1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ኢትዮጵያ ከ22 ዓመት በኋላ በአዳጊዎቿ ለአፍሪቃ ዋንጫ አለፈች

ረቡዕ፣ ኅዳር 24 2018

የኢትዮጵያ ዕድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ የእግር ኳስ ተጨዋቾች ከ22 ዓመታት በኋላ ለአፍሪቃ ዋንጫ ማለፍ ችለዋል ። ቡድኑ ማለፉን ያረጋገጠው ማክሰኞ ኅዳር 23 ቀን፣ 2018 ዓ.ም የኬንያ አቻውን አዲስ አበባ ውስጥ 3 ለ0 ድል ካደረገ በኋላ ነው ። ፌዴሬሽኑ ይህ አጋጣሚ ከእጁ እንዳይወጣ ብዙ ሊሠራ እንደሚገባ ተገልጧል ።

የአፍሪቃ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (CAF) ዓርማ
የአፍሪቃ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (CAF) ዓርማ፦ የኢትዮጵያ እድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪቃ ዋንጫ አልፏል

የተገኘው እድል ከእጅ እንዳይወጣ ጠንክሮ መሥራት ያሻል

This browser does not support the audio element.

ኢትዮጵያ ከ22 ዓመታት ቆይታ በኋላ በአዳጊ የእግር ኳስ ተጨዋቾቿ ወደ አፍሪቃ ዋንጫ ተመልሳለች ። ማክሰኞ ኅዳር 23 ቀን፣ 2018 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ፥ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ውስጥ በነበረው ግጥሚያ የኢትዮጵያ አዳጊ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን የኬንያ አቻውን 3 ለ0 ድል በማድረግ ደጋፊዎቹን አስቦርቋል ። ግቦቹን ዳዊት ካሣው፣ ቢንያም አብርሃ እና ብሩክ ዕይላቸው አስቆጥረዋል ። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብርሃኑ ጥላሁን ከሁለት ዐሥርተ-ዓመታት በኋላ በተገኘው ድል እሳቸውም ፌዴሬሽኑም እጅግ መደሰቱን ገልጠዋል ።

«እውነት ለመናገር 22 ዓመት በኋላ ነው ይህን ታሪክ መሥራት የቻልነው፥ በዚም እጅግ በጣም ደስተኖች ነን በአዳጊዎች እግር ኳስ ልማት ላይ በደንብ ከተሠራ የተሻለ ነገር ማምጣት እንደሚቻል ያሳየንበት ውጤት ነው ማለት ይቻላል እና እዚህ ታሪክ ውስጥ በመኖሬ በጣም ደስተኛ ነኝ፤ እንደ ኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም ሁላችንም እጅግ በጣም ደስተኞች ነን »

በዶይቸ ቬለ የኪስዋሂሊ ክፍል የስፖርት አዘጋጅ ኬኒያዊው ጋዜጠኛ ጆሴፋት ቻሮ በትናንቱ ግጥሚያ የኬንያ ቡድን ከኢትዮጵያ ጋር ሲነጻጸር የተጨዋቾቹ ብቃት ደካማ ነበር ብሏል ። በተለይ ደግሞ ተከላካዮች እና ግብ ጠባቂው የኢትዮጵያ አጥቂዎችን መቆጣጠር ተስኗቸው እንደነበር ገልጧል ። እንዲያም ሆኖ እስከ 66ኛው ደቂቃ ድረስ የኬንያ  ቡድን የተረጋጋ ነበር ብሏል ። ከዚያ በኋላ ግን የትኩረት አቅጣቸውን እና ሚዛናቸውን ማጣታቸውን አክሏል ። ለኢትዮጵያ ቡድንም መልካም ምኞቹን ገልጧል ።

«ድንቅ ነው፤ ለኢትዮጵያ ቡድን ለዚያ አስደናቂ ድል እንኳን ደስ ያላችሁ ታላቅ ድል ነው እናም አሁን ማለፍ ችለዋል፣ ያም ይገባቸዋል አሁን ለአፍሪቃ ዋንጫ በማለፍ ታንዛኒያ እና ዩጋንዳን ተቀላቅለዋል   ይህ በጣም ደስ የሚል እና አስደናቂ ነው እንኳን ደስ ያላቸው »

የተገኘው እድል ከእጅ እንዳይወጣ ጠንክሮ መሥራት ያሻል

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በፌስቡክ ይፋዊ ገጹ ላይ ባወጣው አጠር ያለ ጽሑፍ፦ «ኢትዮጵያ ውድድሩን በስኬት እንድታስተናግድ ድጋፍ» ላደረጉ አካላት በመላ ምስጋናውን አቅርቧል ። ጀርመን አገር ነዋሪ የሆኑት የኤኮኖሚ እና አስተዳደር ባለሞያው እንዲሁም በስፖርቱ ዘርፍ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ በኃላፊነት የሚያገለግሉት ዶ/ር  ዶ/ር ፀጋዬ ደግነህ ለፌዴሬሽኑ መልእክት አላቸው ። 

አዲስ አበባ ስታዲየም፦ ፎቶ ከማኅደር ። ማን ያውቃል? አንድ ቀን የኢትዮጵያ እግር ኳስ በዚህ ስታዲየም በርካቶችን ያስቦርቅ ይሆናልምስል፦ Omna Tadel

«ለፌዴሬሽኑ ይኼ ትልቅ ስኬት የመሆኑን ያህል ትልቅ ኃላፊነት ነው ይህን ስኬት ማጣት የለበትም እጢህ ላይ ጠንክሮ ለመሥራት እያንዳንዱን ተጨዋች በግል፣ በጨዋታ ብቃት፣ አብሮ በማጀብ እንዲሁም በሥነ-ልቦና እና ዓለም አቀፋዊ ልምድ ሊያገኙበት የሚችሉበት ላይ መሠራት አለበት »

መንግስት ከ17 ዓመት በታች ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የ10 ሚሊዮን ብር ማበረታቻ ሽልማትና ውቅና መስጠቱን ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር-ኢትዮጵያ ዘግቧል ። የኢትዮጵያ ቡድን ቀድሞ ከሚታማበት የእድሜ ጉዳይ በተለየ መልኩ ዘንድሮ የተጨዋቾች ትክክለኛ እድሜ በምርመራ መረጋገጡም ተገልጧል ።  በኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮ ስፖርት መርኃ ግብር ዋና አዘጋጅ ምስጋናው ታደሰ ዕድሜ ላይ ጥሩ እንደተሠራ ጠቁሟል ። «በካፍም በሴካፋም ባለሞያዎች አስፈላጊውም ምርመራ ተደርጎላቸው በትክክለኛ እድሜ ላይ ይገኛሉ ተብለው የተረጋገጡ ወጣቶች ናቸው ።» በውድድሩ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ኬንያ፤ ታንዛኒያ፣ ዩጋንዳ፣ ሱዳን፣ ርዋንዳ፣ ብሩንዲ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ እና ጅቡቲ በሁለት ምድብ ተደልድለው ተጫውተዋል ።

ቀጣዩ ከ17 ዓመት በታች የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ አዘጋጅ የዘንድሮ ዋንጫን የወሰደችው ሞሮኮ ናት ። ከምሥራቅ አፍሪቃ በፍጻሜው ግጥሚያ ዩጋንዳን 3 ለ2 በመርታት ዋንጫ ያነሳችው ታንዛኒያእና ሁለተኛ ደረጃ ያገኘችው ዩጋንዳ እንዲሁም በሦስተኛነት ያጠናቀቀችው ለአፍሪቃ ዋንጫ ኢትዮጵያ ማለፋቸውን አረጋግጠዋል ። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ፀሐይ ጫኔ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW