ኢትዮጵያ እና ኤርትራ “ማንኛውንም ውጥረት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲፈቱ” ሀገራት ጥሪ አቀረቡ
ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 4 2018
የኢትዮጵያ እና የኤርትራ “ሉዓላዊነት፣ ነጻነት እና የግዛት አንድነት እንዲከበር” ብሪታኒያ እና ቱርክን ጨምሮ አምስት ሀገራት በጋራ ጥሪ አቀረቡ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ በሐምሌ 2010 በተፈራረሙት “የሰላም ሥምምነት መንፈስ ማንኛውም ውጥረት ወይም አለመግባባት በሰላም እና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲፈታ” ጠይቀዋል።
የካናዳ፣ ጃፓን፣ ኖርዌይ፣ ቱርክ እና ዩናይትድ ኪንግደም መንግሥታት ጥሪውን ያቀረቡት የአልጀርስ ሥምምነት የተፈረመበትን 25ኛ ዓመት በማስመልከት ትላንት አርብ ባወጡት መግለጫ ነው።
ሀገራቱ በ1993 የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እና ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ በአልጀርስ የተፈራረሙትን ሥምምነት፣ ሥምምነቱ የሚያራምዳቸውን መርኆዎች እና በሥምምነቱ የተቋቋመው ኮሚሽን የወሰናቸውን ድንበሮች እንደሚደግፉ በጋራ መግለጫቸው ጠቁመዋል።
የአውሮፓ ኅብረት “የአልጀርስ ሥምምነትን እና በድንበር ኮሚሽኑ የተወሰነውን” የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ድንበር “ሙሉ በሙሉ” እንደሚደግፍ አስታውቋል።
በ1993 በአልጀርስ እንዲሁም በ2010 በአስመራ በተፈረሙት ሥምምነቶች መሠረት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ አንዳቸው የሌላቸውን “ሉዓላዊነት፣ ነጻነት እና የግዛት አንድነት” እንዲያከብሩ የአውሮፓ ኅብረት ጥሪ አቅርቧል።
ኅብረቱ እንደሚለው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና ፕሬዝደንት ኢሳያስ የአስመራ መግለጫን ሲፈራረሙ “ሁለቱ ሀገሮች የአልጀርስ ሥምምነትን እና በሥምምነቱ በተቋቋመው የድንበር ኮሚሽን የተወሰነውን ድንበር ለማክበር ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።”
ሁለቱም ወገኖች “ማንኛውንም ውጥረት ወይም አለመግባባት በሰላማዊ እና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲፈቱ” ጥሪ ያቀረበው የአውሮፓ ኅብረት “ይህ ለቀጠናው መረጋጋት ቁልፍ” እንደሆነ አሳስቧል።
ሀገራቱ የአልጀርስ ሥምምነትን እያስታከኩ ያወጧቸው መግለጫዎችበኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ያለው ውጥረት እንዳሳሰባቸው የሚጠቁሙ ናቸው።
የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ “ለዘላቂ ሰላም” እና አንዳቸው የሌላውን “ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት” ለማክበር ለተፈራረሙት የአልጀርስ ሥምምነት ቁርጠኝነታቸውን እንዲያረጋግጡ ትላንት አርብ ጥሪ አቅርበው ነበር።
አርታዒ ታምራት ዲንሳ