1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ አካባቢውን ለማተራመስ ከሚጥሩ ጋር ትንቀሳቀሳለች ያለቻትን ሶማሊያን አስጠነቀቀች

ዓርብ፣ ነሐሴ 24 2016

ሶማሊያ ሙሉ ጠንካራ የፀጥታ ተቋም እጇ ላይ እስኪገባ ድረስ ኢትዮጵያ ድጋፏን እንደምትቀጥል አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ አረጋግጠዋል። ይሁንና ሶማሊያ አካባቢውን ለማተራመስ ከሚጥሩ ያሏቸው አካላት ጋር የምታደርገው እንቅስቃሴ "በአዘቦት የሚታለፍ ነገር አይደለም"፣ ስለሆነም ሶማሊያ ይህንን ልታቆም ልታቆም ይገባል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

Äthiopien Botschafter Taye Atske Silassie
ምስል Solomon Muchie/DW

ኢትዮጵያ አካባቢውን ለማተራመስ ከሚጥሩ ጋር ትንቀሳቀሳለች ያለቻትን ሶማሊያን አስጠነቀቀች

This browser does not support the audio element.

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር ያላትን ግንኙነት በሰላም ለመፍታት እስከመጨረሻው ትገፋበታለች ብለዋል። ኢትዮጵያ ከሶማሊያ የምትወዛገብበት ጉዳይ በሰላም እንዱፈታ ግፊት የምታደርገው ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ እና "ድንበር ዘልሎ የሚመጣ ትርምስ" ስለማትፈልግ ነው ብለዋልም። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ራሷን ራስገዝ አድርጋ በምትቆጥረው ሶማሊላንድ ውስጥ ለሚገኘው ቆንስላ ጽሕፈት ቤቷ አዲስ አምባሳደር ሾማለች። ኢትዮጵያ  አምባሳደር ተሾመ ሹንዴ ሀርጌሳ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽሕፈት ቤት አምባሳደር ሆነው መሾማቸውን ዶቼቬለ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማረጋገጥ ችሏል። አምባሳደር ተሾመ ኬንያ ውስጥ በዲፕሎማትነት ሲያገለግሉ የቆዩ ሲሆን ለሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ የሹመት ደብዳቤ ማቅረባቸውን ከሶማሊላንድ የወጡ ዘገባዎች አመልክተዋል።

የሚኒስትሩ ዝርዝር መግለጫ 

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀ ሥላሴ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት በተለመለከተ በስፋት ማብራሪያ ሰጥተዋል። የኢትዮጵያ እና የጎረቤት ሶማሊያ ግንኙነት "ልዩ ትኩረትን ስቧል" ያሉት ሚኒስትሩ ምክንያቱም የግንኙነት ሰበዞች በርካታ በመሆናቸው ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በሁለቱ ሀገራት መካከል የተፈጠረውን ልዩነት በሰላም ለመፍታት ጥረት አድርጓል ያሉት ሚኒስትሩ፣ ይህንንም ለማሳካት በኬንያ ናይሮቢ እና በቱርክ አንካራ ተከታታይ ጥረቶች ተደርገው እንደነበር ገልፀዋል። ይሁንና "አንዳንድ የሶማሌ ባለስልጣናት ልዩነትን ማስፋት የዘወትር ተግባራቸው አድርገዋል" ሲሉ ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ሶማሊያ እንደ ሀገር እንድትቆም የሕይወት፣ የደም እና የአጥንት ብዙ መስዋዕትነ ስለመክፈሏ ሲያብራሩም "የቆጠብነው ነገር የለም" ብለዋል። ነገር ግን ይህንን አስተዋፅዖ ከቁብ አለመቁጠር ይከነክናል ነው ያሉት። "መስዋዕትነታችንን ማጣጣል ተገቢ አይደለም" 

ምስል Solomon Muchie/DW

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጥሪና ማስጠንቀቂያ

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የሶማሊያ መንግሥት ወደ ሰላም ሊመጣ እና አሸባብን በጋራ መዋጋታችንን ልንቀጥል ይገባል ሲሉ ጥሪ አድርገዋል። ሶማሊያ ሙሉ ጠንካራ የፀጥታ ተቋም እጇ ላይ እስኪገባ ድረስ ኢትዮጵያ ድጋፏን እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል። ይሁንና ሶማሊያ አካባቢውን ለማተራመስ ከሚጥሩ ያሏቸው አካላት ጋር የምታደርገው እንቅስቃሴ "በአዘቦት የሚታለፍ ነገር አይደለም"፣ ስለሆነም ሶማሊያ ህንን ልታቆም ይገባል ብለዋል።
የአፍሪካ ሕብረት የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ) በቀጣዩ ጥር ወር ተጠናቆ በቀጣይ AUSOM የሚበል የተለያዩ ሀገራት ጥምር ጦር ይዋቀራል ያሉት አምባሳደር ታዬ አፅቀ ሥላሴ የዚህ አወቃቀር ሁኔታ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ላይ "አዲስ ሥጋት" ይዞ መምጣቱን መንግሥታቸው  ሰሞኑን ያስታወቀ ሲሆን በዚህ ሂደት ሶማሊያ የኢትዮጵያን የተሳትፎ ጉዳይ በውል ታጤናለች የሚል እምነት መኖሩን አብራርተዋል።

በሶማሊላንድ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽ/ቤት አዲስ አምባሳደር ተሹሞለታል

በሌላ በኩል በሶማሊላንድ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽ/ቤት አዲስ አምባሳደር ተሹሞለታል። ተሿሚው አምባሳደር ተሾመ ሹንዴ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ ባለፈው ሰኔ ለ24 የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሠራተኛ ለነበሩ ዲፕሎማቶች የባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር እና የአምባሳደርነት ሹመት በሰጡበት ወቅት የአምባሳደርነት ሹመት የተሰጣቸውና አሁን ለዚህ ቆንስላ ጽሕፈት ቤት የተመደቡ ናቸው። ኢትዮጵያ ሶማሊላንድ ውስጥ ባላት የቆንስላ ጽ/ቤት ልዩ መልዕክተኛ ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩት አምባሳደር ደሊል ከድር ነበሩ። 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ታዬ አፅቀ ሥላሴ የግብጽ ወደ ሶመሊያ የጦር ኃይል ማስገባቷ ኢትዮጵያን እንቅልፍ የሚያሳጣ ጉዳይ እንዳልሆነና ይልቁንም ከሕዳሴ ግድብ ጋር ያለውን ልዩነት ለመፍታት አሁንም እንፈልጋለን ብለዋል። የኢትዮጵያን የባሕር በር የማግኘት ጉዳይም "ካጣነው በኋላ የገባን" ብለውታል።

ሰሎሞን ሙጬ 
ኂሩት መለሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW