1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ ብሪክስን ብትቀላቀል ምን ጥቅም ታገኛለች?

ረቡዕ፣ ሰኔ 28 2015

ኢትዮጵያ ብሪክስን ብትቀላቀል ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪቃ ያቋቋሙት ባንክ "አዲስ የብድር ምንጭ" ሊሆናት እንደሚችል አቶ አሌክሳንደር ደምሴ ያምናሉ። አቶ ያሬድ ሐይለመስቀል ግን "ከእነሱ ተርፎ የሚዘንብልን ነገር አይኖርም" ሲሉ ይሞግታሉ። ናይጄሪያ፣ ግብጽ እና ሳዑዲ አረቢያን ጨምሮ በርካታ አገራት ወደ ብሪክስ አዘንብለዋል

የኒው ዴቬሎፕመንት ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት በምሥራቅ ሻንጋይ
ዋና መሥሪያ ቤቱ በምሥራቅ ሻንጋይ የሚገኘው ኒው ዴቬሎፕመንት ባንክ በብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪቃ በ50 ቢሊዮን ዶላር መነሻ ካፒታል ዓለም ባንክን ለመገዳደር የተቋቋመ ነው። የቀድሞዋ የብራዚል ፕሬዝደንት የሚመሩት ባንክ ባለፉት ሁለት ዓመታት አዳዲስ ባለድርሻዎች ተቀብሏል። ምስል Fang Zhe/Xinhua/IMAGO

ኢትዮጵያ ብሪክስን ብትቀላቀል ምን ጥቅም ታገኛለች?

This browser does not support the audio element.

በመጪው ነሐሴ አጋማሽ በደቡብ አፍሪቃ የሚካሔደው የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ እንደ አሜሪካ ያሉ ልዕለ-ኃያላን እና እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች በተለያየ ምክንያት በአይነ-ቁራኛ የሚከታተሉት ነው። ምዕራባውያኑ በሩሲያ የዩክሬን ወረራ የጦር ወንጀል ፈጽመዋል የሚል ክስ የቀረበባቸውን ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን የዓለም አቀፉ የጦር ወንጀሎች መዳኛ ፍርድ ቤት (ICC) አባል የሆነችው እና የጉባኤው አዘጋጅ ደቡብ አፍሪቃ በቁጥጥር ሥር እንድታውል ይሻሉ።

የብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪቃ መሪዎች በአንጻሩ ብሪክስን ለመቀላቀል ጥያቄ ያቀረቡ አገራትን ጉዳይ እንዴት ማስተናገድ እንዳለባቸው መወሰን ይኖርባቸዋል። ከእነዚህ አገራት አንዷ 120 ሚሊዮን ገደማ ሕዝብ ያላት እና የአፍሪቃ ኅብረት መቀመጫ የሆነችው ኢትዮጵያ ነች።

የኢትዮጵያ መንግሥት ብሪክስን በአባልነት ለመቀላቀል በይፋ ጥያቄ እንዳቀረበ ያረጋገጠው ባለፈው ሣምንት ነበር። ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን "ለማስከበር" ብሪክስን ለመቀላቀል ጥያቄ ማቅረቧን ያረጋገጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር  መለስ ዓለም ሰኔ 22 ቀን 2015 በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ  "ጥያቄያችን በጎ ምላሽ ያገኛል ብለን እናስባለን" ሲሉ ተናግረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም "ብሔራዊ ጥቅማችንን ለማረጋገጥ ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋሞች አባል እንድንሆን እንሰራለን። ከእነዚህ አንደኛው ብሪክስ ነው። ጥያቄ ቀርቧል። ጥያቄያችን በጎ ምላሽ ያገኛል ብለን እናስባለን" ሲሉ ተናግረዋል። ምስል Solomon Muchie/DW

ኢትዮጵያ የአምስቱን አገራት ስብስብ ለመቀላቀል ያቀረበችው ጥያቄ የቻይና አፍሪካ አማካሪ ተቋም መሥራች እና ዳይሬክተር ለሆኑት አቶ አሌክሳንደር ደምሴ የሚገርም አይደለም። "ኢትዮጵያ ወደ ብሪክስ መጠጋቷ የአፍሪካን የኃይል አሰላለፍ ወደ ብሪክስ ያመጣ ነው" የሚሉት አቶ አሌክሳንደር የብሪክስ አባል አገራት በዓለም የኃይል አሰላለፍ እንዲመጣ የሚሹትን ለውጥ ለማሳካት በአፍሪቃ ከፍ ያለ ሚና ሊኖራቸው ከሚችሉ አገራት አንዷ ኢትዮጵያ እንደሆነች ያምናሉ።

አቶ አሌክሳንደር "ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በብሪቶን ውድስ ሥምምነት የተመሠረቱት ተቋማት ላይ መሠረት ያደረገው ሥርዓት አሁን በብሪክስ በተመሠረተው ሥርዓት እየተለወጠ ነው። ነገር ግን ቀስ እያለ ነው የሚለወጠው። ቀስ እያሉ ደግሞ ወሳኝ የሚባሉ እንደ ኢትዮጵያ አይነት አገሮች ወደዛ እየተጠጉ ነው" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ለምን ፊቷን ወደ ብሪክስ አዞረች?

ኢትዮጵያ ፊቷን ወደ ብሪክስ ያዞረችው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የሚያቀርቧቸውን የኤኮኖሚ ማሻሻያ ምክረ ሐሳቦች ተግባራዊ እያደረገ በሚገኝበት ወቅት ነው። የዐቢይ መንግሥት የአገር በቀል የኤኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብሩን የመጀመሪያ ምዕራፍ ተግባራዊ ሲያደርግ በተለይ መቀመጫቸውን በዋሽንግተን ካደረጉት ዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ጠቀም ያለ ፋይናንስ ቃል ተገብቶለት የነበረ ቢሆንም በጦርነቱ ምክንያት እንደታሰበው አልተሳካም።

ብሪክስ አዳዲስ አባልት ለመቀበል ፈቃደኝነቱን ቢያሳውቅም ሒደቱ ምን እንደሚመስል የሚታወቅ ነገር ባለመኖሩ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገራት ጥያቄ ምላሽ ለማግኘት ጊዜ ሊወስድ ይችላል። ምስል Wu Hong/AP Images/picture alliance

የኢትዮጵያ መንግሥት በዓለም አቀፍ ተቋማት የቀረቡትን ምክረ ሐሳቦች ተግባራዊ ቢያደርግም ብድር እና እርዳታው እንደታሰበው አለመሰጠቱን የሚናገሩት ዋይኤችኤም የተባለው የቢዝነስ እና የመዋዕለ-ንዋይ አማካሪ ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ሐይለመስቀል "የእኛ ወደ ብሪክስ መሔድ በምዕራቡ ዓለም መናደድ ይመስለኛል" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

ከአስራ አምስት ዓመታት ገደማ በፊት አምስቱ አገራት ኅብረት ሲመሰርቱ በዓለም በፍጥነት በማደግ ላይ የሚገኙ ኤኮኖሚዎች ባለቤቶች ነበሩ። በተለይ የሩሲያ፣ ደቡብ አፍሪቃ እና ብራዚል ምጣኔ ሐብታዊ ዕድገት እንደተጠበቀው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ባይደርስም የብሪክስ አባላት ግን እንደ አሜሪካ ባሉ ምዕራባውያን ለሚዘወረው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ እና የፖለቲካ ሥርዓት ተገዳዳሪ ወደ ማበጀት ያዘነበሉ ይመስላል።

ለዚህም የዓለም ባንክን ለመገዳደር ከሰባት ዓመታት ገደማ በፊት በ50 ቢሊዮን ዶላር የመነሻ ካፒታል "ኒው ዴቬሎፕመንት ባንክ"ን አቋቁመዋል። የቀድሞዋ የብራዚል ፕሬዝደንት ዲልማ ሮዜፍ የሚመሩት ባንክ ባለፉት ሁለት ዓመታት ባንግላዴሽ፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች እና ግብጽን በአባልነት ተቀብሏል። ኡሯጓይ ባንኩን ለመቀላቀል ያቀረበችው ጥያቄ በሥራ አመራር ቦርዱ ጸድቆ የመጨረሻው ደረጃ ላይ ይገኛል። ባንኩ በዋናነት በአምስቱ የብሪክስ አባል አገራት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ቢሆንም አቶ አሌክሳንደር ግን ለኢትዮጵያ "እንደ አዲስ የብድር ምንጭ መታየት ይችላል" የሚል እምነት አላቸው።

ኒው ዴቬሎፕመንት ባንክን የሚመሩት የቀድሞዋ የብራዚል ፕሬዝደንት ዲልማ ሮዜፍ ናቸው። ባንኩን ለመመሥረት ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪቃ እያንዳንዳቸው 10 ቢሊዮን ዶላር አዋጥተዋል። ባንኩ ባንግላዴሽ፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች እና ግብጽን በአባልነት ተቀብሏል። ምስል O Globo/ZUMA/picture alliance

የብሪክስ አባልነት ለኢትዮጵያ ምን ይዞ ይመጣል?

ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ከሆነች "የተለያዩ የመሠረተ-ልማት ፕሮጀክቶች በባንኩ ፋይናንስ ሊደረጉ ይችላሉ" የሚሉት አቶ አሌክሳንደር አገሪቱ "አይ.ኤም.ኤፍ እና የዓለም ባንክ ላይ ብቻ ትኩረት ማድረግ" እንደማይገባት ተናግረዋል። በደቡብ አፍሪቃው ጉባኤ ዋንኛ መነጋገሪያ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው የዶላር ጉዳይም ለኢትዮጵያ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አቶ አሌክሳንደር ይጠቅሳሉ። የብሪክስ አባል አገራት እርስ በርስ በሚያደርጉት የንግድ ልውውጥ ከዶላር ይልቅ አዲስ የመገበያያ ገንዘብ ሥራ ላይ የማዋል ፍላጎት አላቸው።  

ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ለምትሻው አንገብጋቢ ፋይናንስ ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪቃን ካቀፈው ስብስብ አማራጭ ለማግኘቷ ግን አቶ ያሬድ ጥርጣሬ አላቸው። "አሁን ባለው ሁኔታ ሕንድም ታዳጊ አገር ናት፤ ሩሲያም የነፍስ ወከፍ ገቢዋ ትንሽ ነው። ቻይናም አጠቃላይ ገቢዋ ትልቅ ይሁን እንጂ ገና ዝቅተኛ ገቢ ያላት አገር ነች። ብራዚልም እንደዚያው ነው" የሚሉት አቶ ያሬድ "ከእነሱ ተርፎ ለእኛ የሚዘንብልን ነገር አይኖርም" የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል።

አቶ ያሬድ እንደሚሉት ብሪክስም ይሁን ዓለም ባንክ የመሥራቾቻቸው "ጥቅም ማስጠበቂያ ናቸው።" የመዋዕለ-ንዋይ አማካሪው ኢትዮጵያ ጥቅሟን ማስጠበቅ የምትችለው በአፍሪቃ ውስጥ ብቻ እንደሆነ ይሞግታሉ። "የራሳችንን ተቋማት መመሥረት አለብን። ድንበር ማፍረስ አለብን፣ ጎሰኝነት ይበቃናል" የሚሉት አቶ ያሬድ ኢትዮጵያ እንደ ኬንያ፣ ሶማሊያ ካሉ የአፍሪቃ አገሮች ያላትን የንግድ እና የገንዘብ ልውውጥ ብታጠናክር የበለጠ እንደምትጠቀም ይመክራሉ።  

የብሪክስ እና ተጋባዥ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በመጋቢት ወር በደቡብ አፍሪቃ ባደረጉት ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች፣ ግብጽ፣ አልጄሪያ እና አርጀንቲና የአባልነት ጥያቄ ማቅረባቸው ተገልጿል። ምስል Russian Foreign Ministry Press Service/TASS/picture alliance

እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ በርከት ያሉ አገሮች ብሪክስን ለመቀላቀል ፍላጎት አሳይተዋል። ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች፣ ግብጽ፣ አልጄሪያ፣ አርጀንቲና፣ ሜክሲኮ እና ናይጄሪያ ብሪክንስ ለመቀላቀል በይፋ ጥያቄ ማቅረባቸውን የደቡብ አፍሪቃ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናሌዲ ፓንዶር ባለፈው መጋቢት ተናግረዋል። ኢንዶኔዥያ፣ ባንግላዴሽ እና ኢራንም ተመሳሳይ ፍላጎት አላቸው።

የኢትዮጵያም ሆነ ተመሳሳይ ጥያቄ ያቀረቡ እንደ ሳዑዲ አረቢያ ያሉ አገራት ጥያቄ እንዴት ምላሽ እንደሚያገኝ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም። "ሒደቱ ጊዜ ይፈጃል" የሚሉት አቶ አቶ አሌክሳንደር ብሪክስ አዳዲስ አባላት እየተቀበለ የሚስፋፋበት "ራሱን የቻለ መደበኛ አካሔድ" ማበጀት ጊዜ እንደሚወስድ ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ብሪክስን ለመቀላቀል ጥያቄ በማቅረቧ የውይይቱ አካል ሆናለች የሚሉት አቶ አሌክሳንደር "አዎንታዊ የሆነ መልስ እንደምታገኝ እገምታለሁ" ሲሉ ተናግረዋል።

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW