1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

ኢትዮጵያ የኒውክሌር ቴክኖሎጂን መጠቀም ትሻለች

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 16 2011

ኢትዮጵያ የኒውክሌር ቴክኖሎጂን በህክምና፣ በግብርናና በኢንደስትሪ ዘርፍ ጥቅም ላይ ለማዋል እንቅስቃሴ መጀመሯን ዐስታወቀች። የህክምና ዘርፉን በኢትዮጵያም ለማዘመን የቀዶ ጥገና ህክምናውን ጥራት ለማሻሻል እንዲሁም የኢነርጂ እና የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ ዘርፍ ለማሳደግ የኒውክሌር ቴክኖሎጂ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረውም ሚኒስትሩ አስረድተዋል።

Schweiz CERN Forschung Schnelle Teilchen überholen Licht Albert EinsteinSchweiz CERN Forschung Schnelle Teilchen überholen Licht Albert EinsteinSchweiz CERN Forschung Schnelle Teilchen überholen Licht Albert Einstein
ምስል dapd

የኒውክሌር ቴክኖሎጂ በኢትዮጵያ ለመጀመር እንውስቃሴ መጀመሩ ተገልጧል

This browser does not support the audio element.

ኢትዮጵያ የኒውክሌር ቴክኖሎጂን በህክምና፣ በግብርናና በኢንደስትሪ ዘርፍ ጥቅም ላይ ለማዋል እንቅስቃሴ መጀመሯን ዐስታወቀች። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ጀማል በከር በተለይ ለዶቼ ቨለ (DW) እንደገለጹት በቅርቡ በ11 ኛው ዓለም አቀፉ የአቶም ኤክስፖ ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ ከሩሲያ ጋር የተፈራረመችው የሁለትዮሽ የኒውክሌር ቴክኖሎጂ የፍኖተ ካርታ ትግበራ ስምምነት ዓለም አቀፍ ሰላማዊ ስምምነቶችን እና ድንጋጌዎችን መሠረት ያደረገ ነው ብለዋል። በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ እያደገ የመጣውን የህክምና ዘርፍ በኢትዮጵያም ለማዘመን የውጭ ምንዛሪ ወጭን ለማዳን እንዲሁም የቀዶ ጥገና ህክምናውን ጥራት ለማሻሻል እንዲሁም የኢነርጂ እና የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ ዘርፍ ለማሳደግ የኒውክሌር ቴክኖሎጂ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረውም ሚኒስትሩ አስረድተዋል።  

እንደ ጎርጎሪዮሱ አቆጣጠር ከግንቦት ወር 1954 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ የተለያዩ ክፍሎች የዩራንየም ክምችት መገኘቱን ኒዎርክ ታይምስ እና ሌሎችም የመገናኛ አውታሮች በዘገባቸው ዐስታውቀው ነበር። ሆኖም ይህን ለተለያዩ የምርት ግብአቶች እና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች እጅግ ጠቃሚ እና ተፈላጊ የሆነ የተፈጥሮ ሃብት አገሪቱ ጥቅም ላይ ሳታውለው ለበርካታ ዓመታት ቆይታለች። በቅርቡ ግን በሩስያ በተካሄደው 11ኛው ዓለማቀፍ የአቶም-ኤክስፖ ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር  ዶ/ር ጌታሁን መኩሪያ እና የሩስያ መንግሥት አቶሚክ ኢነርጂ ኮርፖሬሽን ዳይሬክተር ጀነራል አሌክሲ ሌካቼቭ የኒውክሌር ቴክኖሎጂን ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል የሁለትዮሽ የትግበራ ፍኖተ-ካርታ ስምምነት ተፈራርመዋል። ይኸው ስምምነት የኒውክሌር ቴክኖሎጂን ለኃይል ማመንጫ፤ ለግብርና፤ ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ግብዓት የሚውሉ ዘመናዊ ቁሶችን ለማምረትና፤ የህክምናውን ዘርፍ ለማዘመን ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል መሆኑንም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ጀማል በከር በተለይ ለዶቼቨለ (DW) ገልጸዋል።

Äthiopien | Innovation & Technology Minister Jemal Beker Äthiopien | Innovation & Technology Minister Jemal Beker 
ምስል DW/E. Fekade

የኒውክለር ቴክኖሎጂን በኢትዮጵያ ማስፋፋት በተለይ በዓለም እያደገ የመጣውን የህክምና ዘርፍ በኢትዮጵያ በማዘመን የጨረር ህክምና አገልግሎቶችን ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማዳረስ እንዲሁም በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በሌሎች አገራት እንደ ካንሰር ያሉ በሽታዎችን ለመታከም ህሙማን ያወጡት የነበረውን  ወጪ ለማስቀረትና ለመንግስት ፈተና የሆነውን የውጭ ምንዛሬ እጥረትም ለመቅረፍ ይረዳል ነው የሚሉት ሚኒስትሩ።  ከዚህም ባሻገር የቀዶ ጥገና ህክምናን የተቀላጠፈ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል ሲሉ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ጀማል አስረድተዋል። ቴክኖሎጂው ትላልቅ ኢንደስትሪዎችን በኢትዮጵያ ለመገንባት ብሎም በዝናብ ላይ ጥገኛ ከሆነው የኃይል ማመንጫ ኢትዮጵያን በማላቀቅ ወደ ድብልቅ የኢነርጂ አማራጮችም ለማሸጋገር ጠቀሜታ አለው ነው ያሉት።

China Atomkraftwerk Modell in PekingChina Atomkraftwerk Modell in Peking
ምስል picture-alliance/dpa/Imaginechina/Hu Qingming

ኢትዮጵያ እንደ ኦፓል የከበረ ማዕድን እንዲሁም ለሞባይል ስልኮች እና ልዩ ልዩ የኤሌክትሮኒክስ ምርቶች ግብአት እጅግ ተፈላጊ የሆነውን  ታንታለምን ጨምሮ ለኒውክለር ቴክኖሎጂ ምርት የሚያገለግለው ዩራኒየም ከፍተኛ ክምችት እንዳላት ቢታወቅም በምርቶቹ ሽያጭ እና ገቢ ላይ መንግሥትን ግልጽነት ይጎለዋል የሚሉ ነቀፌታ እና ትችቶች በተለያዩ ወገኖች ሲሰነዝሩ ቆይተዋል። በተለይ በሚንስቴር መስሪያቤቱ አሁን ለመጀመር የታቀደው የኒውክለር ቴክኖሎጂ ዓለማቀፍ ሰላማዊ የኒውክሌር ቴክኖሎጂ ስምምነቶችን በማክበር ለተፈለገው አገልግሎት ብቻ ጥቅም ላይ የመዋሉን ሂደት በተመለከተ የትግበራ ፍኖተ ካርታ ስምምነቱ ምን ምን ያህል ግልጽነት የተሞላው ነው ስንል  የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታውን አቶ ጀማል በከር ጠይቀናቸው ነበር።  " በ 11 ኛው ዓለማቀፉ የአቶም ኤክስፖ ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ ከሩሲያ ጋር የተፈራረመችው የሁለትዮሽ የኒውክሌር ቴክኖሎጂ የፍኖተ ካርታ ትግበራ ስምምነት ዓለማቀፍ ሰላማዊ ስምምነቶችን እና ድንጋጌዎችን መሰረት ያደረገ ነው " ሲሊ ነው ሚኒስትር ዴኤታው የሃገራቱ ስምምነት የተመሰረተበትን ዋና ማዕቀፍ ያብራሩት።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የኒውክለር ቴክኖሎጂን በኢትዮጵያ ለማስፋፋት ከጀመረው እንቅስቃሴ ጎን ለጎን የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲም የኒውክሌር ግንባታ፤ የባዮ ቴክኖሎጂዎች፤ ዘላቂ የኃይል አቅርቦትና የሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች የምርምር ስራዎቻቸውን የሚያከናውኑባቸው፤ሌሎች የልህቀት ማዕከላትን አቋቁሞ አገሪቱን ዓለም ከደረሰችበት ዘመናዊ የዕድገት ደረጃ ለማድረስ ጥረት እያደረገ ሲሆን ለምርምርና ቴክኖሎጂ ስርፀት ተግባራት የሚያገለግል ግዙፍ የቤተ-ሙከራ ማዕከላትን ያካተተ ተጨማሪ ህንፃም ለመገንባት እየተዘጋጀ መሆኑን በቅርቡ አስታውቋል።

እንዳልካቸው ፈቃደ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW