ኢትዮጵያ ውስጥ ከሰሞኑ ከበድ ባለ መጠን እየጣለ ያለው ዝናብ ያሰጋልን?
ቅዳሜ፣ መስከረም 3 2018
ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም በመዲናዋ አዲስ አበባ ከሰሞኑ ከበድ ያለ ዝናብ እየተስተዋለ ነው፡፡ ትናንት መስከረም 02 ቀን 2018 ዓ.ም. በመዲናዋ አንዳንድ ስፍራዎች ቅጽበታዊ ጎርፍ ተከስቶ ተስተውሏልም፡፡ክረምቱ ጋር ተያይዞ እስከ መስከረም አጋማሽ ከበድ ያለ ዝናብ ይጠበቃል የሚለው ብሔራዊ ሜትሮሎጂ ግን የከፋ የአየር ጠባይ ይከሰታል የሚል ትንቢያ አለመኖሩን አስገንዝቧል፡፡
በተለምዶ የወርሃ ክረምቱ ዝናብ እየቀነሰ ይመጣል ተብሎ በሚጠበቅበት ባሁን ወቅት ትናንት መስከረም 02 ቀን 2018 ዓ.ም. ከሰዓቱን ዘጠኝ ሰዓት ግድም አዲስ አበባ ውስጥ በጣለው ከበድ ያለ ዝናብ አንድ አንዳ የከተማዋ አከባቢዎች ላይ ቅጽበታዊ ጎርፍ ተከስቶ ተስተውሏል፡፡ በርካታ የከተማዋ አከባቢዎች ላይ የአደጋ ጊዜ ተሸከርካሪዎችም ጉዳዩን ለመቆጣጠር ስባትሉ ተስተውሏል፡፡ የትናንትና እለቱ ጎርፍ ከጎበኛቸው ከነዚህ የከተማዋ አከባቢዎች ኮተቤ፣ ላምበረት፣ ወሰን ተብሎ የሚጠሩ አከባቢዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በተለይም በለሚ ኩራ ክፍለከተማ ወሰን ተብሎ በሚጠራ አከባቢ ተፈጥሯዊ ማፋሰሻውን ሰብሮ የወጣው ከባድ ጎርፍ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ በመግባት ነዋሪዎችን ስፈትን ታይቷል፡፡
ዶይቼ ቬለ ቅጽበታዊ ጎርፉ የተስተዋለባቸውን የተወሰኑ የመዲናዋ አከባቢዎችን ብመለከትም በዚህ የጎርፍ አደጋ ስለደረሰው ጉዳት አላረጋገጠም፡፡ ለአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስራ አመራር ኮሚሽን ህዝብ ግንኙነት ጥያቄውን አቅርበን ለማጣራትም ያደረግነው ጥረት ለዛሬ አልሰመረም፡፡
የክረምት ወቅት እየተሰናበተ ባለበት ባሁን ወቅት የዝናብ መጠኑ ጠንከር እያለ መምጣቱስ የተጠበቀ ነው ወይ በሚል ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት የትንቢያና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ዳይሬክተር ዶ/ር አሳመምነው ተሾመ ጥያቄ አቅርበናል፡፡ “ከሰሞኑ አዲስ አበባን ጨምሮ በአገራችን የተለያዩ አከባቢዎች እየተስተዋለ ያለው ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ በሚቀጥሉት አስር ቀናት ግድም ቀጣይነት ይኖራቸዋል” ያሉን ባለሙያው፤ መደበኛ የክረምቱ ዝናብ አወጣት ከወትሮው በተለዬ በምዕራብ፣ በደቡብ ምዕራብ እና በመካከለኛው የአገሪቱ አከባቢዎች እንደምዘገይ አንስተወል፡፡ የብሔራዊ ሜትሮሎጂው ትንቢያ እንዳመላከተውም ከደቡባዊ የህንድ ውቅያኖስ የሚነሳው እርጥበታማ የአየር ሁኔታ ወደ ኢትዮጵያ ዘልቆ በመግባት ከፍተኛ የክረምቱ ዝናብ ቆይታ እስከ መስከረም15-20 ድረስ ልዘልቅ እንደምችልም ተጠቁሟል፡፡
አሁን የምንገኝበት መስከረም ወር የክረምቱ የመጨረሻ ወር መሆኑን ያስታወሱት ዶ/ር አሳምነው፤ በኢትዮጵያ ዋነኛ የክረምት ወቅት በሆነው ከሰኔ እስከ መስከረም ባሉት ወራት አብዛኛው የአገሪቱ አከባቢዎች ከመደበኛ እስከ ከፍተኛ መጠን ያለውን ዝናብ አስተናግደዋል፡፡ “ከአመታዊው ዝናብ ከሰኔ እስከ መስከረም ባለው ወቅት እንደ አገር ከዓመታዊ የዝናብ መጠን 85 በመቶ ያህሉን የሚስተዋልበት የክረምት ወቅት ነው” የሚሉት የሜትሮሎጂ ባለሙው ሚዚያ አከባቢ በደቡብ እና ደቡብ ምዕራብ አከባቢ የጀመረው
የክረምቱ የዝናብ ሁኔታ በሂደትም ሰሜናዊ፣ ማዕከላዊ እና ምዕራብ የአገሪቱ አከባቢዎች ላይ መስፋፋቱ የሚጠበቅና መደበኛ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ ይህ የዝናቡ አወጣጥ ደግሞ ከሰሜን ምስራቅ፣ ሰሜን፣ ሰሜን ምዕራብ፣ ምዕራብ እና ደቡብ ምዕራብ አከባቢዎች ላይ እያለ እስከ መስከረም 17 ጀምሮ መደበኛ ጊዜውን ጠብቆ እንደሚወጣ አስረድተዋል፡፡
ከሰሞኑ አዲስ አበባ ውስጥ የተስተዋለው ከበድ ያለው ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ በቀጣይ ቀናት ስጋትን ይደቅን ይሆን በሚል የተጠየቁት ባለሙው ዶ/ር አሳምነው ተሾመ፤ “ከበድ ብለው በተለያዩ የአገሪቱ አከባቢዎች የሚስተዋለው ዝናብ ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊያስከትል ብችልም ያን ያህል አስጊ የሆነ የአየር ሁኔታ ግን እንደማይኖር” ተናገግረዋል፡፡ ኢንስቲትዩቱ በእየለቱ የሚስተዋሉትን የአየር ሁኔታ ትንቢን እንደ ውሃና መስኖ እንዲሁም አደጋ ስጋት አመራር ካሉ ተቋማት ጋር በቅንጅት እንደምሰራም ነው ያመለከተው፡፡
ስዩም ጌቱ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ፀሀይ ጫኔ