1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ የምትሻውን አንገብጋቢ የውጭ እርዳታ እና ብድር መቼ ታገኛለች?

Eshete Bekele
ረቡዕ፣ መጋቢት 13 2015

የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት መስሪያ ቤቶች የ2016ን በጀት ሲያዘጋጁ "ከውጭ ሊገኝ የሚችልን ዕርዳታ እና ብድር በማሰብ" ሊሆን እንደማይገባ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ አሳስበዋል። የፕሪቶሪያ የሰላም ሥምምነት እና የሽግግር ፍትኅ አተገባበር ምዕራባውያን የከለከሉትን እርዳታ እና ብድር ለመፍቀድ ቅድመ-ሁኔታ አድርገዋል።

Äthiopien | Permierminister Abiy Ahmed und Anthony Blinken
ምስል Fana Broadcasting Corporate S.C

ኢትዮጵያ የምትሻውን አንገብጋቢ የውጭ እርዳታ እና ብድር መቼ ታገኛለች?

This browser does not support the audio element.

በ2016 በጀት ዓመት የኢትዮጵያ መንግሥት ትኩረት ከሚያደርግባቸው ጉዳዮች መካከል "በወቅቱ ብድር መክፈል" አንዱ ይሆናል። የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ ከፌድራል ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች ጋር ባደረጉት ውይይት 2016 "አዲስ የካፒታል ፕሮጀክቶች የማይኖሩበት" እንደሚሆን ተናግረዋል።

ባለፈው መጋቢት 6 ቀን 2015 የተካሔደውን ውይይት አስመልክቶ የገንዘብ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ አቶ አሕመድ በሚቀጥለው ዓመት "በመደበኛ በጀት ላይ ከፍተኛ ማስተካከያ እና ቁጥጥር" እንደሚደረግ መናገራቸውን አስታውቋል። በመግለጫው መሠረት የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት መስሪያ ቤቶች የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ሲያዘጋጁ "ከውጭ ሊገኝ የሚችልን ዕርዳታ እና ብድር በማሰብ ሳይሆን" በመንግሥት እጅ "ላይ ባለ ሀብት" ሊሆን እንሚገባ አቶ አሕመድ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።

የውጭ እርዳታ እና ብድር ከጎርጎሮሳዊው 2021/2022 የኢትዮጵያ በጀት 22 በመቶ ድርሻ እንደነበረው የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ ያስታውሳሉ። "አምና ግን በአገሪቱ በነበረው የፖለቲካ ሁኔታ እና ጦርነት ከውጪ የምናገኘው ዕርዳታ እና ብድር በጣም ስለቀነሰ ወደ 10 በመቶ ወርዷል። ብድር እና እርዳታው ወደ 81 ቢሊዮን ብር አካባቢ ወርዷል" ሲሉ ዶክተር አብዱልመናን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት የ2015 በጀት ከ230 ቢሊዮን ብር በላይ በላይ የጎደለው ነበር። ለዚህም የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የአገሪቱን ኤኮኖሚ በማዳከሙ፣ ጦርነቱ በተሔደባቸው አካባቢዎች ያሉ የኤኮኖሚ ተቋማት በመውደማቸው አሊያም እንቅስቃሴ በማቋማቸው 40 ቢሊዮን ብር የሚደርስ የታክስ ገቢ ሳይሰበሰብ መቅረቱ አንደኛው ምክንያት ነው።

በዓመቱ "ዋና ዋና የልማት አጋሮች" የሚሰጡትን የበጀት ድጋፍ ማቆማቸው በ2015 በጀት ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድሯል። በእነዚህ ብርቱ ችግሮች የተከሰተው የበጀት ጉድለት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ብሔራዊ ባንክን ጨምሮ ፊቱን ወደ አገር ውስጥ ምንጮች እንዲያዞር አስገድደውት ነበር።

የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት መስሪያ ቤቶች የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ሲያዘጋጁ "ከውጭ ሊገኝ የሚችልን ዕርዳታ እና ብድር በማሰብ ሳይሆን" በመንግሥት እጅ "ላይ ባለ ሀብት" ሊሆን እንደሚገባ አቶ አሕመድ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።ምስል Ethiopian Investment Holdings (EHI)

በዓመቱ "መንግሥት ከታክስ ቀጥሎ ትልቁ የገቢ ምንጭ ያደረገው የአገር ውስጥ ብድርን ነው። ከብሔራዊ ባንክ መበደር ማለት ብር ማተም ማለት ነው" የሚሉት ዶክተር አብዱልመናን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በጥቅምት ወር ባንኮች ከሚሰጡት ብድር በ20 በመቶ ከመንግሥት ትሬዠሪ የ5 ዓመት ቦንድ እንዲገዙ ያወጣው መመሪያ "የኢትዮጵያ መንግሥት የበጀት ጉድለቱን ለመሙላት ምን ያህል የገንዘብ ችግር እንደገጠመው" የሚያሳይ እንደሆነ ያስረዳሉ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ከምዕራባውያኑ የሚያገኘውን ብድር እና እርዳታ እንዲያጣ ምክንያት የሆነው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በፕሪቶሪያ በተፈረመው በቋሚነት ግጭት የማቆም ሥምምነት ጋብ ብሎ የሻከረው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የመሻሻል ምልክቶች ታይተዋል። ጦርነቱ እንዲቆም ከፍተኛ ግፊት ስታደርግ የቆየችው እና ለፕሪቶሪያው ሥምምነት መፈረም ከፍ ያለ ሚና ያላት አሜሪካ ለኢትዮጵያ መንግሥት የከለከለችውን የገንዘብ ዕርዳታ ለመስጠት እያጤነች መሆኑ ተሰምቷል።

የአሜሪካው ፎሬይን ፖሊሲ መጽሔት እንደዘገበው ይኸ ጉዳይ የፕሬዝደንት ጆ ባይደን አስተዳደር ባለሥልጣናትን ለሁለት የከፈለ ነው። በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ሞሊ ፊ እና በመሥሪያ ቤቱ የፖለቲካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ቪክቶሪያ ኑላንድን የመሳሰሉ ከፍተኛ ዲፕሎማቶች በቋሚነት ግጭት የማቆም ሥምምነት ከተፈረመ ወዲህ አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ወደነበረበት መመለስ አለባት የሚል አቋም እንዳላቸው ፎሬይን ፖሊሲ ዘግቧል። እነዚህ ዲፕሎማቶች አሜሪካ በአፍሪካ ያላትን ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ተደማጭነት ለማጠናከር የሻከረውን የአዲስ አበባ እና ዋሽንግተን ግንኙነት ማደስ አስፈላጊ ነው ብለው ያምናሉ።

የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ በውድቀት አፋፍ ላይ ይገኛል የሚል አቋም ያላቸው እነዚህ ዲፕሎማቶች መዳኛው ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅትን ከመሳሰሉ ተቋማት የሚሰጥ ብድር እና የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ እንደሆነ ይሞግታሉ። በፎሬይን ፖሊሲ ዘገባ መሠረት የደቡብ አፍሪካው ሥምምነት ከተፈረመ በኋላ የኢትዮጵያን መንግሥት እጅግ አንገብጋቢውን ኤኮኖሚያዊ ድጋፍ መከልከል የሥምምነቱን ተግባራዊነት ግፋ ሲልም የመላ አገሪቱን መረጋጋት የሚፈታተን ይሆናል የሚል ሥጋት ከእነ ሞሊ ፊ ዘንድ አለ።

ጦርነቱ እንዲቆም ከፍተኛ ግፊት ስታደርግ የቆየችው እና ለፕሪቶሪያው ሥምምነት መፈረም ከፍ ያለ ሚና ያላት አሜሪካ ለኢትዮጵያ መንግሥት የከለከለችውን የገንዘብ ዕርዳታ ለመስጠት እያጤነች መሆኑ ተሰምቷል። በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ሞሊ ፊን የመሰሉ ዲፕሎማቶች የግንኙነቱን መሻሻል ሲደግፉ የአሜሪካ የዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት (USAID) አስተዳዳሪ ሳማንታ ፓወር የሚገኙበት ጎራ ለተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች እና የጦር ወንጀሎች ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ቁርጠኝነት ሊኖር ይገባል የሚል አቋም አላቸው። ምስል Seyoum Getu/DW

የአሜሪካ የዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት (USAID) አስተዳዳሪ ሳማንታ ፓወር የሚገኙበት ጎራ በወገኑ የፕሬዝደንት ጆ ባይደን አስተዳደር ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋትን አንገብጋቢ ኤኮኖሚያዊ ዕርዳታ ለመፍቀድ በጦርነቱ ወቅት ለተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች እና የጦር ወንጀሎች ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ቁርጠኛ ለመሆኑ ማረጋገጫ ሊያገኝ ይገባል የሚል እምነት አለው።

የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ለመሆን በህወሓት ከታጩት አቶ ጌታቸው ረዳ በተገናኙበት የአዲስ አበባ ጉዟቸው የሰጧቸው ማብራሪያዎች እጅግ ዲፕሎማሲያዊ ሆነው ታይተዋል። ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት ካቆመው የግጭት ማቆም ሥምምነት በኋላ የታዩ መሻሻሎችን ደጋግመው ሲጠቅሱ ነበር። የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች መቀነሳቸውን፣ የኤርትራ ወታደሮች በአብዛኛው መውጣታቸውን ደጋግመው አንስተዋል። ብሊንከን ኢትዮጵያ የሽግግር ፍትኅ ሥርዓት ለመዘርጋት ለጀመረችው ጥረትም በጎ አተያይ እንዳላቸው ንግግሮቻቸው ያሳብቃሉ።

ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ሲገናኙ የኢትዮጵያ ኤኮኖሚያዊ ፈተናዎች አጀንዳ ነበር። ለእነዚህ ኤኮኖሚያዊ ፈተናዎች አሜሪካን ጨምሮ ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የምትጠብቀው እገዛ ግን እንዲህ በቀላሉ የሚገኝ አይመስልም። የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሰጡት ማብራሪያ "የራሳችንን ግንኙነት እና እገዛ በተመለከተ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች አሁንም እየተፈጸሙ አለመሆኑን፤ የሽግግር ፍትኅ በሁለት እግሩ ቆሞ አካታች እና ተዓማኒ በሆነ መንገድ ሥራ ላይ መዋሉን ለማረጋገጥ ሥምምነቱን ገቢራዊ የማድረግ ሒደት እስከቀጠለ ድረስ ከኢትዮጵያ ጋር የሚኖረን ግንኙነት የኤኮኖሚ ጉዳዮችን አካቶ አብሮ ወደፊት ይራመዳል" ሲሉ ተናግረዋል።

የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ሲገናኙ የኢትዮጵያ ኤኮኖሚያዊ ፈተናዎች አጀንዳ ነበር። ምስል Ethiopian Foreign Ministry

ብሊንከን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማብራሪያ ሲሰጡ ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች አንዱ የኢትዮጵያ ወደ አጎዋ የመመለስ ዕድልን የተመለከተ ይገኝበታል። ኢትዮጵያ የተወሰኑ የብቃት መሥፈርቶች የሚያሟሉ ከሰሐራ በርሐ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገራት ከ1 ሺሕ 800 በላይ የሸቀጥ አይነቶችን ቀረጥ ሳይከፍሉ በአሜሪካ ገበያ እንዲሸጡ ከሚፈቅደው የግብይት ሥርዓት ውጪ የሆነችው ታኅሳስ 23 ቀን 2014 በፕሬዝደንት ጆ ባይደን ውሳኔ ነበር። ብሊንከን ለጥያቄው በቀጥታ ምላሽ ባይሰጡም "ኢትዮጵያ ወደ አጎዋ ለመመለስ ያላትን ምኞት እኛም እንጋራለን። ግጭት የማቆም ሥምምነቱ እየተተገበረ በመሆኑ በግልጽ ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ እየሄደ ነው" ሲሉ ተደምጠዋል።

አንቶኒ ብሊንከን ከአዲስ አበባ ወደ ዋሽንግተን በተመለሱ በቀናት ልዩነት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ የኤርትራ ጦር፣ የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) እና የአማራ ኃይሎች አባላት "የጦር ወንጀል ፈጽመዋል" የሚል ድምዳሜ ላይ መድረሳቸውን ይፋ አድርገዋል። ብሊንከን የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የተለያዩ የዓለም አገራትን የሰብዓዊ መብቶች ይዞታ የተነተነበትን የ2022 ዓመታዊ ሪፖርት ይፋ ሲያደርግ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ የኤርትራ ጦር እና የአማራ ኃይሎች አባላት "በሰብአዊነት ላይ ወንጀል ፈፅመዋል" ሲሉ ወንጅለዋል።

የአሜሪካ ድምዳሜ ከአዲስ አበባ እና ከአስመራ ብርቱ ተቃውሞ ገጥሞታል። የኢትዮጵዮጵያ መንግሥት እንዲያውም ብሊንከን የደረሱበት መደምደሚያ "አሜሪካ በኢትዮጵያ አካታች የሰላም ሒደት እንዲኖር የምታደርገውን ድጋፍ የሚያደናቅፍ" እንደሆነ ተችቷል። የአዲስ አበባ እና ዋሽንግተን ግንኙነት መሻሻል አሳየ ሲባል መልሶ የተፈጠረው አተካሮ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ እና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የምትሻውን እገዛ ለማግኘት ብዙ መጓዝ እንደሚጠበቅባት የሚጠቁም ነው።

እሸቴ በቀለ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW