1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ፤ አስገድዶ መድፈር የተፈጸመባቸዉ ሴቶች ፍትህን ያገኛሉ?

ሐሙስ፣ የካቲት 28 2016

ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን፤ ስርዓታችን በዋነኝነት አባታዊ ስርዓት ነዉ። ሴቶቹም ብንሆን አባታዊ ስርዓት የፈጠረን ነን። ስለዚህ በራስ መተማመናችን፤ ለራሳችን ያለን ግምት ከወንዶቹ እኩል አይደለም። የሄድንበት ስርዓት ራሱ አንቺ አትችይም፤ እየተባለ እየተመረጠልን ነዉ ያደግነዉ። አሁንም ሴቶች ከፍርሃትና ከመሸማቀቅ አልወጣንም ብሎ መናገር ይቻላል።

 ሴታዊት የፆታ እኩልነት ተሟጋች ንቅናቄ
ሴታዊት የፆታ እኩልነት ተሟጋች ንቅናቄምስል Setaweet

በፌደራል መንግሥት፤ በህወሓትም፤ በአማራ ኃይላትም ቢሆን፤ ሴቶች በነዚህ ሁሉ እንደተደፈሩ ምልከታ አለ

This browser does not support the audio element.

«የፌደራል መንግሥትም ቢሆን፤ ህወሓትም ቢሆን፤ የአማራ ኃይላትም ቢሆኑ፤ ሴቶች በነዚህ በሁሉም እንደተደፈሩ ምልከታ አለ። እስካሁን የምናዉቃቸዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ የታጠቁ ኃይላት በሙሉ ሴቶችን ደፍረዋል ብለን መደምደም እንችላለን።» ያሉን የሴታዊት ንቅናቄ መስራች እና አስተባባሪ ናቸዉ። ኢትዮጵያ ዉስጥ በተካሄዱ እና አሁንም  በሚታዩ ግጭት እና ጦርነቶች ምክንያት፤ ሴቶች የተለያዩ ጥቃት እየተፈፀመባቸዉ ነዉ። ሴቶችን መድፈር እንደ አስገድዶ መድፈርን እንደ መደበኛ የጦርነት ስልት መወሰዱ ይቁም፤ እስካሁን ኢትዮጵያ ዉስጥ በግጭት ጦርነቶች ሳብያ ጾታዊ እና ወሲባዊ ጥቃቶች ለደረሰባቸዉ ሴቶች ፍትህ ለማስፈን አሁንም አልረፈደም፤ ስትል የምትወተዉተዉ ሴታዊት የተሰኘች የፆታ እኩልነት ተሟጋች ንቅናቄ ናት። ሴታዊት ንቅናቄ ዓላማ አድርጋ የተነሳችዉ በኢትዮጵያ ከጾታዊ ጥቃት ነጻ የሆነ ፍትሃዊ ማህበረሰብ ተፈጥሮ ማየትን ነው።

ማርች 8  ታስቦ የሚዉለዉን  ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ፤ በኢትዮጵያ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ በሴቶች መብት ላይ የሚሰሩ ድርቶች ድምጻቸዉን ከፍ አድርገዉ ለማሰማት ዝግጅታቸዉን አጠናቀዋል። የሴታዊት የጾታ እኩልነት ንቅናቄ መስራች እና አስተባባሪ ዶ/ር ስህን ተፈራ ሰሞኑን በተለያዩ ክልሎች ከሚገኙ በጾታ እኩልነት እና በሴቶች ጉዳዮች ላይ ከሚሰሩ ድርጅት ተጠሪዎች ጋር ታስቦ የሚዉለዉን ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን በማስመልከት ዉይይት አድርገዋል። ዉይይታቸዉ በአብዛኛዉ በግጭትና ጦርነት ኢትዮጵያ ዉስጥ ስለተደፈሩ እና አሁንም እየተደፈሩ ስላሉ ሴቶች ጉዳይ ነዉ።

«በዚህ ዓመት ትኩረት አድርገን እየሰራን ያለነዉ፤ በተለይ አሁን በአገሪትዋ የሚታየዉ እና በጣም እያሳሰበን ስለመጣዉ ሁለት ነገር ነዉ» ብለዋል። በመቀጠል «አንደኛዉ በአገሪቱ በድርቅ ምክንያት የተከሰተዉ ረሃብ በሃገሪቱ ዙርያ ችግር እየፈጠረ መሆኑ፤ ሁለተኛዉ የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ረቆ በዚህ ሳምንት ወይም በሚቀጥለዉ ሳምንት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል። እኛ እንደ ሲቪል ማህበረሰብ ሌሎችንም አማክረን ረቂቁ ያጫረብንን ስጋት እንዲሁም ተስፋን ለማቅረብ እየተዘጋጀን ነዉ»   

የሽግግር ፍትሕ ረቂቁን በተመለከተ ምን ለማድረግ አስባችኋል? ለሚለዉ ጥያቄ ሰዋዊት፤   

ሴታዊት የፆታ እኩልነት ተሟጋች ንቅናቄምስል Setaweet

«በሽግግር ፍትሕ ዙርያ መንግሥት እየሰራበት ነዉ ያለዉ። ፖሊሲዉ በጣም ጥሩ ተደርጎ ነዉ የተረቀቀዉ። ይህ ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት በጣም በቅርቡ ይሄዳል ብለን እናስባለን፤  መጀመርያ ጥሩ የምንላቸዉን እና ያስተዋልናቸዉን ነገሮች በማመስገን እንናገራለን፤  ምክንያቱም ኢትዮጵያ ዉስጥ የሽግግር ፍትሕ ሲደረግ ለመጀመርያ ጊዜ ነዉ፤ ረቂቁ በጥሩ ደረጃ መሰራቱን አይተናል፤ መጀመርያ ጊዜ ያየነዉ ረቂቅ የሴቶችን ጉዳይ ያሟላ አልነበረም፤ ግን የኛም ድርጅትም ሆነ የተመድ ተባብረን ባደረግነዉ አስተዋጽኦ የሴቶች ጉዳይን አካቷል፤ በኢትዮጵያ  በሚታየዉ እና በነበረዉ ጦርነት ታይተዉ የማይታወቁ ነገሮች በተለይም በሴቶች ላይ ጾታዊ ጥቃት ተፈፅሟል» ሲሉ ዶክተር ስህን ተናግረዋል።  

ይሁንና የሽግግር ፍትህ በዚህ ጊዜ ሊካተት ይችላል ወይ ብለን፤ ትንሽ የሚከብዱ እና ምቾት የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመጠየቅ ተዘጋጅተናልም ሲሉ የሴታዊት አስተባባሪ አክለዋል። ለምሳሌ የሽግግርን ፍትህ ፖሊሲዉን ለማስረቀቅ ስራዉን የያዘዉ የፍትህ ሚኒስትር ነዉ። ግን የፍትህ ሚኒስትር በኢትዮጵያ ለተከሰቱ ችግሮች ተጠያቂ መሆን ሲገባዉ ፍትህ በኔ በኩል ነዉ የሚተላለፈዉ የሚለዉ ነገር፤ ከፍተኛ ስጋት አሳድሮብናልm፤ ብለዋል። በርካታ የአገራችን ክፍሎች በአሁኑ ወቅት በማያባራ ግጭት ውስጥ ይገኛሉ፣ ቀሪዎቹም ፀጥታ አስተማማኝ ሁኔታ ላይ ነው ያለው ለማለት ያስቸግራል። በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች በብዙ ቦታዎች ግጭቶች በሃገር መከላከያ ሰራዊት እና በፋኖ እና የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ታጣቂዎች መካክል እየተካሄዱ ነው።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ያለው የፀጥታ ሁኔታ የተረጋጋ ቢመስልም፣ ምርጫ እስካሁን ለማካሄድ አልተቻለም። በጋምቤላም እንዲሁ በቅርብ ጊዜያት በትጥቅ የተደገፉ ግጭቶች ታይተዋል። በትግራይ ነፍጥ ያዘለ ግጭት ባይኖርም፣ ጦርነቱ የፈጠራቸው ቀውሶች ገና በቂ መፍትሔ አላገኙም፣ የፕሪቶሪያውን ስምምነት አተገባበር በተመለከተም በርካታ ቀሪ ጉዳዮች አልተፈቱም። በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መካክል ያለው ጥርጣሬ፣ የጥላቻ እና የመራራቅ ስሜት ገና አልበረደም። የሽግግር ፍትህ ፖሊሲው በሃገሪቱ ዘላቂ ሰላም እና መተማመን ለማምጣት በጎ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ቢታመንም፣ አሁን ያለው የሃገሪቱ የፀጥታ ሁኔታ ካልተሻሻለ፣ መንግስትም ህግና ስርዓት የማስክበር ግዴታውን በአግባቡ ካልተወጣ በስተቀር የሽግግር ፍትህን ተግባራዊ ለማድረግ በጣም አዳጋች ይሆናል። አገሪቱ ውስጥ የሚታየው የግጭት አዙሪት እና ፈር የለቀቀ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ለብሔራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ከፍተኛ ተግዳሮት እንደሆነው ሁሉ ለሽግግር ፍትህ አፈፃጸምም እንቅፋት እንዳይሆን፡ መንግስት የህግ የበላይነትን ሊያረጋግጥ፣ የሰብዓዊ መብትቶች የማክበርና የማስከበር የፖለቲካ ቁርጠኝነት ሊኖረው ይገባል።

ሴታዊት የፆታ እኩልነት ተሟጋች ንቅናቄምስል Setaweet

ለምንድን ነዉ በአሁን ጊዜ ችግሮች ባልቆሙበት ጦርነት በሚካሄድበት እና የህዝብ ጥያቄ መልስ ባልተሰጠበት፤ የምዕራብ ትግራይ ጥያቄ ባልተመለሰበት የትግራይ ተፈናቃዮች ወደ ቤታጠዉ ባልተመለሱበት የሽግግር ፍተህ ለመጠየቅ መቅረባችን ከልባችን ነዉ ወይ? ይህ የፍትህ ጥያቅያችን ለይምሰል እንዳይሆን ብለን መጠየቅ እንፈልጋለን፤ የሚሉ ሃሳቦችም ተነስተዋል። በትግራይ ክልል ስለተደፈሩ ሴቶች ቁጥር የተለያዩ የዉጭ ሚዲያዎች እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በቁጥር ደረጃ አስቀምጠዋል፤ በአማራ ክልል በአፋር ብሎም በኦሮምያ የተደፈሩ ሴቶች ቁጥር ቀላል አለመሆኑም የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ። ባለፈዉ ሳምንት ከአማራ ክልል የመጡ የሴቶች ማህበራት፤ አሁን በሚካሄደዉ ጦርነት በክልሉ ወደ አራት ሺህ ሰዎች መደፈራቸዉን በገጻቸዉ ላይ ይፋ አድርገዋል።  ይሁንና ሴቶቹ በማን እንዴት እንደተደፈሩ የወጣ ግልጽ ነገር አለመኖሩ ተመልክቷል።   

በትግራይም ሆነ በአማራ ክልል ከፍተኛ ረሃብ እንዳለ የተለያዩ ዘገባዎች ይወጣሉ፤ ይህ የቤተሰብ ኃላፊ ለሆነችዉ የልጆች እናትዋ ከፍተኛ ተግዳሮች መሆኑም ተመልክቷል። ይህን ችግር በተመለከተ ሴታዊት ንቅናቄ በዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን «ማርች 8 » ችግሩ መፍትሄ እንዲያገኝ ጥሪ ታሰማለች።  በአዋሽ አፋር ክልል ሴቶች ማህበር አገልግሎት የምትሰጠዉ ሴት በሰብሰባዉ ላይ ተሳታፊ ነበረች። በአፋር የተደፈሩ ሴቶች ቁጥር ቀላል እንዳልሆነ እና ፤ ሴቶች ይህን ጉዳታቸዉን በይፋ ለመናገር ባህልና ልማድ እንደሚጫናቸዉ ተናግራለች። አስማ ሴቶችን በማማከር ስራዋ ሴቶች የደረሰባቸዉን ችግር ሳይደብቁ እና ሳይፈሩ እንዲናገሩ ምክር እንደምትሰጥ ተናግራለች። የአፋር ሴቶች በትግራይ በነበረዉ ጦርነት አሁንም በአማራ ክልል ባለዉ ጦርነት፤ ብሎም በአፋር እና ኢሳ መካከል የሚካሄደዉ የጎሳ ግጭት ሰለቦች እንደሆኑ ገልጻለች።

ከአሶሳ ባንባሲ ወረዳ የመጡ ሌላዋ ሴት ፤ በተለይ በግጭት እና ጥቃት ከኦሮምያ ተፈናቅለዉ ባንባሲ ዉስጥ የሚገኙ ተፈናቃይ ሴቶች መደፈራቸዉን አሁንም በመጠለያ ዉስጥ የሚደፈሩ ሴቶች መኖራቸዉን እና ችግር ዉስጥ መሆናቸዉን ተናግረዋል። በመጠለያ ጣብያዉ ከሴቶች መደፈር ሌላ ሴቶች የንጽህና መጠበቅያ ቁሳቁስ  አለመኖሩን ብሎም የምግብ እጥረት እንዳለ ገልጸዋል። በስርዓተ ፆታ ጉዳይ የማህበረሰብ አንቂ የሆነችዉ የሰላሌ ዩንቨርስቲ መምህርት ማህደር ዳዲ  አባታዊ የሆነ ስርዓታችን የፈጠረን ሴቶች በመሆናችን ይህን ለመቀየር ልንሰራ ይገባል፤ ስትል ተናግራለች።    

ስርዓታችን በዋነኝነት አባታዊ ስርዓት ነዉ። ሴቶቹም ብንሆን አባታዊ ስርዓት የፈጠረን ነን። ስለዚህ በራስ መተማመናችንም ይሁን ፤ ለራሳችን ያለን ግምት፤ ከወንዶቹ ተመጣጣኝም እኩልም አይደለም። የሄድንበት ስርዓት ራሱ አንቺ አትችይም፤ አንቺ ይህን ማድረግ አትችይም ፤ አንቺ ይህ አይሆንሽም እየተባለ እየተመረጠልን ነዉ ያደግነዉ። ስለሆነም አሁንም ቢሆን ሴቶች ከፍርሃት እና ከመሸማቀቅ የወጣን ነን ብዬ ለመናገር ይከብደኛል። ቢሆንም ግን አሁን ላይ አገራችን ላለችበት ነባራዊ ሁኔታ፤ ማዕከላዊ የሆነ ሰዉ፤ ወገንተኛ ያልሆነ፤ የተሻለ ፍርድ እና አገልግሎት ሊሰጥ የሚችል ሰዉ የሚመጣ ከሆነ አገር ካለችበት ሁኔታ ወጥታ ትስተካከላለች ብዬ አምናለሁ።  

ሴታዊት የፆታ እኩልነት ተሟጋች ንቅናቄምስል Setaweet

ብዙ ጥናቶችም እንደሚያረጋግጡት ሴቶች የተሻሉ ናቸዉ። ያለ አድሎ ከመስራት አንጻር የአገልጋይነት ስሜት ይዞ ህዝብን ከማገልገል አንጻር፤ ከወንዶች የተሻሉ ናቸዉ ብዬ አምናለሁ። ግን ወደፊት ለመምጣት፤ አሁን ያለዉ ሁኔታ እሳት ላይ እንደመቀመጥ ነዉ። በተለይ በተለይ አሁን አገራችን ላይ ያለዉን ነባራዊ ሁኔታን ስናይ፤ በአብዛኛዉ የቤተሰብ ሁኔታ፤ ሴቶች ጫንቃ ላይ ነዉ የተቀመጠዉ። ወንዶቹ ሴቶችን ለማገዝ ገና ናቸዉ። እና ይህ እስካልተሻሻለ ድረስ፤ ለዉጥ ሊመጣ አይችልም እና እዚህ ላይ መደንብ መሰራት መቻል አለበት። በተለይ ሴቶችን የሚጠብቅ ማህበረሰብ ያስፈልጋል። አሁን ላይ በየቦታዉ የምንሰማዉ እና ከህጻናት ጀምሮ ያለዉ ጥቃት፤ በቁጥርም በአይነትም በጣም ከፍተኛ ነዉ። ለዚህ ጠባቂ የሆነ ማኅበረሰብ ያስፈልጋል። ህጻንዋ ሴት ልጅ እንድትማር፤ ከፊለፊት ያለችዉ ያላትን የትምህርት ደረጃ እንድታሳድግ ፤ በአመራርነት ላይ ያለችዉ ደግሞ በነጻነት የተሻለ ቦታ ላይ ሆና የተሻለ ነገር ሰርታ እንድትመጣ የሚደረግበት አይነት ሁኔታ የሚፈጠር ከሆነ ምናልባትም አሁን ላለን ቁስል ሁነኛ መድሃኒት ነዉ ብዬ አምናለሁ።»     

ሴታዊት ይሄንን ራዕይ እውን ለማድረግ የተለያይዩ የሴቶች መብቶች ላይ የሚያተኩሩ ጥናታዊ ጽሁፎች እና የውይይት መድረኮችን ታዘጋጃለች። በማህበረሰቡ ውስጥ ያሉ ጾታ ላይ ያተኮሩ የተዛቡ እሳቤዎችን ለማስወገድ ስልጠናዎችን እና ዘመቻዎችን እንደ አስፈላጊነቱ ታካሂዳለች፤ እንዲሁም ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች የሥነ-ልቦናና ማህበራዊ ድጋፍ አገልግሎት ትሰጣለች። ሴታዊት በሀገራችን ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲካሄድ የቆየውን ግጭት አስመልክታም፤ በተደጋጋሚ በግልና ከሌሎች የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን በጦርነቱ ሴቶች በተለየ ሁኔታ ተጎጂ መሆናቸውን እና ፆታዊ ጥቃት የጦርነት መሳሪያ መደረጉን በመቃወም የጦርነት ይቁም ጥሪዎችን ስታሰማ ቆይታለች። ያለ ሴቶች ተሳትፎ ቤት አይደምቅም፤ አገር አይበለፅም ፖለቲካዉም አይሰምርም እና ሴቶቻችንን እያከበርን መብታቸዉን እያስከበርን፤ በሥራ እኩል ተሳታፊ እያደረግን፤ እንደ ግዕዝ እቃ የሚደፍራትን ለፍርድ እያቀረብን ፍትህን እየሰጠን የአገሪቱን አካሄድ እናቅና ያሉንን እንግዶቼን ለሰጡን ቃለ ምልልስ እያመሰገንኩ የዛሬዉን ዝግጅቴን እዚህ ላይ አጠናቅቃለሁ አዜብ ታደሰ ነኝ ጤና ይስጥልኝ።

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW