ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚታየዩ የተለያዩ የፀጥታ ችግሮች መፍትሄ እያገኙ ይሆን?
ሰኞ፣ መስከረም 12 2018
መንግሥት ፀጥታን ለማስከበር ያስቀመጠው አቅጣጫ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሁለት ሳምንታት በፊት ከጸጥታ ተቋማት አመራሮች ጋር ውይይት መደረጉን ጠቅሰው "ዝርፊያ እና እገታዎችን በተጠና መንገድ ለመቆጣጠር" አቅጣጫ ስለመቀመጡ አስታወቀው ነበር።
ለመሆኑ ይህ ችግር ምን ያህል እየተፈታ ነው?
መንግሥት ለዚህ የፀጥታ ችግርእውቅና መስጠቱ ትልቅ ነገር መሆኑን የጠቀሱ አንድ የፖለቲካ ተንታኝ፤ ምርጫ በመቃረቡ ምክንያት መሰል አቋሞች መራመዳቸውን፤ ለሦስት ዓመት በላይ የዘለቀው ማገት፣ ገንዘብ መጠየቅ፣ መንገድ መዝጋት እና መሰል ችግሮች በቀላሉ ይፈታሉ ብለው እንደማያምኑም ገልፀዋል። ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች "በእጀባ" ለመንቀሳቀስ የሚገደዱበት አካባቢ ጥቂት አለመሆኑን የገለፁ አንድ የዘርፉ ባለሙያ ደግሞ እገታ እና መሠል የፀጥታ ችግሮች ተፈተዋል ማለት አንችልም" ብለዋል።
ዝርፊያ፣ እገታ እና ሥጋት ላይ የሚጥሉ የፀጥታ ችግሮች አሳሳቢነት
የኢትዮጵያ መንግሥት በመላ ሀገሪቱ "የአሻጥር፣ የከተማና የገጠር ውንብድና፣ የኮንትሮባንድ፣ የሙስና፣ ሕገ ወጥ የሰዎችና የገንዘብ ዝውውር እና የመሳሰሉ ወንጀሎችን በመከላከልና በመቆጣጠር የሕዝቡን ሰላም ማስከበር እንደሚገባ" ከጸጥታ ተቋማት አመራሮች ጋር በዓመቱ መግቢያ አካባቢ ተደረገ ከተባለ ውይይት በኋላ ተገልጿል። በወቅቱ "በተለያዩ ቦታዎች የሚደረጉ ዝርፊያዎችን፣ እገታዎችን እና መሰናክሎችን በተጠና መንገድ መቆጣጠር ይገባናል" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የፀጥታ ኃይላት "እነዚህን አካላት ከእኩይ ተግባራቸው መግታት፣ ብሎም ለሕግ ማቅረብ እንደሚገባቸው አጽንዖት ተሰጥቶታል"፣ ለዚህ ተግባርም "የየአካባቢው ማኅበረሰብ ትብብር ወሳኝ መሆኑ በውይይቱ ወቅት ተነሥቷል" ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንም "በመንግሥት ከሚፈጸሙ ሕገ ወጥ እና የዘፈቀደ እሥሮች ጎን ለጎን በታጣቂ ቡድኖች፣ ለዝርፊያ በተደራጁ ቡድኖች የሚፈጸሙ" ያላቸው እገታዎች "በነጻነት እና ሌሎች መሠረታዊ መብቶች ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ቀጥለዋል።" ሲል ማሳሰቡ ይታወሳል።
ለመሆኑ ይህ ችግር በተባለው ደረጃ የሚፈታ ይሆን? የባለሙያ አስተያየት
ለመሆኑ ይህ ችግር በተባለው ደረጃ የሚፈታ ይሆን ? አስተያየታቸውን ብቻ ለዶቼ ቬላ የገለፁ አንድ የፖለቲካ ተንታኝ ጥርጣሬ አላቸው። “በገንዘብ ሰውን ማገት በተለይ ደግሞ የጸጥታ መዋቅሩ ይሳተፍበታል በምንለው ደረጃ ይህ ወንጀል እስከዛሬ በተለይ ላለፉት ሦስት፣ አራት ዓመታት በስፋት የቆየ ነው። ስለዚህ ይህንን [ችግሩ መኖሩን] እውቅና መስጠቱ የሚበረታታ ነው ባይ ነኝ። ይመስለኛል ምርጫ እየመጣ ስለሆነ እንደ መንግሥት እየተንቀሳቀስን ነው የሚል ነገር ለመፍጠር ይመስለኛል። ነገር ግን አሁንም [ችግሩን] ይፈቱታል የሚል እምነት የለኝም።"
ከችግሩ ሰለባዎች መካከል የሀገር አቋራጭ አሽከርካሪዎች ይገኙበታል
እንዲህ ያለው የእገታ እና የዘርፉ ወንጀል በተለይ ከአዲስ አበባ ወደ ጎጃም መስመር ተደጋግሞ መፈጸሙ የተዘገበ ቢሆንም በአሽከርካሪዎችእና ተሳፋሪዎች ላይ የበረታ መሆኑን የከባድ መኪና አሸከርካሪዎች ማህበር ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ዘውዴ በተለይ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል። "ችግሩ ተፈቷል ማለት አንችልም" ሲሉም አክለዋል። "እዚያ አካባቢ [ደቡብ ጎንደር] በእጀባ ነው የሚኬደው። በእጀባ መካከል በሚከፈት ተኩስ ሾፌሮች ተጎጂ እየሆኑ ነው። በሌሎች አካባቡዎች ያሉት ነገሮች ኬላዎች ባይነሱም ግድያዎችና የመሳሰሉ ነገሮች የሉም አሁን። በአጠቃላይ ችግሩ ተፈቷል ብለን ማለት አንችም።"
መገናኛ ዐውታሮችን የተመለከተው የመንግሥት አቅጣጫ እና መሬት ላይ ያለው እውነታ በሌላ በኩል በጋዜጠኞች እና የፖለቲካ ተሳትፎ ባላቸው ግለሰቦች ላይ "ማንነታቸው በውል ያልታወቁ" በሚል እገታ፣ እሥር፣ መሰወር ይፈፀምባቸዋል። መንግሥትን ደግፈው የሚናገሩ እና የሚፅፉት ተቃውመው ከሚፅፉት ጋርም እኩል አይታዩም። ታግተው የቆዩ ሰዎች ተለቀቁ ከመባል በቀር የድርጊቱ ፈፃሚ ማን ነው? ለምን ተደረገ? ተጠያቂነቱስ የሚሉ ጉዳዮች ተዳፍነው ሲቀሩ እየተስተዋለ ነው።
መንግሥት "በማኅበራዊ ሚዲያ በኩል የሽብር ተግባር የሚፈጽሙትን ትኩረት ሰጥቶ መከታተል እንደሚገባ" ከፀጥታ አካላት መሪዎች ጋር በነበረ ውይይት ላይ አቅጣጫ ስለመቀመጡም አስቀድሞ ተነግሯል። ሂውማን ራይትስ ዎች ዛሬ ሰኞ ባወጣው መግለጫ "የኢትዮጵያ የጸጥታ ኃይሎች ከነሐሴ 2025 ጀምሮ በርካታ ጋዜጠኞችን እና የሚዲያ ባለሙያዎችን በዘፈቀደ ማሰራቸውን" ጠቅሷል። የተቋሙ የአፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር ላቲሺያ ባደር “የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ነፃ ዘገባን ለማፈን የሚያደርጓቸው አዳዲስ ጥረቶች የህዝብን የመንግሥት ቁጥጥር ለመከላከል ነው” በማለት "ባለሥልጣናቱ በጋዜጠኞች እና በመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ላይ ማነጣጠሩን ማቆም እና በሥራቸው ምክንያት በግፍ የታሰሩትን በአስቸኳይ መፍታት አለባቸው።" ሲሉ ጥሪ አድርገዋል።
የጤና ባለሙያዎችን የመብት ጥያቄ የተመለከተ ዘገባ በመሥራታቸው ታሥረው የሚገኙ የሸገር ሬዲዮ ጋዜጠኞች የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በ50 ሺህ ብር ዋስትና እንዲለቀቁ ትዕዛዝ ቢሰጥም ይግባኝ ተጠይቆባቸው ለ20 ቀናት በእሥር ላይ መሆናቸውን ተቋሙ ማሳያ ጠቅሷል። የጸጥታ ተቋማት ውይይት እና የሰሞኑ የወታደራዊ መኮንኖች የማዕረግ ዕድገት ርእሠ ብሔር ታዬ አፅቀ ሥላሴ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት 4 ሙሉ ጄነራልነትን ጨምሮ ቅዳሜ ዕለት ለ66 ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ማዕረግ ከሰጡ በኋላ "የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሀገሪቱን ከየትኛውም ትንኮሳ ለመከላከል በአስተማማኝ ኹኔታ በመደራጀት እና በመዘመን ላይ የሚገኝ ተቋም ነው" ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዓመቱ መግቢያ ላይ ባወጡት መግለጫ "የጸጥታ ተቋሞቻችን የሀገሪቱን ሉዓላዊነት፣ ነጻነት፣ ዳር ድንበር፣ ሰላምና ደኅንነት" ለማስከበር በሚችሉበት "ዐቅም እና ዐቋም ላይ እንደሚገኙ ተረጋግጧል" ማለታቸው ይታወሳል።
ሰለሞን ሙጬ
አዜብ ታደሰ
ታምራት ነገራ