ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ወደ ጀመረችው ድርድር ተመልሳለች-ምን ይጠብቃታል?
ሐሙስ፣ ሐምሌ 27 2015
ኢትዮጵያ ከ20 ዓመታት በፊት የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የጀመረችውን ሒደት ከቆመበት ለማስቀጠል ባለፈው ሣምንት ወደ ጄኔቭ ተመልሳለች። ዋና ተደራዳሪነቱን ወደ ብሔራዊ ባንክ ገዥነት ከተዛወሩት አቶ ማሞ ምኅረቱ የተረከቡት የንግድ እና ቀጠናዊ ትሥሥር ሚኒስትሩ አቶ ገብረመስቀል ጫላ ናቸው። ኢትዮጵያ በአፍሪካ አኅጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠና በኩል ለመነገድ የምታደርገን ጥረት ከዳር ያደረሰውን ተቋም የሚመሩት አቶ ገብረመስቀል ባለፈው ሣምንት ወደ ጄኔቭ አቅንተው "በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ" መወያየታቸውን ከሒደቱም መተዋወቃቸውን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ከድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ንጎዚ ኦኮንጆ ኢዌላ ጋር ከተነጋገሩ በኋላ የዓለም የንግድ ድርጅት ባሰራጨው የቪዲዮ መልዕክት "ድርድሩን አንድ ጊዜ ከዚህ ከጀመርን ያለ ማቋረጥ ለመቀጠል የአቅማችንን ያክል እንሞክራለን። ይኸ የኢትዮጵያ መንግሥት ቁርጠኝነት እና ዋና ዳይሬክተሯ የሰጡን አቅጣጫ ነው" ሲሉ ተደምጠዋል። በአቶ ገብረመስቀል በኩል የኢትዮጵያ መንግሥት ለዓለም የንግድ ድርጅት ማስተላለፍ የፈለገው መልዕክት ቢያንስ በዋና ዳይሬክተሯ ተቀባይነት ያገኘ ይመስላል።
የዓለም የንግድ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር "የኢትዮጵያ የንግድ ሚኒስትር ብቻ ሳይሆን የአባልነት ዋና ተደራዳሪ ጭምር የሆኑት ክብርነታቸው [አቶ ገብረመስቀል] ከልዑካኖቻቸው ጋር ያደረጉት ጉብኝት የሚያስደስት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኢትዮጵያ የአባልነት ሒደቱን ዳግም እንድትጀምር በማድረጋቸው ደስተኞች ነን" ሲሉ ተናግረዋል። ድርድሩ እንዴት እንደሚቀጥል ከኢትዮጵያ ልዑካን መወያየታቸውን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሯ "ሒደቱ አንዴ እየተጀመረ ሌላ ጊዜ እየተቋረጠ ሳይሆን ያለዕንከን መቀጠሉን ለማረጋገጥ በትብብር ለመሥራት ዝግጁ ነን" ብለዋል።
ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅትን ለመቀላቀል በይፋ ጥያቄ ያቀረበችው በ1995 ነበር። ለሒደቱ መዘግየት "በድርጅቱ ውስጥ ለመቀላቀል አስፈላጊ የሆኑ ሪፎርሞች መዘግየት" ምክንያት እንደሆነ የኢትዮጵያ መንግሥት ያዘጋጀው ረቂቅ የንግድ ፖሊሲ ያትታል። የቀድሞው ኢሕአዴግ ይመራበት በነበረው የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ጭምር ኢትዮጵያን የዓለም ንግድ ድርጅት አባል የማድረግ ውጥን እንዳለው ቢያሰፍርም ለጉዳዩ ግን የሚገባውን ትኩረት እንዳልሰጠ የንግድ ሕግ እና ፖሊሲ ባለሙያው አቶ በረከት ዓለማየሁ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።
አቶ በረከት እንደሚሉት የኢሕአዴግ ቸልተኝነት ይከተል ከነበረው "ርዕዮተ ዓለም ጋር የተያያዘ" ጭምር ነው። ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ብትሆን ወደ ገበያው የሚገቡ "የውጭ የንግድ ሥራዎችን በፉክክር ደረጃ አንችላቸውም የሚል ፍርሐት" እንዲሁም "መንግሥት በቂ የሆነ የመቆጣጠር አቅም የለውም" የሚል አመክንዮ "ሒደቱ በፍጥነት እንዳይሔድ እና እንዲጓተት" ማድረጉን የንግድ ሕግ እና ፖሊሲ ባለሙያው አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ለዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት የምታደርገውን ድርድር የተረከበው የአሁኑ የንግድ እና ቀጠናዊ ትሥሥር ሚኒስቴር ያለፈባቸው የአደረጃጀት ለውጦች ለሒደቱ መዘግየት አስተዋጽዖ ካበረከቱ ጉዳዮች አንዱ እንደሆነ የንግድ ሕግ እና ፖሊሲ ባለሙያው አቶ በረከት ዓለማየሁ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። የአባልነቱ ዋና ተደራዳሪ በየጊዜው መቀያየር ሌላ በሒደቱ ላይ ጫና ያሳደረ ጉዳይ ነው።
ለስምንት ዓመታት ገደማ አንዳች ትርጉም ያለው እርምጃ ሳያሳይ የቆየው ሒደት ዳግም የተነቃቃው በጥር 2012 ነበር። የኢትዮጵያን የአባልነት ጥያቄ የሚመለከተው የዓለም የንግድ ድርጅት ኮሚቴ ካደረገው አራተኛ ስብሰባ በኋላ በቀድሞው ዋና ተደራዳሪ አቶ ማሞ ምኅረቱ የሚመራው ልዑካን ቡድን ሒደቱን በታኅሣስ 2014 ገደማ የማጠናቀቅ ዕቅድ ነበረው። ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ የታየው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት የመንግሥት ትኩረት ከንግድ ድርድር ጉዳዮች ይልቅ አገሪቱን ወደማረጋጋት እንዲያዘነብል አስገድዶታል። የኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት የሚኖረውን ጠቀሜታ በጥልቀት የሚፈትሽ "ግልጽ እና የተሟላ የንግድ ፖሊሲ አለመኖር" ለሒደቱ መጓተት አስተዋጽዖ እንዳበረከተ አቶ በረከት ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የምታደርገውን ድርድር የሚመለከተውን ኮሚቴ በሊቀ-መንበርነት የሚመሩት በድርጅቱ የዩናይትድ ኪንግደም ምክትል ቋሚ መልዕክተኛ ሬቤካ ፊሸር ናቸው። አገራቸው ዩናይትድ ኪንግደም ባለፈው ሰኔ ለኢትዮጵያ ዋና ተደራዳሪ እና ባለሙያዎቻቸው ቴክኒካዊ ዕገዛ 450,000 ፓውንድ መድባለች።
"ለንግድ ሥራዎች እና ባለወረቶች ተገማችነት እና እርግጠኝነት ይሰጣል" ተብሎ የሚጠበቀው የኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት ለዩናትድ ኪንግደም "ጠቃሚ" ጉዳይ ነው። የንግድ ሕግ እና ፖሊሲ ባለሙያው አቶ በረከት እንደሚሉት ሒደቱን ፈታኝ የሚያደርገውም በኢትዮጵያ ገበያ ከፍ ያለ ፍላጎት ካላቸው እንደ ዩናይትድ ኪንግደም እና አሜሪካ ያሉ አገሮች ጋር የሚደረጉ የሁለትዮሽ ድርድሮች ናቸው።
ወደ ኢትዮጵያ ገበያ የመግባት ፍላት ያላቸው በኤኮኖሚ የበለጸጉት አገሮች ፋይናንስ፣ ቴሌኮም እና ኢነርጂን በመሳሰሉ የሥራ ዘርፎች ማሻሻያ እንዲደረግ ግፊት ሊያሳድሩ እንደሚችሉ አቶ በረከት ይጠብቃሉ። ለረዥም ዓመታት ለውጭ ባለወረቶች ተዘግተው የቆዩ እንደ ቴሌኮም እና የባንክ አገልግሎቶች የመሳሰሉ ዘርፎች ላይ ተግባራዊ እየተደረጉ ያሉ ማሻሻያዎች ለሒደቱ መፋጠን አዎንታዊ ሚና ሊጫወቱ የሚችሉ እርምጃዎች ናቸው። ባለፉት ዓመታት ተግባራዊ የተደረጉት ማሻሻያዎችም ሆኑ ወደፊት የታቀዱት ግን በዓለም የንግድ ድርጅት አባል ሃገራት ዘንድ ይሁንታ ማግኘት ይኖርባቸዋል።
"በሁለትዮሽ የገበያ ዕድል ድርድሮች ተጨማሪ የሕግ፣ የፖሊሲ እና ተቋማዊ ማሻሻያዎች እንዲደረጉ» ግፊት ሊኖር እንደሚችል አቶ በረከት ይጠብቃሉ። ከእነዚህ ውስጥ የመድን ዋስትናን ጨምሮ ለውጭ ባለወረቶች ዝግ የሆኑ ዘርፎች እንዲከፈቱ የሚደረግ ግፊትን ይጨምራል። "ከፍተኛ ቀረጥ አለባቸው ተብለው የሚታሰቡ የዕቃዎች ንግድ ዘርፎች ላይም ቀረጣችሁን ቀንሱ ወይም ቀረጣችሁን አስወግዱ የሚል ጥያቄም ሊኖር ይችላል። በንግድ እና በኢንቨስትመንት ዙሪያ በመንግሥት ደረጃ አድሏዊ አሠራሮችን የሚያስቀሩ ወይም የሚቀንሱ እርምጃዎችን ውሰዱ የሚሉ ጥያቄዎች ሊኖሩ ይችላሉ" ሲሉ የንግድ ሕግ እና ፖሊሲ ባለሙያው አስረድተዋል።
የዓለም የንግድ ድርጅት በአሁኑ ወቅት 164 አባላት አሉት። ኢትዮጵያ ተሳክቶላት የድርጅቱ አባል ብትሆን ገበያዋን ለሌሎች ከፍታ ሸቀጦቿን በአባል አገራቱ ያለ ቀረጥ የመሸጥ ዕድል ታገኛለች። እንደ የዓለም የንግድ ድርጅት ያሉ ሥምምነቶች ቀረጥ ያልሆኑ የንግድ መሰናክሎችን (non-tariff barriers) ያስወግዳሉ። በዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ እንደ ቡና ያሉ ሸቀጦቿን ያለ ክልከላ አቅሟ በፈቀደ መጠን የገበያ ፍላጎት ባለበት ሁሉ እንድትሸጥ ዕድል ይሰጣል።
የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎችም ከአካባቢያዊ እና ዓለም አቀፍ የእሴት ሰንሰለቶች እንዲተሳሰሩም ያደርጋል። ከእነዚህ ትሩፋቶች ለመቋደስ ግን ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል አገራት የሚያነሷቸውን "የሕግ፣ የፖሊሲ እና የተቋማዊ አሠራር ማሻሻያዎች" ማድረግ እንደሚኖርባት አቶ በረከት አስረድተዋል። "እነዚህ ደግሞ በባህሪያቸው ጊዜ የሚፈጁ ናቸው። ምን ያክል ጊዜ ይፈጃል የሚለውን ቁርጥ አድርጎ ማስቀመጥ አስቸጋሪ ነው" የሚሉት አቶ በረከት "የአባልነት ጥያቄው ሒደት እና መልስ የሚያገኝበት ጊዜ የሚወሰነው አባል መሆን የፈለገው እና ጥያቄ ያቀረበው አገር በሚወስደው ተነሳሽነ፤ በሚወስዳቸው የሕግ፣ የኤኮኖሚ፣ የፖሊሲ እና ተቋማዊ ማሻሻያዎች" እንደሚሆን ገልጸዋል።
እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሠ