1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ እና ኤርትራ የሰላም ስምምነት ሊፈራረሙ ነው

ቅዳሜ፣ መስከረም 5 2011

ኢትዮጵያ እና ኤርትራ "በመካከላቸው ያለውን አዎንታዊ ግንኙነት ለማጠናከር" ያለመ ስምምነት በነገው ዕለት በሳዑዲ አረቢያ ሊፈራረሙ ነው። በጅዳ ከተማ በሚደረገው የፊርማ ሥነ-ሥርዓት የሳዑዲው ንጉስ ሳልማን፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬሽ እና የአፍሪቃ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋኪ ማሐማት ይገኛሉ ተብሏል

President Isaias Afwerki &  Prime Minister Abiy Ahmed in Asmera
ምስል Yemane G. Meskel

የኢትዮጵያው ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ እና የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሰላም ስምምነት ለመፈራረም ሳዑዲ አረቢያ ገቡ። ኢትዮጵያ እና ኤርትራ የሰላም ስምምነት የሚፈራረሙት ነገ እሁድ በሳዑዲ አረቢያ በሚደረግ ጉባኤ ላይ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል።

የኢትዮጵያው ጠቅላይ ምኒስትር ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍጹም አረጋ በትዊተር ገፃቸው ማምሻውን እንደገለጹት ጠቅላይ ምኒስትር አብይ ወደ ሳዑዲ የተጓዙት በልዑል መሐመድ ቢን ሳልማን በቀረበላቸው ግብዣ ነው። በዚህም መሰረት ጠቅላይ ምኒስትሩ በኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እና ሳዑዲ አረቢያ የሶስትዮሽ ጉባኤ እንደሚሳተፉ አስታውቀዋል። የኤርትራው ማስታወቂያ ምኒስትር አቶ የማነ ገብረ መስቀል በበኩላቸው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ያመሩት ሀገራቸው ቀደም ሲል ከኢትዮጵያ ጋር ያደረገችውን ስምምነት ይበልጥ ለማጠናከር ነው።  

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ቃል-አቀባይ ፋርሐን ሐቅ በትላንትናው ዕለት በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ "በመካከላቸው ያለውን አዎንታዊ ግንኙነት ለማጠናከር" ያለመ ስምምነት እንደሚፈራረሙ አስታውቀው ነበር። በሁለቱ ሀገራት መካከል ስምምነቱን የሚፈራረሙት በሳዑዲ አረቢያው ንጉስ ሳልማን አማካኝነት መሆኑንም  ተናግረዋል። ከቀይ ባሕር ዳርቻ በምትገኘው የጅዳ ከተማ እንደሚፈረም በሚጠበቀው በዚህ ስምምነት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬሽ እና የአፍሪቃ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋኪ ማሐማት ይገኛሉ ተብሏል። 
 
ጠቅላይ ምኒስትር አብይ እና ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ባለፈው ሐምሌ 2 ቀን 2010 ዓ.ም. "የሰላም እና የወዳጅነት መግለጫ" የጋራ ሰነድ በአስመራ ከተማ የተፈራረሙ ሲሆን የነገው ስምምነት ሁለተኛቸው ይሆናል። ጠቅላይ ምኒስትር አብይ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አስመራ ተጉዘው የፈረሙት ሰነድ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ሰፍኖ የቆየው የጦርነት ሁኔታ በይፋ ማብቃቱ ይፋ የተደረገበት ነበር። 

"የሰላም እና የወዳጅነት አዲስ ዘመን" መከፈቱን ያበሰረው ሰነዱ ለሁለት አስርት አመታት በአይነ ቁራኛ ሲተያዩ የከረሙት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ "ጥብቅ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ባሕላዊ እና የጸጥታ ትብብር" እንደሚመሰርቱም ገልጿል። ሁለቱን አገሮች ወደ ጦርነት በከተታቸው የድንበር ይገባኛል ውዝግብ ላይ የተላለፈው ውሳኔ እንደሚተገበር ሁለቱ መሪዎች መሥማማታቸውን በዚሁ ሰነድ ገልጸዋል። 

ባለፉት ሶስት ወራት በተደጋጋሚ ሲገናኙ የቆዩት ሁለቱ መሪዎች የኢትዮጵያን የዘመን መለወጫ በዓል ምክንያት በማድረግ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ይፋዊ የየብስ ግንኙነት እንዲጀመር አድርገዋል። የየብስ ግንኙነቱ የተጀመረባቸው በዛላምበሳ እና ቡሬ መስመሮች ያሉ መንገዶች ናቸው። 

እሸቴ በቀለ

ተስፋለም ወልደየስ 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW