ኢትዮጵያ የኒዩክሌር ኃይል ማመንጫ ያስፈልጋታልን?
ሐሙስ፣ መስከረም 29 2018
ኢትዮጵያ የኒኩሌር ኃይል ማመንጫ ልማትን በተመለከተ ከሩሲያ ጋር በጋራ ለመሥራት መስማማቷን በቅርቡ ገልፃለች። ጠቅላይ ሚኒሥትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በይፋዊ የፌስቡክ ገፃቸው እንዳሰፈሩት ስምምነቱ በተለይም ለማኅበረሰብ አገልግሎት የሚውል ንፁሕ ኃይል ለማቅረብ የጋራ የኒኩሊየር ኃይል ማመንጫ ማልማት ላይ ያተኩራል። ስለኒዩክሌር ኃይል ሲነሳ በአብዛኛው ከሰላማዊ ጠቀሜታው ይልቅ ለጦርነት የመዋሉ ጉዳይ ተደጋግሞ ይነሳል እና ስምምነቱን በስጋት የተመለከቱም አሉ። በኢትዮጵያ የኑዩክሌር ሳይንስ ማኅበረሰብ መስራች እና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ አስቻለው ዓለሙ በኒዩክሌር ኃይል ላይ ያለው አመለካከት አሉታዊ መሆኑኑን ይገልፃሉ።ስለሆነም ማኅበሩ ይህንን አመለካከት ለመቀየር እየሰራ መሆኑን ያስረዳሉ።
በአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩንቨርሲቲ የኒዩክሌር ማብላያ ቴክኖሎጂ የልህቀት ማዕከል ኃላፊ ዶክተር ደረጃው አየለ በበኩላቸው ፤ የኒዩክሌር ኃይል በርካታ ጠቀሜታዎች አሉት ይላሉ።ማብራሪያቸውን ኒዩክሌር ምንድነው ከሚለው ይጀምራሉ። እንደ አዶክተር ደረጃው ገለፃ፤ የኑክሌር ከሀይል ከኤለክትሪክ ማመንጫነቱ በተጨማሪ ለትምህርት እና ምርምርም ወሳኝ ጠቀሜታ አለው።ይህም የሳይንስ እውቀትን ለማዳበር፣ ፈጠራን ለማስተዋወቅ እና እንደ ሃይል፣ ጤና እና አካባቢ ያሉ የማህበረሰብ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ይረዳል።
አቶ አስቻለው በበኩላቸው በኢትዮጵያ በዘርፉ ለሚደረግ ለጥናት ምርምር የአሁኑ ጅምር ጠቀሜታው የጎላ ነው ይላሉ።
ከፍተኛ የኃይል ጥንካሬ እና ዝቅተኛ የካርቦን ልቀት
የኑክሌር ነዳጅ ከፍተኛ የኃይል ጥንካሬ ያለው ሲሆን፤ አንድ ኪሎ ግራም ዩራኒየም በተመሳሳይ በድንጋይ ከሰል ከሚመረተው 20,000 እጥፍ ሃይል ማምረት ይችላል። ይህ የሀይል ግዝፈት ከቅሪተ አካል ነዳጆች ጋር ሲነፃፀር የነዳጅ ፍጆታ ድግግሞሽ እና መጠን ይቀንሳል።የኑክሌር ኃይል ማመንጫዎች በሚሠሩበት ጊዜ አነስተኛ የሙቀት አማቂ ጋዞችን የሚያመነጩ በመሆናቸውም ለአየር ንብረት ለውጥ አወንታዊ አስተዋፅኦ አለው። ይህም በአንድ ኪሎዋት ሀይል ከ15-50 ግራም ካርቦንዳይ ኦክሳይድ በስዓት ያመነጫል።ይህም በሰዓት 450 ግራም ከሚያመነጨው የተፈጥሮ ጋዝ እና 1,050 ግራም ከሚያመነጨው የደንጋይ ከሰል ጋር ሲነፃፀር በጣም የተሻለ ነው።በዓለም ላይ ያለው የኑክሌር ኃይል ማመንጫ በየዓመቱ 1.5 ጊጋ ቶን የካርቦን ልቀትን ለማስወገድ ይረዳል።አስተማማኝነቱን በተመለከተም የኑክሌር ኃይል ማመንጫዎች ከየትኛውም የኃይል ምንጭ በተሻለ በከፍተኛ የአቅም ያለማቋረጥ መሥራት ይችላል፤ በቅሪተ አካል ነዳጅ ላይ ያለውን ጥገኛነትም ይቀንሳል።
በዚህ ሁኔታ የኑክሌር ኃይል በርካታ ጥቅሞች ቢኖሩትም ፣ የሚያደርሳቸው ጉዳቶች ደግሞ የኑክሌር ኃይልን አከራካሪ ምርጫ ያደርጉታል።ከነዚህም መካከል ፦ የኑክሌር ዝቃጭ አያያዝ እና አወጋገድ ይገኝበታል።የኑክሌር ኃይል ማመንጫዎች የራዲዮአክቲቭ ቆሻሻ እና ተረፈ ምርት አላቸው። ይህንን አደገኛ ቆሻሻ ለማስወገድ አዳዲስ የማከማቻ ቦታዎች መገንባት አለባቸው።የረጅም ጊዜ የማስወገጃ መፍትሄዎች ደግሞ ውስብስብ እና ውድ ናቸው።
ከፍተኛ የካፒታል ወጪ
ከወጭ አንፃር፤ የኑክሌር ኃይል ማመንጫዎችን መገንባት ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ይፈልጋል።መረጃዎች እንደሚያሳዩት በኒውክሌር ጣቢያ ውስጥ ለአንድ ኪሎዋት ኃይል በግምት ከ5,500-8,100 የአሜሪካ ዶላር ወጪ ማድረግን ይጠይቃል። ስለዚህ፣ 1,100 ሜጋዋት አቅም ያለው የኒዩክሌር ማብላያ ለመገንባት ፣ ከ6 ቢሊዮን እስከ 9 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጪ ያስወጣል እንደ ማለት ነው።ከዚህ አንፃር ከውኃ ፣ ከፀሐይ እና ከንፋስ ኃይል ጋር ሲነጻጸር, የኑክሌር ዋጋ በጣም ውድ ነው። በተጨማሪም፣ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት ወደ ኑክሌር ኃይል የሚፈስ ከሆነ፣ ወደ ታዳሽ ሀይሎች የሚደረገውን መዋዕለንዋይ ሊሻማ ይችላል። ዶክተር ደረጃው ግን የኤለክትሪክ ሀይል ከተመረተ በኋላ ዋጋው ርካሽ መሆኑን ይገልፃሉ።
የዩራኒየም ሀብት ውሱንነት
ለኑክሌር ኃይል ማመንጫዎች ዋናው ንጥረ ነገር የሆነው ዩራኒየም ውሱን ሀብት መሆኑም ሌላው ተግዳሮት ነው። የዓለም የኑክሌር ማኅበር እንደገለጸው፣ አሁን የለው ሀብት በአሁኑ የፍጆታ መጠን ለ90 ዓመታት ያህል የሚያገለግል ነው። ነገር ግን፣ የኒውክሌር ሃይል አቅም ካደገ፣ ሀብቱ በፍጥነት ሊያልቅ ይችላል።ከዚህ አንፃር የኑክሌር ኃይል ለዓለም የኃይል ፍላጎቶች ሙሉ በሙሉ መፍትሄ ባለመሆኑ አማራጭ፣ ታዳሽ ሀብቶች አዋጭ ሆነው ይታያሉ።አቶ አስቻለው ግን የሀይል አማራጮችን ቀላቅሎ መጠቀም የተሻለ ነው ይላሉ።
የኑክሌር ኃይል ማመንጫዎች የፍንዳታ አደጋዎች ስጋት
የአለም ኑክሌር ማህበር መረጃ እንደሚያሳየው ከ1970ዎቹ የነዳጅ ቀውስ በኋላ የኒውክሌር ሃይል አጠቃቀም ከፍ ብሏል።በዚህም የኒዩክሌር ሀይል የተረጋጋ እና ቀልጣፋ የኃይል ምንጭ እንደሚሆን ተስፋ ሰጥቷል። ነገር ግን፣ በ1979 በስሪ ማይል ደሴት፣ በ1986 በቼርኖቤል እና በ2011 በጃፓን ፉኩሺማ የተከሰቱት ከፍተኛ አደጋዎች ዓለም አቀፍ ስጋት ቀስቅሰዋል። በጎርጎሪያኑ 2011 በጃፓን የፉኩሺማ የተከሰተው አደጋ ከ150,000 በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል እና 200 ቢሊዮን ዶላር ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ አስከትሏል። በዚህ ምክንያት ሀገሪቱ 54 የኒውክሌር ማመላለሻዎቿን ወዲያውኑ ዘግታለች። የሃይል አቅርቦት ክፍተቱም በነዳጅ ተሞልቷል። እንደ ጀርመን ያሉ ሀገራትም የኒውክሌር ኃይልን ለማስቀረት እቅድ በማውጣት ትኩረታቸውን ወደ ታዳሽ እና አማራጮች የሀይል ምንጮች አዙረዋል።
ስለሆነም፤የኑክሌር ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ቁጥጥር በኑክሌር ኢንዱስትሪ ውስጥ ደህንነት እና የአካባቢ ጥበቃን በማረጋገጥ ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታል።ከዚህ ባሻገር በዘርፉ የሚደረገው ቁጥጥር ተግባራትን በኃላፊነት ለመፈፀም፣ ግልጽነትን፣ ተጠያቂነትን እና በኑክሌር ቴክኖሎጂ ሰላማዊ አጠቃቀም ላይ የህዝብ አመኔታን ለማግኘት ይረዳል። ያ ከሆነ የኒዩክሌር ሀይልን ለህክምና ፣ ለኤለክትሪክ ሀይል አቅርቦት ፣ለምርምር እና ለሌሎች ጠቃሚ አገልግሎቶች ያለ ችግር ጥቅም ላይ ማዋል ይቻላል።
አዳዲስ የኑክሌር ኃይል የሚፈልጉ ሀገራት ቁጥር እየጨመረ ነው
በአጠቃላይ የኑክሌር ሃይል እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አዳጊ ሀገራት ዕድሎችን እና ጉልህ ተግዳሮቶችን አካቶ የያዘ ነው።የኑክሌር ሃይል ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለመደገፍ እና ከካርቦን ነፃ የሆነ አስተማማኝ ኃይል ለማግኘት ይረዳል ። ነገር ግን ማብላያውን ለመገንባት ከፍተኛ ወጭ የሚጠይቅ ሲሆን፤ የሕግ ማዕቀፎችን ፣ ጥብቅ ጥንቃቄ እንዲሁም ትልቅ እና የተረጋጋ የኤሌክትሪክ መረቦችን ይፈልጋል።
ዓለም አቀፉ የኑዩክሌር ማኅበር መረጃ በቅርቡ ባወጣው መረጃ አዳዲስ የኑክሌር ኃይል የሚፈልጉ ሀገራት ቁጥርራቸው እየጨመረ ነው።እንደ ማህበሩ ወደ 30 የሚጠጉ አገሮች የኒውክሌር ኃይል ፕሮግራሞችን እያሰቡ፣ እያቀዱ ወይም እየጀመሩ ነው።
የትኞቹ የአፍሪቃ ሀገራት የኒዩክሌር ኃይል ይጠቀማሉ
ደቡብ አፍሪቃ ብቸኛዋ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ (የኮበርግ የኑክሌር ኃይል ጣቢያ) ያላት አፍሪካዊት ሀገር ነች። ግብፅ በአሁኑ ወቅት የኤል ዳባ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያን ከሩሲያ ጋር በመገንባት ላይ ትገኛለች። ኒጀርን፣ ጋና፣ ናይጀሪያ፣ ኡጋንዳ፣ ኬንያ እና ዜምባብዌን የመሳሰሉ የአፍሪቃ ሀገራትም ከሩስያ ጋር በዚሁ የኑክሌር ጉዳይ ስምምነት ላይ ደርሰው የኒውክሌር ኃይልን ለኤሌክትሪክ ኃይል ለማዋል ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
ሀገራቱ በሚያገኙት የኤሌትሪክ ሃይል አስፈላጊ አገልግሎቶችን እና ምጣኔ ሀብትን ማሳደግ እንደሚችሉ በማመናቸውም ፤እንደ የዓለም ባንክ ያሉ ዓለምአቀፍ አካላት ሀገራቱ የኒውክሌር ሃይልን ለማግኘት የሚያደርጉትን ጥረት በመደገፍ ላይ ናቸው።
ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።
ፀሐይ ጫኔ