1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ የወደብ ጥያቄና የኤርትራ አፋር ብሔራዊ ጉባኤ አቋም

ነጋሽ መሐመድ
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 20 2016

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ በቅርቡ ኢትዮጵያ የወደብ ባለቤትነት ወይም ተጠቃሚነት «ጥያቄ ማንሳት አለባት» ማለታቸዉ የሁለቱ መሪዎች ልዩነት የፈጠረዉና ልዩነቱን ይበልጥ ያሰፋ ምክንያት ተደርጎም ይጠቀሳል።

የኤርትራ አፋር ብሔራዊ ጉባኤ የኤርትራን መንግስት ይቃወማል
የኤርትራ አፋር ብሔራዊ ጉባኤ አርማ

ቃለ መጠይቅ፣ የወደብ ጥያቄና የኤርትራ አፋር ብሔራዊ ጉባኤ አቋም

This browser does not support the audio element.

የኢትዮጵያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድና የኤርትራዉ ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ የዛሬ አምስት ዓመት ግድም መስርተዉት የነበረዉ ጥብቅ ወዳጅነት እየሻከረ መምጣቱን የተለያዩ ወገኖች እየገለፁ ነዉ።ግንኙነቱ የሻከረ ወይም የቀዘቀዘበትን ምክንያት ሁለቱ ወገኖች እስካሁን በግልፅ አላስታወቁም።

ይሁንና ጥብቅ ይመስል የነበረዉ ወዳጅነት መቀዝቀዙ፣ የቀዘቀዘበት ምክንያትና የደረሰበት ደረጃ በአፍሪቃ ቀንድ አካባቢ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ድርጅቶችን ትኩረት ስቧል።አንዳድ አስተያየት ሰጪዎች ሁለቱ መሪዎች በግል የጀመሩትን ወዳጅነት በግልፅ እንዳላሳወቁ ሁሉ አሁንም ልዩነት ወይም ጠባቸዉን በግልፅ አያሳዉቁም በማለት ይተቻሉ።

የአዲስ አበባና የአስመራ መሪዎችን መልዕክት፣ እርምጃና የየደጋፊዎቻቸዉን እንቅስቃሴ በቅርብ የሚከታተሉ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ግን የሁለቱ መሪዎች «ጥብቅ ፍቅር» መደፍረስ የጀመረዉ የኢትዮጵያ ፌደራዊ መንግስትና ሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ህወሓት) አምና በዚሕ ሰሞን ፕሪቶሪያ ዉስጥ የሰላም ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ ነዉ።

ኤርትራም የተሳተፈችበት ጦርነትን ያስቆመዉ ድርድርና ስምምነት ሲደረግ አስመራ አለመወከሏ ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂን ቅር ማሰኘቱ በሰፊዉ ይነገራል።የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ በቅርቡ ኢትዮጵያ የወደብ ባለቤትነት ወይም ተጠቃሚነት «ጥያቄ ማንሳት አለባት» ማለታቸዉ የሁለቱ መሪዎች ልዩነት የፈጠረዉና ልዩነቱን ይበልጥ ያሰፋ ምክንያት ተደርጎም ይጠቀሳል።

አቶ ዓሊ መሐመድ ዑመር የኤርትራ አፋር ብሔራዊ ጉባኤ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና ቃል አቀባይምስል Ali Mohammed Omer

ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ ስለወደብ የሰጡትን መግለጫና ማብራሪያ ከኤርትራ በተጨማሪ ሶማሊያና ጀቡቲም ተቃዉመዉታል።የኤርትራ መንግስትን የሚቃወመዉ የኤርትራ አፋር ብሔራዊ ጉባኤ (EANC-በእንግሊዝኛ ምሕጻሩ) የጠቅላይ ሚንስትሩን የወደብ ሐሳብ ተቃዉሞታል።የጉባኤዉ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና ቃል አቀባይ አቶ ዓሊ መሐመድ ዑመር እንደሚሉት ፓርቲያቸዉ የሚቃወመዉ «የወደብ ባለቤትነትን እንጂ ወደብ መጠቀምን አይደለም» ይላሉ።

የኢትዮጵያና የኤርትራ መሪዎችን ግንኙነት በተመለከተም አቶ ዓሊ ግንኙነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ «እየሻከረ መምጣቱን የሚያመለክቱ እርምጃዎች» እንዳሉ ይናገራሉ። አቶ ዓሊ እንዳሉት ሰሞኑን በኢትዮጵያና ኤርትራ ድንበር አካባቢዎች በተለይም አሰብ ዉስጥ ከፍተኛ ወታደራዊ እንቅስቃሴና አዳዲስ ጦር ኃይል እየሰፈረ ለመሆኑ መረጃ ደርሷቸዋል።ማገናኛዉን በመጫን ከአቶ ዓሊ ጋር ያደረግነዉን ሙሉ ቀለ ምልልስ ያድምጡ።

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW