1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ እና አከራካሪው የመንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ህግ

ሐሙስ፣ ግንቦት 20 2001

የኢትዮጵያ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከጥቂት ወራት በፊት አንድ እጅግ ገዳቢ የሆነ የመንግሥት ያልሆኑ የውጭና የሀገር ውስጥ ድርጅቶችን ምዝገባና መተዳዳሪያ ደምብ የሚመለከት ህግ ማጽደቁ ይታወሳል።

ምስል AP

ብዙዎች፡ ህጉ በርዳታ አሰጣጥ ተግባር ላይ በተሰማሩት ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ስራ ላይ ብርቱ ቁጥጥርና ጫና ያሳርፋል በሚል ብርቱ ተቃውሞ አሰምተዋል። ይህ አዲሱ ህግ በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ስራ ላይ ያሳረፈው ተጽዕኖ ይኖር ይሆን?
አዲሱ ህግ እስከዛሬ ግልጽነት ተጓድሎት የቆየውን መንግስታዊ ያልሆኑትን ድርጅቶች አሰራርና በጀታቸውን ለማስተካከል የታሰበ የወጣ መሆኑን የኢትዮጵያ መንግስት አስታውቋል። ይሁንና፡ ህጉን የሚጠራጠሩት ወገኖች ህጉ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችንና ማህበራትን ስር የሚያሰናክል አድርገው እንደሚመለከቱት የጀርመናውያኑ የዓለም ረሀብተኞች መርጃ ድርጅት የምስራቃዊና የደቡባዊ አፍሪቃ የርዳታ መርሀ ግብር ዋና ስራ አስኪያጅ ሀንስ ባይለርን አስታውቀዋል።
« እንደሚታወቀው፡ እኛ ህጉን በጥርጣሬ ነው የምንመለከተው። በዚሁ ህግ አንጻርም በዓለም አቀፍ ደረጃ፡ ባካባቢው ባሉ በኤምባሲዎች በኩል ተቃውሞአችንን አሰምተናል። እንዲያም ሆኖ ህጉ ጸድቆዋል። ይሁን እንጂ፡ መንግስት ህጉ በስራ ላይ ሊውል የሚችልበትን መመሪያ አላወጣም። »
ህጉ በተለይ የጎሳ፡ የጾታና የህጻናትን እና የአካል ተጎጂዎችን መብቶች ለማስከበር የሚጥሩ፡ እንዲሁም፡ ውዝግብ በማስወገዱ ረገድ ድርሻ ለማበርከት የሚፈልጉትን መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በተለይ ከበጀታቸው መካከል ከአስር ከመቶ የበለጠውን ከውጭ የሚያገኙ በጎ አድራጊ ድርጅቶችን ስራ ይገድባል በሚል ብርቱ ተቃውሞ የተፈራረቀበት ህግ ከጸደቀበት ጊዜ አንስቶ በድርጅቶቹ ስራ ላይ ያሳረፈው ተጽዕኖ ስለመኖሩ የጀርመናውያኑ የዓለም ረሀብተኞች መርጃ ድርጅት የምስራቃዊና የደቡባዊ አፍሪቃ የርዳታ መርሀ ግብር ዋና ስራ አስኪያጅ ሀንስ ባይለር ሲናገሩ፡
« እስካሁን ባለን መረጃ መሰረት፡ ህጉ እስከዛሬ ድረስ በተግባር አልተተረጎመም። በስራችን ላይ እስካሁን ያስከተለው አንዳችም ችግር የለም፤ ምክንያቱም፡ እኛ በሰብዓዊ መብት ማስከበሩ ዘርፍ ላይ አይደለም የተሰማራነው። እኛ ማለትም በኢትዮጵያ ከኛ ጋር የሚተባበሩት የሀገር ውስጥ አጋር ድርጅቶች የተሰማሩት በገጠር ልማት፡ በውኃ አቅርቦቱ ዘርፍ እንደመሆኑ መጠን እስካሁን ያጋጠመን ችግር የለም። »
ልክ እንደ ጀርመናዊው የርዳታ ሰጪ ድርጅት ባለሙያ ሀንስ ባይለርም፡ ካለፉት ሀያ ሶስት ዓመታት በርዳታ ስራ የተሰማሩት አቶ ሳልፊሶ ኪታቦም በሰጡን የግል አስተያየታቸው አዲሱ ህግ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ስራ ላይ ያስከተለው ችግር የለም። ሆኖም፡ ህጉ በርግጥ ጎጂ ጎን ይኑረው አይኑረው ለማወቅ መንግስት ወደፊት አወጣዋለሁ ያለውን ዝርዝር መመሪያ ጠብቆ መመልከቱ ጠቃሚ እንደሚሆን ነው ያስረዱት።

አርያም ተክሌ/ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW