪ የሚሆንበትን "መስክ አጥንቶ በመስራት እና አሸናፊ ሆኖ መገኘት" ይርበታል።
እሸቴ በቀለ
ነጋሽ መሐመድ