1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሞሪታኒያን ወደ አጎዋ ስትመለስ የኢትዮጵያ ውትወታ መልስ ሳያገኝ ቀረ

Eshete Bekele
ረቡዕ፣ ጥቅምት 28 2016

ሞሪታኒያ የአፍሪካ ሀገሮች ያለ ቀረጥ ሸቀጦቻቸውን በአሜሪካ ገበያ እንዲሸጡ ወደ ሚፈቅደው አጎዋ ስትመለስ የኢትዮጵያ ውትወታ መልስ ሳያገኝ ቀርቷል። የአሜሪካ የንግድ ተወካይ ቢሮ ኢትዮጵያ ለአጎዋ ብቁ መሆን አለመሆኗን ባለፈው ዓመት መጨረሻ ቢገመግምም ጉዳዩ ውሳኔ እየተጠባበቀ ነው። ዩጋንዳን ጨምሮ አራት ሀገሮች ከታህሳስ ጀምሮ ከአጎዋ ተሰርዘዋል

የአሜሪካ የንግድ ተወካይ ካትሪን ታይ በደቡብ አፍሪካ በተካሔደው የአጎዋ 20ኛ ጉባኤ
በጁሐንስበርግ በተካሔደው እና ወደ 40 የሚሆኑ የአፍሪካ ሀገራት የንግድ ሚኒስትሮች በታደሙበት የአጎዋ 20ኛ ጉባኤ የአሜሪካ የንግድ ተወካይ ካትሪን ታይ የንግድ ሥርዓቱ እንዲራዘም ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ምስል SIPHIWE SIBEKO/REUTERS

ሞሪታኒያን ወደ አጎዋ ስትመለስ የኢትዮጵያ ውትወታ መልስ ሳያገኝ ቀረ

This browser does not support the audio element.

ሞሪታኒያ ሸቀጦቿን ያለ ቀረጥ በአሜሪካ ገበያ እንድትሸጥ የሚፈቅደውን አጎዋ እንደገና ስትቀላቀል የኢትዮጵያ ውትወታ ምላሽ ሳያገኝ ቀርቷል። ሰሜን ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር በሠራተኞች መብት ጥበቃ እና አስገዳጅ የጉልበት ሥራን በማስወገድ ረገድ “ተጨባጭ እና የሚለካ” መሻሻል በማሳየቷ ከታህሳስ 22 ቀን 2016 ጀምሮ ወደ አጎዋ እንደምትመለስ የአሜሪካ የንግድ ተወካይ ቢሮ አስታውቋል።

ሞሪታኒያ በአፍሪካ የዕድገት እና ዕድል ድንጋጌ (African Growth and Opportunity Act) በኩል ለመነገድ ብቁ ሆና የተገኘችው አምባሳደር ካትሪን ታይ የሚመሩት የአሜሪካ የንግድ ተወካይ ቢሮ ካካሔደው ዓመታዊ ምዘና በኋላ ነው። የትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎችን ባዳረሰው ጦርነት ተፈጽመዋል በሚባሉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ሳቢያ ኢትዮጵያ በታህሳስ 2014 ወዳጣችው አጎዋ ለመመለስ ያቀረበችውን ጥያቄ የመረመረው የአሜሪካ የንግድ ተወካይ ቢሮ አዎንታዊ ምላሽ ሳይሰጥ ቀርቷል።

ምላሽ ያጣው የኢትዮጵያ ውትወታ

የኢትዮጵያ ከአጎዋ መሰረዝ የሐዋሳ የኢንዱስትሪ ፓርክን የመሰሉ ተቋማት አማራጭ ገበያ እንዲያፈላልጉ አስገድዷቸዋል። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ኢትዮጵያ በይፋ ከአጎዋ ከመሰረዟ በፊትም ሆነ በኋላ የፕሬዝደንት ጆ ባይደን አስተዳደር በጉዳዩ ላይ የያዘውን አቋም እንዲቀይር ግፊት ሲያደርግ ቆይቷል።

በጦርነቱ የሻከረው የኢትዮጵያ እና የአሜሪካ ግንኙነት የመሻሻል አዝማሚያ ሲያሳይ በመጋቢት 2015 ወደ አዲስ አበባ ያቀኑት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በፕሪቶሪያ የተፈረመው የግጭት ማቆም ሥምምነት አተገባበር ለጉዳዩ ቁልፍ እንደሆነ ተናግረው ነበር። 

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ወደ አዲስ አበባ ባቀኑበት ወቅት “ኢትዮጵያ ወደ አጎዋ ለመመለስ በግልጽ የተቀመጡ መስፈርቶችን ማሟላት አለባት” ሲሉ ተናግረው ነበር። ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በፕሪቶሪያ የተፈረመው የግጭት ማቆም ሥምምነት አተገባበር ለውሳኔው ቁልፍ ሚና እንደሚኖረው ጥቆማ ሰጥተዋል። ምስል Fana Broadcasting Corporate S.C

“እርምጃውን የወሰድንው ሕግ ስለሚያስገድደን ነው“ ያሉት ብሊንከን “ኢትዮጵያ ወደ አጎዋ ለመመለስ በግልጽ የተቀመጡ መስፈርቶችን ማሟላት አለባት። እኛም የምንጋራውን ያንን ዓላማ ለማሳካት በግጭት ማቆም ሥምምነቱ በተለይም በአተገባበሩ ረገድ አስተዳደራችን ከመንግሥት ጋር በቅርበት ይሰራል” ሲሉ ተናግረዋል።

በደቡብ አፍሪካ ከህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ጋር የተፈረመው ግጭት የማቆም ሥምምነት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ኢትዮጵያን ወደ አጎዋ ለመመለስ ሲያደርግ በቆየው ውትወታ በቀዳሚነት የሚያቀርበው መከራከሪያ ነው።

መንግሥት በቀጠረው ስኩየር ፓተን ቦግስ (Squire Patton Boggs) የተባለ ኩባንያ በኩል በየካቲት 2015 ለአምባሳደር ካትሪን ታይ ባቀረበው ማመልከቻ የሥምምነቱን አተገባበር ሒደት ዘርዝሮ በማቅረብ የኢትዮጵያ ጉዳይ ከመደበኛው አሰራር በተለየ ምዘና (out of cycle review) እንዲታይ ጠይቆ ነበር።

መቀመጫውን ዋሽንግተን ባደረገው ኩባንያ ለአምባሳደር ታይ በተጻፈው ደብዳቤ 56,000 የሥራ መደቦች በአጎዋ በኩል ወደ አሜሪካ በሚላክ የወጪ ንግድ ላይ ጥገኛ እንደሆኑ የገለጸው መንግሥት ውሳኔው በተለይም በሴቶች ላይ የከፋ ተጽዕኖ እንዳሳደረ ገልጿል። ኢትዮጵያ ከአጎዋ ውጪ በመሆኗ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በተለይም ሴቶች ሥራቸውን እንዳጡ የገለጸው ደብዳቤ ከመደበኛው አሰራር በተለየ ምዘና እርምጃው ካልተቀለበሰ መንግሥት ግጭት ለማቆም ሥምምነቱ ቁርጠኛ ቢሆንም እንኳ “አሜሪካ የዜጎችን ደሕንነት አደጋ ላይ መጣሏን ትቀጥላለች” በማለት አስጠንቅቋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት እና ህወሓት በፕሪቶሪያ የተፈራረሙት ግጭት የማቆም ሥምምነት ኢትዮጵያ ወደ ታገደችበት አጎዋ እንድትመለስ መንገድ ይከፍታል ተብሎ ቢጠበቅም እስካሁን አልተሳካም።ምስል SIPHIWE SIBEKO/REUTERS

የአሜሪካ ንግድ ተወካይ ቢሮ ኢትዮጵያ ወደ አጎዋ መመለሷን የሚደግፉ እና የሚቃወሙ ወገኖችን ሐሳብ በሐምሌ 2015 ባካሔደው የቪዲዮ ኮንፈረንስ አዳምጦ ዓመታዊ ምዘናውን ቢያካሒድም እስካሁን በይፋ የተላለፈ ውሳኔ የለም። የአሜሪካ የንግድ ረዳት ተወካይ የሆኑት እና የአፍሪካ ጉዳዮችን በኃላፊነት የሚመሩት ኮንስታንስ ሐሚልተን ኢትዮጵያ ወደ አጎዋ ለመመለስ ያቀረበችው ጥያቄ “እስካሁን ውሳኔ በመጠባበቅ ላይ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

የአሜሪካ ንግድ ተወካይ ቢሮ ዓመታዊ ምዘና ሞሪታኒያን ወደ አጎዋ መልሶ የኢትዮጵያን ውትወታ ቸል ቢልም ሌሎች አራት የአፍሪካ ሀገራትን ከግብይት ሥርዓቱ አግዷል። ጋቦን እና ኒዠር በመፈንቅለ-መንግሥት፤ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ እና ዩጋንዳ መንግሥታት ይፈጽሙታል በተባለ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ምክንያት በአጎዋ በኩል የነበራቸውን ዕድል በአሜሪካው ፕሬዝደንት ውሳኔ ተቀምተዋል።

አጎዋ ለአፍሪካ አገራት ምን ፈየደ?

የአሜሪካ ንግድ ተወካይ ቢሮ ውሳኔን የምትጠባበቀው ኢትዮጵያ አጎዋ በፈጠረው የግብይት ዕድል የተሻለ ተጠቃሚ ከሆኑ የአፍሪካ ሀገሮች አንዷ ናት። በጎርጎሮሳዊው 2021 ኢትዮጵያ 277 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ሸቀጥ በአጎዋ በኩል በአሜሪካ ገበያ እንደሸጠች የአሜሪካ የንግድ ኮሚሽን መረጃ ያሳያል። በመረጃው  መሠረት በዓመቱ ከፔትሮሊየም በቀር ያሉ ሸቀጦችን ለአሜሪካ ገበያ በማቅረብ አጎዋን የተሻለ ከተጠቀሙ ሀገራት ኢትዮጵያ በ15 ደረጃ ላይ ትገኛለች።

በኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ታንዛኒያ የሚገኙ የጨርቃ ጨርቅ አምራቾች ስለ አጎዋ “ጠንካራ እውቀት” እንዳላቸው የሚገልጸው ሪፖርት ከሥመ-ጥር የአሜሪካ የአልባሳት ኩባንያዎች ጋር ያላቸውን የሥራ ውል ለመጠበቅ፣ ተጨማሪ መዋዕለ ንዋይ ለመሳብ እና የገበያ ትሥሥራቸውን ለማጠናከር ጭምር እንደሚጠቀሙበት ያሳያል።

በጎርጎሮሳዊው 2021 ኢትዮጵያ 277 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ሸቀጥ በአጎዋ በኩል ያለ ቀረጥ በአሜሪካ ገበያ እንደሸጠች የአሜሪካ የንግድ ኮሚሽን መረጃ ያሳያል።ምስል Eshete Bekele Tekle/DW

የአጎዋን ዕድል በቅጡ በመጠቀም ረገድ ግን ከሁሉም የአፍሪካ ሀገራት ደቡብ አፍሪካ ቀዳሚ ናት። በጎርጎሮሳዊው 2021 ብቻ ደቡብ አፍሪካ ተሽከርካሪዎች፣ ጌጣ ጌጥ እና ብረት በአሜሪካ ገበያ በማቅረብ 2.7 ቢሊዮን ዶላር ገደማ አጋብሳለች። በአሜሪካ የንግድ ኮሚሽን ሪፖርት መሠረት ናይጄሪያ 1.4 ቢሊዮን ዶላር፣ ኬንያ 523 ሚሊዮን ዶላር ለአሜሪካ ገበያ ካቀረቡት ሸቀጥ ማግኘት ችለዋል።

በአጎዋ የተሻለ ተጠቃሚ የሆነችው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝደንት ሲሪል ራማፖሳ በመጪው 2025 የሚያበቃው አጎዋ እንዲራዘም ሲጠይቁ በምሳሌነት የጠቀሱት እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሃገራት ያለውን ፋይዳ ነው። በጁሐንስበርግ በተካሔደው እና ወደ 40 የሚሆኑ የአፍሪካ ሀገራት የንግድ ሚኒስትሮች በታደሙበት የአጎዋ 20ኛ ጉባኤ መክፈቻ ራማፖሳ ባሰሙት ንግግር አጎዋ ተጨማሪ ምርቶች በማካተት አነስተኛ እና መካከለኛ ተቋማትን ተጠቃሚ በሚያደርግ መንገድ ሊሻሻል እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ራማፖሳ “ከድፍድፍ ነዳጅ ውጪ ወደ አሜሪካ ገበያ የሚላከውን የተወሰነ የአፍሪካ ሸቀጥ በተለይ የጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ውጤቶች ተወዳዳሪነት የአጎዋ ፕሮግራም ከፍ አድርጓል” ሲሉ ተናግረዋል። “ከሌሴቶ፣ ኢትዮጵያ፣ ሞሪሽየስ፣ ማዳጋስካር እና ኬንያ የሚላከው ጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት በአስር ሺሕዎች የሚቆጠሩ የሥራ ዕድሎች መፍጠር ብቻ ሳይሆን ሀገሮቹ ለአሜሪካ ሸማቾች እምነት የሚጣልባቸው አምራቾች እንዲሆኑ አድርጓቸዋል” ሲሉ የአጎዋን ፋይዳ በጁሐንስበርግ ለተሰበሰቡ ዲፕሎማቶች እና ሚኒስትሮች ገልጸዋል።

አጎዋ ይራዘማል?

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ቢል ክሊንተን ያጸደቁት እና በባራክ ኦባማ ፊርማ ለተጨማሪ ዐሥር ዓመታት የተራዘመው አጎዋ በጎርጎሮሳዊው 2025 ያበቃል። የአፍሪካ ሀገራት የአጎዋ ተጠቃሚ ለመሆን አሜሪካ ብቃታቸውን የምትመዝንባቸው መስፈርቶች አወዛጋቢ ቢሆኑም እንደ ራማፖሳ ሁሉ በአህጉሪቱ ፖለቲከኞች ዘንድ እንዲራዘም ፍላጎት አለ። በጁሐንስበርግ በተካሔደው ጉባኤ የአፍሪካ ኅብረት የንግድ እና ኢንዱስትሪ ኮሚሽነር የሆኑት አልበርት ሙቻንጋ አጎዋ “አጎዋ ለአስር ዓመታት እንዲራዘም እንፈልጋለን” ሲሉ ተናግረዋል።

በጁሐንስበርግ የተካሔደው 20ኛ የአጎዋ ጉባኤ ከመከረባቸው ጉዳዮች አንዱ በጎርጎሮሳዊው 2025 የሚያበቃው የአፍሪካ የዕድገት እና ዕድል ድንጋጌ (African Growth and Opportunity Act) የመራዘም ዕድል ነበር።

የደቡብ አፍሪካ የንግድ ሚኒስትር ኢብራሒም ፓቴል አጎዋ በሥራ ላይ የሚቆይበት ጊዜ ከ2025 በኋላም ከተራዘመ አፍሪካ ወደ አሜሪካ የምትልከውን ሸቀጥ በእጥፍ ለማሳደግ መዘጋጀቷን ተናግረዋል። ሚኒስትሩ እንዳሉት በጉዳዩ ላይ ከአሜሪካ ጋር በሚደረገው ድርድር አፍሪካ ወጥ አቋም መያዝ ይኖርባታል። “አፍሪካ በዓለም መድረክ የሚገባትን ሚና እያገኘች ነው” ያሉት ፓቴል “ከአሜሪካ ጋር በሚደረገው ድርድር የጋራ አቋም አበጅተን በተናጠል ልዑካን እናቀርባለን” ሲሉ ተደምጠዋል።

በመጪው ዓመት ምርጫ የሚጠብቃቸው ፕሬዝደንት ጆ ባይደንን ጨምሮ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣናትም አጎዋ ሊራዘም እንደሚገባ ይስማማሉ። አጎዋ “ትዕምርታዊ ብቻ ሳይሆን ጠቃሚ እንዲሆን እንፈልጋለን” ያሉት የአሜሪካ የንግድ ተወካይ አምባሳደር ካትሪን ታይ በጉዳዩ ላይ ውሳኔ የማሳለፍ ሥልጣን የተሰጠው ኮንግረስ አሰራር ውስብስብ ቢሆንም ትኩረት እንዳገኘ በጁሐንበርግ በተካሔደው ጉባኤ ማስተማመኛ ለመስጠት ሞክረዋል። “ሁለት ዓመታት አለን” ያሉት አምባሳደር ታይ “አሁን በጥሩ ደረጃ ላይ ነን። በጉዳዩ ላይ እየተነጋገርን ነው። የኮንግረሱን ትኩረት አግኝተናል” ሲሉ ተደምጠዋል።

የአሜሪካ ሴኔት አባል የሆኑት ክሪስ ኩንስ አጎዋ ለተጨማሪ 16 ዓመታት ተራዝሞ እስከ ጎርጎሮሳዊው 2041 ሥራ ላይ እንዲቆይ የሚያደርግ ረቂቅ ሕግ አዘጋጅተዋል። ረቂቁ አጎዋን ከአፍሪካ አኅጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠና ለማስተሳሰር ጭምር ያለመ እንደሆነ ሬውተርስ ዘግቧል። በአሜሪካ ሴኔት የውጭ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት ኩንስ ያዘጋጁት ረቂቅ የደቡብ አፍሪካን የአጎዋ ተጠቃሚነት እንደገና እንዲፈተሽ መጠየቁ ግን ሌላ አወዛጋቢ ጉዳይ ነው።

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

 

 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW