ኢትዮጵያ የመረጠችው የሊብራል ኢኮኖሚ ሥርዓት ውጤታማ እንዲሆን የሚያስችል ከባቢ አለ?
ረቡዕ፣ የካቲት 5 2017
የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጂዮርጂየቫ አዲስ አበባን ሲጎበኙ የኢትዮጵያ መንግሥት ተግባራዊ እያደረገ የሚገኘው የኤኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር “ፈታኝ” ቢሆንም “ከፍተኛ ጠቀሜታ” እንደሚኖረው ተናግረዋል። የኤኮኖሚ ማሻሻያውን በ3.4 ቢሊዮን ዶላር ብድር የሚደግፈውን አበዳሪ ተቋም የሚመሩት የ71 ዓመቷ ኤኮኖሚስት የኢትዮጵያ የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ በቅርቡ ሊጠናቀቅ እንደሚችል ፍንጭ ሰጥተዋል።
“በዕዳ አከፋፈል ማሻሻያ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን” ያሉት ክሪስታሊና ጂዮርጂየቫ “ከኢትዮጵያ አበዳሪዎች ጋር በሚኖረኝ ግንኙነት ትልቅ ትኩረት ከምሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ መሆኑን መናገር እችላለሁ” ሲሉ ተደምጠዋል።
ኢትዮጵያ በቡድን 20 ሃገራት የጋራ ማዕቀፍ በሐምሌ 2013 የጠየቀችው የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ “የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ የደረሰው” መንግሥት የብር የመግዛት አቅምን በኃይል ያዳከመ የውጪ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት ለውጥ ካደረገ በኋላ ነው። የመዋዕለ-ንዋይ አማካሪው አቶ ያሬድ ኃይለመስቀል የውጪ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት ለውጥ የኤኮኖሚ ማሻሻያው “የመጨረሻ እርምጃ” ሊሆን ይገባ ነበር የሚል አቋም አላቸው።
እርምጃው ተግባራዊ ሲሆን የኢትዮጵያን ዕዳ “ከአቅም በላይ አድርጎታል” የሚሉት አቶ ያሬድ መንግሥት ዕዳ ለመክፈል በቀረጥ መልክ የሚሰበስበው ገቢ መጠን ላይ የተከሰተውን ልዩነት ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል። አቶ ያሬድ “የመገበያያ ገንዘቡን ዋጋ በማሳጣት ብቻ ኢትዮጵያ ዕዳዋን መክፈል የማትችልበት ጣጣ ውስጥ ነው የከተቷት” ሲሉ ይተቻሉ።
መንግሥት ሐምሌ 22 ቀን 2016 ተግባራዊ ካደረገው የውጪ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት ለውጥ ወዲህ ብር ከዶላር አኳያ ያለው የምንዛሪ ተመን በ125% ገደማ ተዳክሟል። የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት “ሀገር በቀል” ብለው የሚያሞካሹት የኤኮኖሚ ማሻሻያ መንግሥት በቀረጥ የሚሰበስበውን ገቢ እንዲጨምር እና ነዳጅን ለመሳሰሉ ሸቀጦች የሚያደርገውን ድጎማ በሒደት እንዲያቆም የሚያስገድድ ጭምር ነው።
ውሳኔዎቹ ቀድሞም ከፍተኛ ከነበረው የዋጋ ግሽበት ጋር ተደማምረው የሸማቹን አቅም ቢፈታተኑም ማሻሻያውን የሚደጉመው የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ኢትዮጵያውያን ታግሰው ፍሬውን እንዲጠብቁ ሰብከዋል።
“ሰዎች የተወሰነ ትዕግሥት እንዲኖራቸው እጠይቃለሁ። ቤተሰቦቻችሁ አኗኗራቸው እንዲሻሻል እየፈለጉ መታገስ ቀላል እንዳልሆነ አውቃለሁ” ያሉት ክርስታሊና ጂዮርጂየቫ “ኢትዮጵያ የጀመረችው ማሻሻያ መርሐ-ግብር ከባድ እና ጊዜ የሚወስድ ነው። ነገር ግን ከፍተኛ ለውጥ ያመጣል፤ አንዳንዶቹ [ለውጦች] መጥተዋል። ተጨማሪ ብዙ ይመጣል” ሲሉ ተደምጠዋል።
“ከኢትዮጵያ ኅዳሴ” ወደ “ኢትዮጵያ ብልጽግና”
የውጪ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት ላይ የተደረገው ለውጥ “ኢትዮጵያ በዘመናዊ ታሪኳ ከየትኛውም ጊዜ በላይ አሁን የበለጠ ወደ ሊብራል የኢኮኖሚ ሥርዓት ያዘነበለችበት” ለመሆኑ ማሳያ እንደሆነ በብሮኪንግስ ኢንስቲትዩት የዓለም አቀፍ ኤኮኖሚ እና ልማት ፕሮግራም ተመራማሪው ዶክተር አዲሱ ላሽተው ያምናሉ። ወደ ሊብራል ኤኮኖሚ ሲደረግ በሚታየው ሽግግር መንግሥት ሐብት በማከፋፈል ረገድ የነበረውን ቀጥተኛ ቁጥጥር በመተው ለገበያ አሳልፎ እየሰጠ ነው።
መለስ ዜናዊ እና ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በተከታታይ በጠቅላይ ሚኒስትርነት የመሩት መንግሥት ገበያውን ለዓለም አቀፍ ኩባንያዎች እንዲከፍት ከአይኤምኤፍ እና ከዓለም ባንክ በተደጋጋሚ ሲቀርብ የነበረውን ጥሪ ሳይቀበል ቆይቷል። የጤና ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች እና መንገድ የመሳሰሉ መሠረት ልማቶች በማስፋፋት የተሳካለት “ልማታዊ መንግሥት” የስኳር እና የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካዎች ለመገንባት ሲሞክር ግን አልሆነለትም።
የጅምላ ንግድ ግብይትን ለማዘመን “አለ በጅምላ” በተባለ ኩባንያ ሞክሮ ከስሯል። በፈጣን ኤኮኖሚያዊ ዕድገት ስሟ ተደጋግሞ የተነሳው ኢትዮጵያ በዋናነት በመንግሥት የልማት ድርጅቶች አባካኝነት ከፍተኛ ዕዳ ተሸክማ ቀርታለች። ለአምራቾች የተዘጋጁት የኢንዱስትሪ ፓርኮች እና የአበባ እርሻ እንደተጠበቀው ኢትዮጵያውያን ወጣቶች የሚፈልጉትን አጥጋቢ የሥራ ዕድል አልፈጠሩም።
“ብልጽግና” የኢትዮጵያ መዳረሻ እንደሆነ ደጋግመው የሚናገሩት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ተግባራዊ ባደረጋቸው የኤኮኖሚ ማሻሻያዎች የሀገሪቱ ገበያ ወለል ብሎ እየተከፈተ ነው። ባለፉት ዓመታት ተግባራዊ የተደረጉት ፖሊሲዎች መንግሥት በገበያ ወደሚመራ የምዕራቡ ሊብራል ኤኮኖሚ እንዳዘነበለ የሚጠቁሙ መሆናቸውን በዓለም አቀፍ ልማት ሥራ ላይ የተሠማሩት አቶ ዮሐንስ አሰፋ ይስማማሉ።
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ (ECX) ሲመሠረት በጥብቅና ሙያቸው የተሳተፉት አቶ ዮሐንስ የባንክ ሥራ ለውጪ ባለወረቶች መከፈት እና የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ መልሶ መቋቋምን በምሳሌነት ይጠቅሳሉ። ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት 3.4 ቢሊዮን ዶላር ለማበደር እና የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ ለማካሔድ ያቀረባቸው ቅድመ-ሁኔታዎችም መንግሥት ገበያውን ለግሉ ዘርፍ የበለጠ እንዲከፍት ግፊት የሚያሳድሩ ናቸው።
መንግሥት እና ገበያ
“ሶሻሊዝም ማንንም አልጠቀመም። ሶሻሊዝም ድሕነት ብቻ ነው ያመጣው” የሚሉት አቶ ዮሐንስ ኢትዮጵያ ወደ ሊብራል የኤኮኖሚ ሥርዓት ፊቷን ማዞሯ “ጥሩ ነገር ነው” የሚል አቋም አላቸው። ነገር ግን “ልቅ የሆነ የምዕራቡ አይነት ሊብራል ኤኮኖሚ ሆኖ ተገቢው ቁጥጥር ከሌለው እሱም ችግር ሊያመጣ ይችላል” ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።
የኢትዮጵያ መንግሥት የተከተለው እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የሚደግፈው የኤኮኖሚ አካሔድ ከኢሕአዴግ የልማታዊ መንግሥት ሞዴል የተፋታ ነው። ይሁንና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “መንግሥት የገበያ ጉድለትን ለማረም ጣልቃ ከመግባት በዘለለ፤ ገበያውን የመፍጠር እና የማጠናከር ሚና ሊኖረው ይገባል” የሚል አቋም ያራምዳሉ።
መንግሥት በመሬት ቁጥጥር፣ የባንክ እና የቴሌኮምዩንኬሽንን ጨምሮ በባለቤትነት በሚያስተዳድራቸው ኩባንያዎች በኩል በገበያው ያለው ሚና እጅግ ከፍተኛ ነው። “በኢትዮጵያ የሊብራል ኤኮኖሚ ለመፍጠር የመንግሥት ቁጥጥር ይቀንሳል ብዬ አላስብም። ምክንያቱም የፖለቲካ አይዲዮሎጂው አይፈቅድም” ሲሉ የመዋዕለ-ንዋይ አማካሪው አቶ ያሬድ ኃይለማርያም ይናገራሉ።
የግለሰቦች መብት እና የንብረት ባለቤትነትን በመሳሰሉ የሊብራል ፖለቲካል ኤኮኖሚ ቁልፍ ምሰሶዎች የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ቢመዘን ፈተናውን ያልፋል ብሎ መናገር ይቸግራል።
በሊብራል ኤኮኖሚ ውስጥ ግንባር ቀደም ሚና ሊኖረው ይገባል የሚባለው የግሉ ዘርፍ አቅም ሌላው ፈተና ነው። አቶ ዮሐንስ “የግሉ ዘርፍ ዝግጁ ነው” የሚል አቋም ቢኖራቸውም “የአቅም ችግር ሊኖር” እንደሚችል አላጡትም። “ፋይናንሲንግ ለግሉ ዘርፍ ኦክስጅን ማለት ነው…መተንፈሻ…ያለ ፋይናንሲንግ ምንም መንቀሳቀስ አትችልም” የሚሉት አቶ ዮሐንስ በፋይናንስ አቅርቦት ረገድ መንግሥት ቅድሚያውን ወስዶ መቆየቱ የግሉን ዘርፍ ለችግር እንደዳረገ ተናግረዋል።
የመሬት ባለቤትነት ነገር
በኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት “መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ የመንግሥትና የሕዝብ ሀብት ነው።” ለኢትዮጵያ ኤኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሚባለውን ግብርና ለማዘመን “የመሬት ባለቤትነት” ማሻሻያ እንደሚያስፈልገው አቶ ዮሐንስ ይናገራሉ። የመሬት ባለቤትነትን የተመለከተ ማሻሻያ ቢደረግ “የተወሰነ መፈናቀል ይኖራል” የሚሉት አቶ ዮሐንስ “ነገር ግን ውጤታማ አሠራር ሲዘረጋ፣ ኢኖቬሽን ሲኖር አንድ ታታሪ ገበሬ ሰነፉን ገበሬ ቀጥሮ ያሰራዋል። ታታሪው ገበሬ የበለጠ ሞደርናይዝ ያደርጋል፤ የበለጠ ኢንቨስት ያደርጋል፤ ሜካናይዜሽን ይመጣል” ሲሉ ይሞግታሉ።
“የመሬት ፖሊሲ ካልተቀየረ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ምንም ተጨማሪ ኤክስፖርት የሚደረግ ነገር የለም” የሚሉት አቶ ያሬድም በመሬት ባለቤትነት ረገድ የፖሊሲ ለውጥ እንደሚያስፈልግ ይስማማሉ። ከመሬት ፖሊሲ ባሻገር ግን የግሉ ዘርፍ በኤኮኖሚው ውስጥ ግንባር ቀደም ሚና እንዲጫወት ካስፈለገ ሀገሪቱ በርካታ የሕግ እና የአሠራር ማሻሻያዎች ያስፈልጓታል። ከስድስት አስርት ዓመታት በላይ ሥራ ላይ የቆየው የኢትዮጵያ የንግድ ሕግ የተሻሻለው እንኳ በመጋቢት 2013 ነበር።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ “ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው ማሻሻያ ፈጣን የኤኮኖሚ ዕድገት እና የሥራ ዕድል በመፍጠር በስተመጨረሻ ለሕዝባችን ከፍተኛ ጥቅም እንደሚያስገኝ በጽኑ እናምናለን” ሲሉ ተናግረዋል። የገንዘብ ሚኒስትሩ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ጋር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “ግቦቻችን ሙሉ በሙሉ እስኪሳኩ ማሻሻያው በትክክል ተግባራዊ መደረጉን ለማረጋገጥ ጤናማ የኤኮኖሚያዊ አስተዳደር ለመከተል ቁርጠኞች ነን” ሲሉ ተደምጠዋል።
አቶ ዮሐንስ አሰፋ በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ድጋፍ ተግባራዊ የሚደረገው ማሻሻያ “ጥሩ እየሔደ ነው” የሚል ዕምነት ቢኖራቸውም ውጤቱን ለማየት እስከ 10 ዓመት መጠበቅ ሊያስፈልግ እንደሚችል ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ይሁንና “እነዚህ ማሻሻያዎች ለረዥም ጊዜ የኤኮኖሚ ጤናማነት በጣም ጠቃሚ ናቸው” ሲሉ አስረድተዋል።
ዓለም አቀፍ ተቋማት ብድር እና እርዳታ ለመስጠት የሚያቀርቧቸው ቅድመ-ሁኔታዎች አቶ ያሬድን ያሰጓቸዋል። መሰል የኤኮኖሚ መዋቅራዊ ማሻሻያዎች እንደ ጋና በመሰሉ የአፍሪካ ሀገራት ተሞክረው መክሸፋቸውን የሚያስታውሱት አቶ ያሬድ ለኢትዮጵያ ፈታኝ እንሚሆን ያስጠነቅቃሉ።
“ሊበራላይዝ ማድረጋችን በመርኅ ደረጃ በጎ ቢሆንም አሁን ባለው ሁኔታ ግን ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያን የመጨረሻው ልጓም ውስጥ ነው የገባችው” የሚሉት አቶ ያሬድ “ካሁን ወዲያ ከአይኤምኤፍ እና ከዓለም ባንክ ፕሮግራም ውጪ ምንም ነገር መሥራት አትችልም” ሲሉ ተናግረዋል።
እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሠ