1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፕሪቶሪያዉ ስምምነትና የመቀሌ ነዋሪዎች አስተያየት

ሐሙስ፣ ጥቅምት 22 2016

ጥቅምት ወር 2013 ዓመተምህረት በኢትዮጵያ መንግስት እና የትግራይ ሐይሎች መካከል የተጀመረው እና ለሁለት ዓመት የዘለቀው ደም አፋሳሽ ጦርነት፥ ወጣት ሃፍቶም በመሰሉ በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ተጋሩ ሕይወት እስከ ወድያኛው የቀየረ ነው።

ጦርነቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የትግራይ ወጣቶችን ጎድቷል
በጦርነቱ ጉዳት ከደረሰባቸዉ የትግራይ ተዋጊዎች ጥቂቱምስል Million Haileselassie/DW

የጦርነቱ መቆም ብዙዎችን አስደስቷል፣ የስምምነቱ ገቢራዊነት ግን አጠያያቂ ነዉ

This browser does not support the audio element.

የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ህወሓት) የተፈራረሙት የሰላም ስምምነት በአንድ ዓመት ዉስጥ ያስገኘዉ ጥቅም በብዙዎች ዘንድ የተለያየ ደረጃ እየተሰጠዉ ነዉ።በጦርነቱ ክፉኛ የተጎዳዉ የትግራይ ክልል ነዋሪዎች ሰላም በመስፈኑ የመደሰታቸዉን ያክል በስምምነቱ ገቢራዊነት ላይ የተለያየ አስየያየት ይሰጣሉ።በኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት እና ህወሓት መካከል ጦርነት ከመቀስቀሱ በፊት፥ የ25 ዓመቱ ወጣት ሃፍቶም ኪዳይ፣ ጠመንጃ ይሁን ውትድርና ፍፁም የማያውቅ በግል ስራ ተሰማርቶ ሕይወቱ የሚመራ ባለራዕይ ነበረ። "ጦርነቱ ሲጀመር፣ የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ሐይሎች በትግራይ ገብተው ግፍ ሲፈፅሙ፣ እኔም እንደሌላው የትግራይ ወጣት ወታደራዊ ስልጠና ወስጄ ወደ ትግል ገባሁ" የሚለው ሃፍቶም፥ በጦር ግንባር ከፍተኛ የአካል ጉዳት ደርሶበት አሁን ግማሽ ሰውነቱ መንቀሳቀስ የማይችል ሆኖ፥ መቐለ በሚገኝ የጦር ጉዳተኞች እንክብካቤ ማእከል ይኖራል። ሃፍቶም "ለሀገሬ፣ ለህዝቤ፣ ለራሴ ብዬ ነው ወደ ትግል የተቀላቀልኩት። የከፈልኩት መስዋእትነት ምንም አይቆጨኝም። የሚጠበቅብኝ ነው። አሁን ግን እኔ ጨምሮ እዚህ ያለን ሁላችን የአካል ጉዳተኛ ሆነናል። ብዙ የሚያስፈልገን ነገር አለ። ዋናው ነገር ሕክምና ማግኘት እፈልጋለሁ። ሕክምና ካገኘሁ ሌላ ተጨማሪ ነገር አልፈልግም" ይላል።


ጥቅምት ወር 2013 ዓመተምህረት በኢትዮጵያ መንግስት እና የትግራይ ሐይሎች መካከል የተጀመረው እና ለሁለት ዓመት የዘለቀው ደም አፋሳሽ ጦርነት፥ ወጣት ሃፍቶም በመሰሉ በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ተጋሩ ሕይወት እስከ ወድያኛው የቀየረ ነው። 

በዉጊያዉ ከተቃጠሉ የጦር መሳሪያና ተሽከርካሪዎች አንዱምስል Million Haileselassie/DW

የዛሬ ዓመት ጥቅምት 2015 ዓመተምህረት ደም አፋሳሹ ጦርነት ያስቆመ የሰላም ስምምነት በአፍሪካ ሕብረት መካከለኛነት በኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሓት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶርያ ከተፈረመ በኃላ፥ የጠበንጃ ድምፅ መቆሙ ብቻ ሳይሆን ትግራይ ላይ ተጥሎ የነበረ ከበባና ክልከላም በሂደት ተነስቷል። በትግራይ ለሁለት ዓመት ተቋርጦ የነበረው የስልክ፣ ኢንተርኔት፣ ትራንስፖርት፣ የንግድ እንቅስቃሴ፣ የእርዳታ አቅርቦት ዳግም የቀጠለው ከፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት በኃላ ነው። 

የትግራይ ዋና ከተማ መቐለ ከሰላም ስምምነቱ በኃላ ወደ ሕይወት ተመልሳለች። የከተማዋ ነዋሪዎችም ሰላምን እያጣጣሙ ያሉ ይመስላሉ። የመቐለ ከተማ ነዋሪዋ የሆነችው ብሌን ምትኩ

"የጠብመንጃ፣ የውግያ አውሮፕላን ወይም የድሮን ቶክስ ድምፅ አለመስማማት ትልቅ ዕረፍት ነው። ከሰላም ስምምነቱ በኃላ ትግራይ ዳግም ወደ ዓለም ተቀላቅላለች" ትላለች።

ይሁንና ከሰላም ስምምነቱ አንድ ዓመት በኃላ አሁንም የሚያስጨንቁ በርካታ ነገሮች አሉ ትላለች። "ይሁንና አሁንም በርካታ ያልተቀየሩ ነገሮች አሉ። የተፈናቀሉ ወንድም እና እህቶቻችን ከቀዬአቸው ከራቁ አራት ዓመት ሊሞላቸው ነው" ትላለች ብሌን።

ሌላው ያነጋገርነው የመቐለ ዩኒቨርስቲ መምህር ዳኒኤል ሰማንጉስ በበኩሉ "በትግራይ ዘንድ የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት አንድ ዓመት ሲዘከር የተለየ እና የተዘበራረቀ ስሜት አለዉ። የውስጥ ተፈናቃዮች ስቃይ ሁላችንም እየጎዳ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ስልክ፣ ኢንተርኔት የመሳሰሉ አገልግሎቶች ተከፍተዋል፣ ልጆች ትምህርት ቤት መዋል ጀምረዋል። የጤና፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ዳግም ጀምረዋል" ይላል።


በትግራይ የሚኖሩ በርካቶች ከአንድ ዓመት በፊት የተፈረመው የሰላም ስምምነት ሙሉበሙሉ እንዲተገበር ይጠይቃሉ። ከጦርነቱ ጅማሮ በፊት የኢትዮጵያ ሉአላዊ ግዛት ከነበረው እና አሁን በኤርትራ ጦር ቁጥጥር ስር ካለው ኢሮብ ወረዳ ተፈናቅሎ በዓዲግራት ያለው ሓጎስ ተስፋይ ከውሉም በኃላ ቢሆን በእነርሱ ዘንድ የተቀየረ ነገር የለም።

በጦርነቱ ለተሰዉ የትግራይ ተዋጊዎች መታሰቢያ ሥርዓትምስል Million Hailesilassie/DW

72 ሲቪክ ማሕበራት ያቀፈው 'የትግራይ ሲቪክ ማሕበረሰብ ሕብረት' የተባለ ነፃ ሲቪክ ተቋም ከአንድ ዓመት በፊት የተፈረመው የሰላም ስምምነት ሙሉበሙሉ አልተተገበረም ይላል። የትግራይ ሲቪክ ማሕበረሰብ ሕብረት ስራአስኪያጅ አቶ ያሬድ በርሃ "የፌደራሉ መንግስት ግዴታው እየተወጣ አይደለም" በማለት ለዶቼቬለ ገልፀዋል። አቶ ያሬድ "የፌደራሉ መንግስት የገባው ቃል ለመፈፀም እየሰራ፣ ግዴታው እየተወጣ አይደለም። ምክንያቱ ግልፅ ባይሆንም የዓለምአቀፉ ማሕበረሰብም በቂ ትኩረት እየሰጠ አይደለም። ይህ ዘላቂ ሰላምን ጥያቄ ውስጥ ልያስገባ የሚችል ነው" ብለዋል።

ከዓለምአቀፍ ለጋሾች ወደትግራይ በአጠቃላይ ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ ይቀርብ የነበረው ሰብአዊ ድጋፍ መቋረጡ ተከትሎ ደግሞ በትግራይ ያለው ሰብአዊ ሁኔታ ወደከፋ ደረጃ ደርሷል። የሰላም ስምምነቱ ተከትሎ በትግራይ የተመሰረተው ግዚያዊ አስተዳደር፥ ጦርነቱ ተከትሎ ወደ ትግራይ የገቡ የውጭ ሐይሎች ከትግራይ እንዲወጡ እንደሚጠብቅ ይገልፃል። የትግራይ ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ሐላፊ አቶ ረዳኢ ሓለፎም "ከፌደራል መንግስት እኛ የምንጠብቀው፣ ትግራይ ውስጥ ያሉ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ውጭ የሆኑ ሁሉም ታጣቂዎች እንዲያስወጣቸው ነው። በስምምነቱ መሰረት የአማራ ታጣቂዎች እና የኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ እንዲወጡ እንጠብቃለን" ይላሉ።

የትግራይ ርዕሰ መስተዳድር ፅሕፈት ቤትምስል Million Haileselassie/DW

የዛሬ ዓመት በፕሪቶርያ የተፈረመው የሰላም ስምምነት፥ ከሁሉም በላይ ደም አፋሳሹ ውግያ ቢያስቀርም፥ ተስፋ ተጥሎበት የነበረው የዜጎች ድህንነት የመጠበቅ፣ ማሕበራዊ ቀውስ መፍታት በመሳሰሉት ግን አፈፃፀሙ አሁንም ጥያቄ ይነሳበታል።

ሚሊዮን ኃይለስላሴ

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW