ኢትዮጵያ እና ኬኒያ ድንበር ላይ የሚታዩ ግጭቶችን ለመፍታት መስማማታቸዉ
ሰኞ፣ መስከረም 5 2018
የኢትዮ- ኬኒያ የጋራ መድረክ
ኢትዮጵያ እና ኬኒያ በቱርካና ድንበር የሚስተዋሉ የሰላምና የፀጥታ መደፍረስን በትብብር ለመቅረፍ የሚያስችላቸውን ሥምምነት አድርገዋል ፡፡ “ ቱርሚ ዲክላሬሽን “ በሚል ትናንት የተደረሰው ሥምምነት የተፈጥሮ ሀብትን በጋራ ለመጠቀም ፤ እንዲሁም መሠረተ ልማትና ንግድን ጨምሮ የሁለትዮሽ የልማት ትብብርን ለማጎልበት ያስችላል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል ፡፡
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ሁለቱ አገራት የሚዋሰኑበት የቱርካና አካባቢ ሄድ መለስ የሚል ግጭት ተለይቶት አያውቅም ፡፡ በተለይም በድንበሩ በዓሳ ማስገር እና የከብት ግጦሽ ፍለጋ የሚደረግ መገፋፋት ዋነኛ የግጭት ምክንያት መሆኑ ይነገራል ፡፡ በአካባቢው በዚህ ዓመት ብቻ በተቀሰቀሱ ግጭቶች ከሁለቱም ወገን የበርካቶች ህይወት ማለፉ የሚታወቅ ነው ፡፡ የሁለቱ አገራት ባለሥልጣናት እነኝህን ግጭቶች ለማስቀረትና የልማት ትብብርን ለመፍጠር ያስችላል ያሉትን የጋራ ውይይት በደቡብ ኦሞ ዞን ቱርሚ ከተማ አካሂደዋል ፡፡ የጋራ ውይይቱ የተካሄደው በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እና በኬኒያ የቱርካና ግዛት ከፍተኛ የመንግሥት ሃላፊዎች መካከል ነው ፡፡ ኢትዮጵያውያን በኬንያ እና ታንዛንያ እስር ቤቶች
የጋራ መድረኩ የደረሰባቸው ስምምነቶች ምንድን ናቸው ?
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ጥላሁን ከበደ ሥምምነቱ በሁለቱም ወገን የጋራ መግባባት የተደረገበት መሆኑን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል ፡፡ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት እና በቱርካና ካውንቲ አስተዳደር መካከል ቁርጠኝነት ያለው ትብብር የግድ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ “ይህም በቀጠናው የዳሰነች፤ የኛንጋቱም እና የቱርካና የአዋሳኝ አካባቢ ማህበረሰቦች ፍላጎትንና የጋራ ተጠቃሚነትን ተደራሽ ለማድረግ ያስችላል ፡፡ በዚህ መነሻም በሁለትዮሽ የስምምነት ማዕቀፍን መሠረት ያደረጉ በፍጥነት መከናወን የሚገባቸው ስራዎችን ለይተናል “ ብለዋል ፡፡
ቀጠናው ሀገር በቀል የማህበረሰብ የግጭት አፈታት ስርዓቶችን ለይቶ በማጠናከር የሚከሰቱ አለመግባባቶች ወደ ግጭት ሳያመሩ መፍታት ፤ የአዋሳኝ አካባቢ ማህበረሰቦች የመሠረተ ልማት እና የኢኮኖሚ ትብብሮች ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በትብብር መስራት የሚሉት በስምምነቱ ከተካተቱት መካከል መሆናቸውን ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቅሰዋል ፡፡ ኢትዮጵያና ኬንያ ድንበር አካባቢ በተከሰተ ግጭት 25 ሰዎች ተገደሉ
ልዩ መልዕክተኛ ሥለውውይቱ ምን አሉ ?
በውይይቱ የቱርካና ግዛትን በመወከል የተሳተፉት ጆን ሙኒያስ በኬንያው ፕሬዚዳንት የሰላም ልዩ መልዕክተኛ ናቸው ፡፡ ጆን ሙኒያስ በውይይቱ በአዋሳኝ ድንበሮች ላይ የፀጥታና የልማት ሥራዎችን በቅንጅት ለማከናዋን የሚያስችል መሠረት መጣሉት ይናገራሉ ፡፡
በቱርሚ ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸውን የገለጹት ጆን “ ባለፉት ጊዜያቶች ከተፈጥሮ ፀጋ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ አልፎ አልፎ ግጭቶች ይታዩ ነበር ፡፡ ዛሬ ይህንን ግጭት ለመፍታት ተስማምተናል ፡፡ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እና በቱርካ በኩል ያሉትን ችግሮች ለይተናል ፡፡ በቀጣይም በጋራ የምንሠራ ይሆናል “ ብለዋል ፡፡ ኢትዮጵያውያን ስደተኛ ወጣቶች በኬንያ
ሥምምነቱ ለጎርብትና መጠናከር ያለው ጠቀሜታ
ዶቼ ቬለ የሁለቱ ግዛቶች ባለሥልጣናት ያደረጉት የጋራ ውይይትና የደረሱበትን ሥምምነት አስመልክቶ የፖለቲካ ሳይንስና የአለምአቀፍ ግንኙነት ባለሙያውና የግሎባል ፒስ ባንክ የሰላም ግንባታ ዳይሬክተር አቶ ደያሞ ዳሌን አስተያየት ጠይቋል ፡፡ አቶ ዳያሞ ሥምምነቱ ለሁለቱ ተጎራባች ህዝቦች የጎላ ጠቀሜታ አለው ይላሉ ፡፡ በተለይም ሁለቱ አጋራት በሚዋሰኑበት የቱርካና ሀይቅ ላይ የጋራ ክትትል ማድረግ አንዱ የሥምምነቱ አካል መሆኑን የጠቀሱት አቶ ዳያሞ “ በተጨማሪም በድንብር ላይ የጋራ ገበያ / croos boader mareket / ለማቋቋም ተስማምተዋል ፡፡ ይህም በመተማመን ላይ የተመሠረተ ጉርብትናን ለማጠናከር ያስችላል ፡፡ ዋናው ወደ ተግባር መቀየሩ ላይ ሥራዎች መሠራት አለባቸው ፡፡ ያ ከሆነ በአካባቢው ዘላቂ ሰላም በማምጣትና በንግድ በመተሳሰር ትልቅ ለውጥ ያመጣል የሚል እምነት አለኝ “ ብለዋል ፡፡
በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ የሁለትዮሽ የስምምነት ማዕቀፍን መሠረት ያደረጉና በፍጥነት መከናወን የሚገባቸው ስራዎች እንዲከናወኑ በሃላፊዎቹ የሥራ ስምሪት የተሰጠ ሲሆን ይህንኑ የሚያስፈጽሙ ኮሚቴዎች መቋቋማቸው ታውቋል ፡፡
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
አዜብ ታደሰ
ዮሃንስ ገብረግዚአብሔር