ኢትዮጵያ ውስጥ ለስደተኞች የሚሰጠው ድጋፍ ብርቱ አደጋ አጋጥሞታል መባሉ
ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 11 2018
ኢትዮጵያ ውስጥ ለስደተኞች የሚሰጠው ድጋፍ ብርቱ አደጋ አጋጥሞታል መባሉ
ኢትዮጵያ ውስጥ ለተጠለሉ ስደተኞች የሚሰጠው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ የውድቀት አፋፍ ላይ ደርሷል ሲሉ የሰብአዊ ድጋፉን የሚያስተባብሩት ተቋማት ይፋ አደረጉ።
የኢትዮጵያ የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት እና ሦስት የተባበሩት መንግሥታት ተቋማት ትናንት ምሽት በጋራ ባወጡት መግለጫ "አፋጣኝ የገንዘብ ድጋፍ ካልተደረገ ከ1.1 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ስደተኞች የሚቀርበው የምግብ፣ የውኃ፣ የጤና አጠባበቅን ጨምሮ አስፈላጊ የሕይወት አድን አገልግሎት በሳምንታት ውስጥ ይቆማል።"
የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን የኢትዮጵያ ተወካይ "ያጋጠመን ኹኔታ ታይቶ የማይታወቅ እና በጣም አስደንጋጭ ነው" ማለታቸው በመግለጫው ተጠቅሷል።
ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው በስደተኞች ዙሪያ የሚሠሩ አንድ ባለሙያ እንደሚሉት ኹኔታው በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የእርዳታ አቅርቦት እጥረት ውጤት ነው።
የዚህ አጣብቂኝ መነሻው ምንድን ነው?
የኢትዮጵያ መንግሥት የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት፣ የተባበሩት ማንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR)፣ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኤጀንሲ እና የአለም ምግብ መርሐ ግብር (WFP) ያወጡት የጋራ መግለጫ "በኢትዮጵያ ያለው የስደተኞች ምላሽ ወደ ውድቀት አፋፍ ላይ ደርሷል።" ሲል ደምድሟል።
በአፍሪካ ሁለተኛዋ ትልቅ የስደተኞች አስተናጋጅ ሀገር የሆነችው ኢትዮጵያ በሱዳን እና በደቡብ ሱዳን ግጭቶች እንዲሁም በሶማሊያ ድርቅ ምክንያት የምታስተናግዳቸው የፍልሰተኞች ቁጥር ቢጨምርም የእርዳታ ድርጅቶች ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት ስለገጠማቸው የአስቸኳይ ጊዜ የእርዳታ አቅርቦቶች በ70 በመቶ እንዲቀንሱ አስገድዷቸዋል ተብሏል።
ኢትዮጵያ ስደተኞችን ለመጠበቅ የገባችውን ቃል ማክበሯን
የገለፁት የኢትዮጵያ የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ጠይባ ሀሰን "ይህን ከባድ ኃላፊነት መንግሥት ብቻውን ሊሸከም አይችልም" ሲሉ ጫናው ሊቋቋሙት የማይችል እየሆነ በመምጣቱ "ፈጣን ዓለም አቀፍ ድጋፍ የግድ አስፈላጊ ነው" ብለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን የኢትዮጵያ ተወካይ በፊናቸው "ያጋጠመን ኹኔታ ታይቶ የማይታወቅ እና በጣም አስደንጋጭ ነው" ሲሉ አሳስበዋል። ይህን መሰሉ አጣብቂኝ መነሻው ምን እንደሆነ የጠየቅናቸው "ንጋት ግሎባል ኢኒሽየቲቭ" የሚባል በዘርፉ የተሰማራ ድርጅት መሥራች እና ኃላፊ አቶ ዳንኤል መለሰ የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድጋፍ መቀነስ ዋነኛ ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል።
በስደተኞች ላይ የተጋረጠው የምግብ እጥረት እና የረሃብ ሥጋት
በአሁኑ ጊዜ ሙሉ የምግብ አቅርቦት ወይም ራሽን የሚያገኙት 70,000 አዲስ የመጡ ስደተኞች ብቻ ናቸው ያሉት መግለጫውን ያወጡት አካላት "የጉዳቱ ተጽእኖ ቀድሞውኑ አስከፊ" መሆኑንና በጥቅምት ወር የዓለም የምግብ ፕሮግራም ለ780,000 ስደተኞች የሰጠውን የምግብ ድጋፍ ከመደበኛው ወደ 40 በመቶ ለመቀነስ መገደዱን አስታውቀዋል። እናም "ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት ሥራዎችን ለማስቀጠል 90 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በአስቸኳይ እየጠየቅን ነው" ሲሉ የዓለም የምግብ መርሐ ግብር ተወካይ እና የሀገር ውስጥ የበላይ ኃላፊ ዝላታን ሚሊሲች ተናግረዋል። "አዲስ የገንዘብ ድጋፍ ወዲያውኑ ካላገኘን፣ በሚቀጥሉት ወራት ለስደተኞች የሚሰጠውን የምግብ እርዳታ ሙሉ በሙሉ ለማቆም ልንገደድ እንችላለን፤ ይህም የምግብ እጥረት እና ረሃብን ያባብሳል።" ሲሉም ተናግረዋል።
በገንዘብ እጥረት ምክንያት የተከሰተው የድጋፍ ቅነሳእየተገባደደ ባለው የግሪጎሪያኑ 2025 በአራስ ጨቅላዎች እና ከአንድ አመት በታች በሆኑ ሕጻናት መካከል ያልፕውን የሞት መጠን ወደ 4.7 በመቶ ከፍ ስለማድረጉ ተጠቅሷል። አቶ ዳንኤል መለሰ እንደሚሉት ችግሩ ከገንዘብ ድጋፍ መቀነስም የተሻገረ ነው።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያን ጨምሮ የኬንያ፣ የሞዛምቢክ እና የዛምቢያ ብሔራዊ የሰብአዊ መብት ተቋማት የስደት መተላለፊያ የሆኑ የደቡባዊ ሀገራት "መብትን መሰረት ያደረገ" የስደት ፖሊሲዎችን እንዲከተሉ በዚሁ ሳምንት በጋራ ባወጡት መግለጫ ጠይቀዋል።
መግለጫው ደቡባዊ የፍልሰት መስመር በሚባሉት ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ሶማሊያ አልፎ እስከ ደቡብ አፍሪካ እና ቦትስዋና ድረስ ያለው መንገድ የበለጠ አደገኛ እየሆነመጥቷል ማለት ነው ያሉት የንጋት ግሎባል ኢኒሽየቲቭ መሥራች እና ኃላፊ አቶ ዳንኤል መለሰ፣ ፍልሰተኞች በምንም መንገድ የተንቀሳቀሱ ይሁን በገቡበት ሀገር መብታቸው ሊጠበቅ ይገባል የሚል እና መንግሥታት በትብብር መሥራታቸው የግድ የሆነበት ጊዜ ላይ ስለመደረሱ ጠቋሚ ነው ብለዋል።
ሰለሞን ሙጬ
ታምራት ዲንሳ