1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ኢትዮጵያ ተስፋ የጣለችበት የካፒታል ገበያ ፍሬ መቼ ይታያል?

ረቡዕ፣ ሐምሌ 9 2017

የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ በደረሰበት ምዕራፍ መንግሥት ከፍ ያለ ተስፋ ሰንቋል። ገበያው የግምጃ ቤት ሰነዶች፣ የወጋገን እና የገዳ ባንኮችን አክሲዮኖች መዝግቦ ለሁለተኛ ገበያ አቅርቧል። ባለሙያዎች “ፈጣን ግብይት” እስኪፈጠር መታገስ እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ። ነገር ግን “ቀስ በቀስ እያደገ ካልመጣ ሊሞት ይችላል” የሚል ሥጋትም አለ።

የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ እና የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝን ጨምሮ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ደወል በተደወለበት መርሐ ግብር ላይ ይታያሉ
የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ዓመታት ከፈጀ የምሥረታ ሒደት በኋላ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ እና የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝን ጨምሮ በርከት ያሉ ባለሥልጣናት በተገኙበት የመንግሥት የግምጃ ቤት ሰነድ፤ የወጋገን ባንክ እና የገዳ ባንክ አክሲዮኖችን መዝግቦ ለሁለተኛ ገበያ ማቅረቡን ሐምሌ 4 ቀን 2017 ይፋ አድርጓል። ምስል፦ Ethiopian Securities Exchange

ኢትዮጵያ ተስፋ የጣለችበት የካፒታል ገበያ ፍሬ መቼ ይታያል?

This browser does not support the audio element.

የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ዓመታት ከፈጀ የምሥረታ ሒደት በኋላ በይፋ ግብይት ሲጀምር ወጋገን ባንክ 6.2 ሚሊዮን፣ ገዳ ባንክ 1.23 ሚሊዮን አክሲዮኖቻቸውን አስመዝግበዋል። በብሔራዊ ባንክ “ትናንሽ ባንኮች” ተብለው ከተመደቡት ጎራ የሚገኙት የሁለቱ ባንኮች የአንድ አክሲዮን ዋጋ (par value) 1,000 ብር ተተምኗል።

ምዝገባው የባንኮቹን ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ወይም አክሲዮኖች መሸጥ ከሚፈልጉ ኢንቨስተሮች በሁለተኛ ደረጃ ገበያ (Secondary Market) ኢትዮጵያውያን እንዲገዙ ዕድል የሰጠ ነው። የሰነደ ሙዓለ ንዋይ መገበያያ ሒሳብ ለመክፈት ፋይዳ ተብሎ የሚጠራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ መታወቂያ እና የግብር ከፋይነት መለያ ቁጥር ማቅረብ አስፈላጊ ቅድመ-ሁኔታዎች ናቸው።

“ወጋገን ብቻ ነው አሁን አክሲዮን እየሸጠ ያለው። ገዳ ባንክም የራሱን አክሲዮን መሸጥ ይጀምራል” ሲሉ የወጋገን ካፒታል ኢንቨስትመንት ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብሩታዊት ዳዊት ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ወጋገን ኢንቨስትመንት ባንክ ገዢዎችን ከሰነደ ሙዓለ ንዋይ አውጪዎች ከሚያገናኙ የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ አባላት መካከል አንዱ ነው።

የወጋገን ባንክ አንድ አክሲዮን በ1,200 ብር እየተሸጠ እንደሚገኝ የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ “ገበያው እየተጠናከረ ሲሔድ ወደ ላይ ሊጨምር ወይም ሊቀንስ ይችላል” ሲሉ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ባንኮች በአክሲዮን ከተቋቋሙ ሌሎች ኩባንያዎች አኳያ የኮርፖሬት አስተዳደር ያላቸው እና በመደበኛነት የፋይናንስ ሪፖርት የሚያወጡ በመሆናቸው የሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ ሲመሠረት ተስፋ የተጣለባቸው ናቸው። የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ጠበቃ የሆኑት አቶ ዮሐንስ አሰፋ ከሌሎች ተቋማት አንጻር “በገበያው ሊመዘገቡ የሚችሉት” ባንኮች እንደሆኑ ይስማማሉ።

የባንኮች አክሲዮኖች እስካሁን በነበረው አሠራር የተሻለ ግብይት እንደነበራቸው የገለጹት አቶ ዮሐንስ ይሁንና በሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ተመዝግበው አክሲዮኖቻቸውን ለሁለተኛ ደረጃ ገበያ በሽያጭ ማቅረብ አሠራር እና አደረጃጀታቸውን ጨምሮ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ግልጽ እንዲሆኑ የሚያስገድድ በመሆኑ በተለይ “የመጀመሪያ ትውልድ” ውስጥ የሚካተቱት “ስድስት ባንኮች ፈቃደኛ” ላይሆኑ እንደሚችሉ ሥጋት አላቸው።

ወጋገን ባንክ 6.2 ሚሊዮን አክሲዮኖች በኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ በማስመዝገብ ለሁለተኛ ደረጃ ገበያ አቅርቧል። ምስል፦ Ethiopian Securities Exchange

ባንኮቹ በኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ቢመዘገቡ “አነስተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎችም በአቅማቸው ደረጃ መሳተፍ ይችላሉ” የሚሉት ባለሙያው ለአክሲዮን ባለቤቶች የተሻለ የግብይት ሥርዓት እንደሚፈጠርላቸው ይጠብቃሉ። ከዚህ በተጨማሪ “አክሲዮን ገበያው በደንብ መሥራት ከጀመረ፤ ብዙ መሸጥ መለወጥ ከተጀመረ የመንግሥት የታክስ ገቢም ይጨምራል” ሲሉ ጠቀሜታውን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ሥራ ሲጀምር አክሲዮኖቻቸውን ያስመዘገቡ ኩባንያዎች ቁጥር ሁለት ብቻ ቢሆንም አቶ ዮሐንስ “ለአጀማመሩ ትንሽ አይደለም። በቂ ነው” የሚል እምነት አላቸው። እንዲያም ሆኖ ግን “በተለይ ትልልቆቹ ባንኮች አለመሳተፋቸው” ለአቶ ዮሐንስ ቅሬታ ፈጥሮባቸዋል።

በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ “ፈጣን ገበያ የሚኖረው” ተጨማሪ ኩባንያዎች ተመዝግበው አክሲዮኖቻቸው ለሁለተኛ ገበያ ለሽያጭ ሲቀርቡ እንደሆነ የሚናገሩት የወጋገን ካፒታል ኢንቨስትመንት ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብሩታዊት ዳዊት  መንግሥት ኩባንያዎች እንዲመዘገቡ በሰጠው ቀነ ገደብ ላይ ተስፋ አድርገዋል። “ሁሉም የአክሲዮን ኩባንያዎች በሕጉ መሠረት መመዝገብ አለባቸው። የዚያን ጊዜ ተጨማሪ ኩባንያዎች ሲመዘገቡ የሚሸጥ እና የሚገዛ ተጨማሪ አክሲዮን ይኖራል” ሲሉ አስረድተዋል።

ወይዘሮ ብሩታዊት ዳዊት የሚመሩት ወጋገን ካፒታል በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ፈቃድ የተሰጠው የመጀመሪያ የኢንቨስትመንት ባንክ ነው። በ385 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል የተቋቋመው የኢንቨስትመንት ባንክ ከሰኔ 11 ቀን፣ 2017 ዓ.ም ጀምሮ “የሙዓለ ንዋዮችን እና የግምጃ ቤት ሰነዶችን የግብይት ትዕዛዝ ከመቀበል እስከ ባለቤትነት ማዛወር ያለውን ዑደት በተሳካ ሁኔታ የቀጥታ የሙከራ ግብይቶችን ሲያካሒድ” እንደቆየ ዐሳውቋል።

የሙከራ ጊዜው ተጠናቅቆ በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ሁለተኛ ደረጃ ግብይት መጀመሩ በይፋ የተበሰረው ባለፈው ሣምንት ሐምሌ 4 ቀን 2017 ዓ.ም ነበር። ከሁለቱ ባንኮች አክሲዮኖች በተጨማሪ በ107፣ 57 እና 149 ቀናት የሚጎመሩ የመንግሥት የግምጃ ቤት ሰነዶች በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ተመዝግበዋል። የተመዘገቡት የብድር ሰነዶች በዓመት ከ16.8 እስከ 17.4 በመቶ ወለድ የሚከፈልባቸው ናቸው።

የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ የደረሰበት ምዕራፍ “ወደፊት ለምንጠብቃቸው ብዙ ሥራዎች የመጀመሪያ ቀን እንደሚሆን አልጠራጠርም” ሲሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ጥላሁን እስማኤል ተስፋቸውን ባለፈው አርብ በአዲስ አበባ ሸራተን ሆቴል በተካሔደ መርሐ-ግብር ላይ ተናግረዋል።

ዶክተር ጥላሁን እስማኤል የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ መሥራች ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው። ምስል፦ Ethiopian Securities Exchange

የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሃና ተኸልኩ “በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ የተከናወኑ የልማት እና የሪፎርም ውጤቶች የሚታዩበት እና የፋይናንስ ዘርፍ ላይ ትልቅ አሻራን የሚያሳርፍ አዲስ ምዕራፍ” ብለውታል። “የመንግሥት ግምጃ ቤት ሰነዶች እና የድርጅት ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ለግብይት” የቀረቡበት ምዕራፍ “ኢንቨስተሮች በገበያው ላይ በንቃት መሳተፍ የሚችሉበትን ዕድል እና ሁኔታ የፈጠረ ነው” ሲሉ ፋይዳውን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ 54 ባለ ድርሻዎች ይኑሩት እንጂ መንግሥት በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በኩል ከፍ ያለውን ድርሻ ይዟል። የምሥራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ የንግድ እና የልማት ባንክ (TDB) እና አያት አክሲዮን ማኅበር ከ5 በመቶ በላይ ድርሻ ካላቸው ተቋማት መካከል ናቸው።

የሀገሪቱን ካፒታል ገበያ ከ51 ዓመታት ገደማ በኋላ መልሶ ለማቋቋም የተደረገው ጥረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የብሪታኒያው ኤፍኤስዲ አፍሪካ እና የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣንን ጨምሮ በርካታ ተቋማት የተሳተፉበት ነው።

የገበያውን ፍትኃዊነት እና ተዓማኒነት የመቆጣጠር ኃላፊነት ለኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን የተሰጠ ነው። ለገበያ ተዋናዮች ፈቃድ የሚሰጠው ባለሥልጣኑ “ጠንካራ እና ከዓለም አቀፍ ምርጥ ተሞክሮዎች ጋር የተጣጣሙ የሕግ እና የቁጥጥር ማዕቀፎችን” ሥራ ላይ እንዳዋለ የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ሃና ተኸልኩ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በጎርጎሮሳዊው 1965 ተመሥርቶ ለዘጠኝ ዓመታት የዘለቀ የአዲስ አበባ የአክሲዮን ግብይት ቡድን የተባለ የካፒታል ገበያ መሰል ተቋም ነበራት። ይሁንና በሀገሪቱ የተሟላ የካፒታል ገበያ ለመመሥረት በተደጋጋሚ የተደረጉ ጥረቶች ከሽፈዋል። በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሥር በተደራጀ ጽሕፈት ቤት የአሁኑን የካፒታል ገበያ ሥርዓት ለማበጀት በአጠቃላይ ወደ አምስት ዓመታት ገደማ ወስዷል።

ሒደቱ የካፒታል ገበያ አዋጅ አዘጋጅቶ ማጽደቅ፣ ተቆጣጣሪውን ባሥልጣን እና ገበያውን ማቋቋም እንዲሁም የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ግምጃ ቤት (CSD) መመሥረትን ጨምሮ በርካታ ሥራዎችን የጠየቀ ነው። ሒደቱን በቅርብ ሲከታተሉ የቆዩት የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ጠበቃ ዮሐንስ አሰፋ ተቋማቱን የመመሥረት ኃላፊነት የተጣለባቸው ባለሙያዎች “ገበያው የሚያስፈልገውን ለመገንባት በጥሞና እና በጥንቃቄ ለመሥራት” የተከተሉት አካሔድ ለመዘግየቱ አንድ ምክንያት ሳይሆን እንደዳልቀረ ይገራሉ።

ገበያውን እና ተቆጣጣሪውን ከመመሥረት ባሻገር አስፈላጊውን የቴክኖሎጂ መሠረተ-ልማት መዘርጋት፣ የሰው ኃይል ቀጥሮ የማሰልጠን እንዲሁም ኢንቨስተሮች እና ሊመዘገቡ የሚችሉ ኩባንያዎችን ማስተማርን የመሳሰሉ ምኅዳሩን የማበጀት ሥራዎች ጊዜ የሚወስዱ መሆናቸውን አቶ ዮሐንስ አስረድተዋል።

የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ እና የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝን ጨምሮ የመንግሥት ባለሥልጣናት የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያበረክታል የሚል ተስፋ አላቸው። ምስል፦ Ethiopian Securities Exchange

የገበያው ስኬታማነት ገና ወደፊት የሚፈተሽ ቢሆንም የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ገና ካሁኑ ከፍ ያለ ተስፋ ሰንቀዋል። የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ የደረሰበትን ምዕራፍ መንግሥታቸው ተግባራዊ እያደረገ የሚገኘውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ “የበለጠ ለማጠናከር አንድ መሠረታዊ ውጤት ያመጣ ርምጃ” እንደሆነ ተናግረዋል።

መንግሥታቸው የሚገጥመውን የበጀት ጉድለት ለመሙላት ባንኮች የግምጃ ቤት ሰነድ እንዲገዙ ያስገድድ የነበረውን አሠራር አቁሟል። በዚህም ምክንያት የ2018 በጀት ካለበት 188 ቢሊዮን ብር ጉድለት “ውስጥ 173 ቢሊዮን ብር የሚሆነው ከሀገር ውስጥ የተጣራ ብድር በመውሰድ እንዲሸፈን” መንግሥታቸው ዕቅድ አለው። “የመንግሥት ግምጃ ቤት ሰነድን ለማስመዝገብ እና ሁለተኛ ገበያ ላይ እንዲውል” የተደረገው “በዚህ ወሳኝ ጊዜ” መሆኑን የገለጹት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ መንግሥት የበጀት ጉድለት ለመሙላት የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ላይ አይኑን እንዳሳረፈ ገልጸዋል።

የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ በበኩላቸው ይህ መንግሥት የሚገጥመውን የበጀት ጉድለት ለመሙላት “ገበያ መር በሆነ እና የዋጋ ግሽበትን በማያስከትሉ ዘዴዎች” ለመበደር ዕድል የሚሰጥ እንደሆነ ተናግረዋል። የብሔራዊ ባንክ ገዥ ገበያው “የረዥም ጊዜ የፋይናንስ አቅርቦት መጠን ለመገመት እና ለመቆጣጠርም መሣሪያ ሆኖ ያገለግላል” ሲሉ አስረድተዋል።

አቶ ማሞ “ግልጽ፣ በገበያ የሚመራ፣ የዳበረ እና የተሳለጠ የካፒታል ገበያ በተለይም የመንግሥት የግምጃ ቤት ሰነዶች የሚሸጡበት ሁለተኛው ገበያ (secondary market) መኖር የብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ተመን ትርጉም ባለው መልኩ ወደ ኢኮኖሚው እንዲተላለፍ ትልቅ አስተዋጽዖ አለው” ሲሉ ተደምጠዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ በጋራ ያስጀመሩት “በባንኮች መካከል የሚደረግ የገንዘብ ገበያ በአጭር ጊዜ ከ830 ቢሊዮን ብር በላይ ማገበያየት” እንደቻለ አቶ ማሞ ተናግረዋል። የብሔራዊ ባንኩ ገዥ “ገበያው ሥር እንዲሰድድ እና የታለመለትን ዓላማ እንዲመታ” የፋይናንስ ተቋማት፣ በዘርፉ የተሠማሩ ተዋንያን እና ባለሙያዎች “ንቁ ተሳትፎ” በማድረግ “ታሪካዊ ዕድል እና ኃላፊነት” እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ይህ ማሳሰቢያ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሃና ተኸልኩ ጭምር የተጋሩት ነው። ዋና ዳይሬክተሯ የገበያው ስኬት የተቆጣጣሪ ባለሥልጣናት፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የፋይናንስ ተቋማት፣ ባለሐብቶች እና የኅብረተሰቡን “ቀጣይነት ያለው ትብብር” እንደሚሻ አስገንዘበዋል። “ተዓማኒነትን ለመገንባት፣ የፋይናንስ እውቀትን ለማጎልበት፣ ተሳትፎን ለማስፋት እና ከፍተኛውን የአስተዳደር እና የግልጽነት ደረጃዎችን ለማስከበር መተባበር” እንደሚኖርባቸው ጥሪ አስተላልፈዋል።

ከተመሠረተ ሦስት ዓመታት ገደማ ያስቆጠረው ገዳ ባንክ 1.23 ሚሊዮን አክሲዮኖች በኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ አስመዝግቧል። ምስል፦ Ethiopian Securities Exchange

አቶ ዮሐንስ አሰፋ ግን የካፒታል ገበያው “ስኬታማ የሚሆነው ሥራው ሲሠራ ነው” የሚል እምነት አላቸው። አለበለዚያ “ገበያው ቀስ በቀስ እያደገ ካልመጣ ሊሞት ይችላል” ሲሉ ያስጠነቅቃሉ። የካፒታል ገበያው ኃላፊዎች በዐሥር ዓመታት ውስጥ 90 ኩባንያዎች ተመዝግበው አክሲዮኖቻቸውን ለሽያጭ ያቀርባሉ ብለው ይጠብቃሉ። የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በሥሩ ከሚገኙ ተቋማት መካከል ኢትዮ-ቴሌኮምን ጨምሮ የተወሰኑትን ያስመዘግባል ተብሎ ይጠበቃል።

“አዳዲስ ኩባንያዎች እየጨመረ፤ ግብይት እየጨመረ ማደግ አለበት” የሚሉት አቶ ዮሐንስ “ተገትሮ ከቀረ ከሕዝቡም ከኢንቨስተሩም ፍላጎት ያጣል። ቀስ ብሎ ተዓማኒነቱንም ሊያጣ ይችላል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።  

ለኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያም ይሁን ተቋሙን ለሚመሩ ኃላፊዎች “አዎንታዊ የሆነ አስተያየት” ያላቸው አቶ ዮሐንስ “ገበያው በረዥም ጊዜ ስኬታማ ይሆናል” ብለው ይጠብቃሉ። መንግሥታዊው ኢትዮ-ቴሌኮም እንዲሁም በገበያው ከፍ ያለ ድርሻ ያላቸው አዋሽ እና አቢሲኒያን የመሳሰሉ ባንኮች ተመዝግበው አክሲዮኖቻቸው ለሁለተኛ ገበያ ቢቀርቡ “ትልቅ ግብይት እና ፍላጎት” እንደሚፈጠር አስረድተዋል።  

“ኬንያ ሲጀመር እነሱም ምንም ነገር አያውቁም ነበር። ነገር ግን ከጊዜ በኋላ እየተማሩ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያው እየተስፋፋ መጣ” የሚሉት የወጋገን ካፒታል ኢንቨስትመንት ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብሩታዊት ዳዊት “ኢትዮጵያም ውስጥ አሁን ምንም እንቅስቃሴ የለም አልልም። አለ ነገር ግን በጣም ትንሽ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

“ከትንሽ ጊዜ በኋላ ሌሎቹ ባንኮች፤ ሌሎቹ ኮርፖሬሽኖች፤ ሌሎቹ ተቋማት ሲገቡ፤  የአክሲዮን ድርሻዎቻቸውን ሲያስመዘግቡ የዚያን ጊዜ እንቅስቃሴ” እንደሚኖር የገለጹት ብሩታዊት “ያ እስኪሆን ድረስ ግን መታገስ አለብን” የሚል እምነታቸውን ለዶይቼ ቬለ አጋርተዋል።

አርታዒ ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW