ኢትዮጵያ በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተያየት ላይ ከአሜሪካ አምባሳደር ማብራሪያ ጠየቀች
ቅዳሜ፣ ጥቅምት 14 2013
ማስታወቂያ
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ምኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው በአዲስ አበባ የሚገኙትን የአሜሪካ አምባሳደር ጠርተው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሰጡት አስተያየት ላይ ማብራሪያ ጠየቁ።
ውጭ ጉዳይ ምኒስትሩ "የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአባይን ውሃ ፍሰት እንደማያቆም እየታወቀ ፕሬዝዳንቱ የሰጡት መግለጫ ሰዎችን ወደ ተሳሳተ ድምዳሜ የሚመራ እና በድርድር ሂደቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳደር በመሆኑ" ማብራሪያ እንደጠየቁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
ግብጽ የኅዳሴ ግድብ እንደምታፈርስ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ተናገሩ
በዚሁ ወቅት ገዱ "ታላቋን አሜሪካንን እየመራ ካለ እና ኃላፊነት ከሚሰማው ፕሬዝዳንት የማይጠበቅ በኢትዮጵያ እና በግብፅ መካከል ጦርነት ቀስቃሽ እንዲሁም በኢትዮጵያ እና በአሜሪካ መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ አጋርነት እና ስትራቴጂካዊ ግንኙነት የሚያንፀባርቅ አይደለም" ሲሉ የትራምፕን አስተያየት ተችተዋል።
ውጭ ጉዳይ ምኒስትሩ "ኢትዮጵያ በሉዓላዊነቷ ላይ በሚሰነዘሩ በየትኛውም አገር ዛቻዎች እንደማትንበረከክ እና ወደፊትም መሰል ንግግሮች ተቀባይነት እንደሌላቸው" ለአምባሳደር ማይክ ራይነር መናገራቸውን ኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
እሸቴ በቀለ
ልደት አበበ