1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ኢትዮጵያ፤ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል የመሆን ጥረቷና ተስፋዋ

ረቡዕ፣ መጋቢት 17 2017

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ ኢትዮጵያ የድርጅቱ አባል እንድትሆን ለተዋቀረው ተደራዳሪ ቡድን ሰሞኑን ስዊዘርላንድ ውስጥ በተደረገው የድርጅቱ የሥራ ቡድን ስብሰባ 110 ጥያቄዎች ቀርበውለት እንደነበር በመግለጽ፤ ሀገሪቱ በአጭር ጊዜ ማለትም በ2026 የዚህ ድርጅት አባል የመሆን "ተስፋ" እንዳላት ገልፀዋል

ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል የመሆን ጥያቄዋ ከአንድ ዓመት በኋላ ሊሳካ እንደሚችል የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር አስታወቁ
የኢትዮጵያ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዋና መስሪያ ቤት።አዲስ አበባምስል፦ Solomon Muchie/DW

ኢትዮጵያ፤ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል የመሆን ጥረቷና ተስፋዋ

This browser does not support the audio element.

ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል የመሆን ጥያቄዋ ከአንድ ዓመት በኋላ ሊሳካ እንደሚችል የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ ተናገሩ።ሚኒስትሩ ትናንት ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ "ባቀድነው መሠረት መጓዝ ከቻልን፣ ኢትዮጵያ የካቲት 2026 የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ትሆናለች የሚል ተስፋ አለኝ" ብለዋል።ያነጋገርናቸው የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ሀገሪቱ የዚህ ድርጅት አባል ብትሆን የማይናቅ ጥቅም እንዳለው ጠቅሰውዋል። ይሁንና ሀገር ውስጥ ያለው ግጭት እና ጦርነት፣ ሙስና እና ሕገ-ወጥ ንግድ የድርጅቱ አባል ለመሆን በምታደርገው የሁለትዮሽም ይሁን የባለብዙ ወገን ድርድር ላይ ጥያቄ የሚያስነሳ ላለመሆኑ ማረጋገጫ የለም ብለዋል።/


ኢትዮጵያ በእርግጥም በቀጣዩ ዓመት የዚህ ድርጅት አባል ትሆን ይሆን?


ኢትዮጵያ 166 ሀገራት አባል ወደ ሆኑበትእና የዓለም ታሪፍን ለማስተካከል እንዲሁም የንግድ ውድድሮችን ሥርዓት ለማስያዝ ወደተቋቋመው የዓለም ንግድ ድርጅት ለመቀላቀል ጥያቄ ካቀረበች ሰነባብታለች።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ ኢትዮጵያ የድርጅቱ አባል እንድትሆን ለተዋቀረው ተደራዳሪ ቡድን ሰሞኑን ስዊዘርላንድ ውስጥ በተደረገው የድርጅቱ የሥራ ቡድን ስብሰባ 110 ጥያቄዎች ቀርበውለት እንደነበር በመግለጽ፤ ሀገሪቱ በአጭር ጊዜ ማለትም በ2026 የዚህ ድርጅት አባል የመሆን "ተስፋ" እንዳላት ገልፀዋል። ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ በንግድ ድርጅቱ አባል የመሆን ጥያቄዋ ለምን ተቀባይነት ሳያገኝ እንደቆየ የመዘግየቱን ምክንያት ሲገልፁ ወቀሳውን በወቅቱ መንግሥት ላይ አድርገዋል።


"ባንኩንም ጥርቅም አድርገህ፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችንም ጥርቅም አድርገህ አፍነህ ይዘህ፣ ገበያውንም አፍነህ ይዘህ የዓለም ንግድ ድርጅት ማለትና ማደናገር ጠቃሚም ተገቢም አልነበረም።"


ኢትዮጵያ የድርጅቱ አባል ለመሆን ምን ያህል ዝግጁ ናት?


ድርጅቱ አዲስ አባል ሀገራትን የሚቀበለው ሌሌች አባል ሀገራት ተቃውሞ ከሌላቸው ብቻ ነው። ኢትዮጵያ በተለይ ዩናይትድ ስቴትስ እና ካናዳ የፋይናንስ ዘርፏ ክፍት ካልሆነ፣ የውጭ ባንኮች ገብተው መሥራት ካልቻሉ እና የገበያ መሰሶ የሆኑ መስኮች ካልተከፈቱ በሚል የአባልነቷን ጥያቄ ተቃውመውባታል። 

የአዲስ አበባባ የጎዳና ላይ ንግድ በከፊል።ኢትዮጵያ በርካታ ስዎች በየጎዳናዉ በአነስተኛ ንግድና የሸቀጥ ልዉዉጥ የሚተዳደሩባት ሐገራት ናትምስል፦ Million Haileselassie/DW

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸ እንደሚሉት ሀገሪቱ አሁን እነዚህን ቅድመ ኹኔታዌች በማንሳቷ አባል ለመሆን እጅግ ይረዳታል።

"ካለው ውስብስብ የሙስና ችግር፣ ያሉት አለመረጋጋቶች ጋር ተያይዞ ሀገሮች ተዋውሞ ያነሱ እንደሆን አላውቅም እንጂ አሁን ኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ አቋቁማለች፣ የፋይናንስ ዘርፉን ክፍት አድርጋለች፣ የውጭ ኩባንያዎች በንግድ ሥርዓቱ እንዲሳተፉ ፈቅዳለች።" 
 

ባለሙያው እንደሚሉት ግን ይህ ብቻ የአባልነት ዋስትና ሰጪ መስፈርት አይደለም። በእርግጥስ ሀገሪቱ በዚህ ወቅት ለዚህ ዝግጁ ናት ወይ? የሚለውን ጥያቄም ያነሳሉ።

"የዚያ ድርጅት [የዓለም ንግድ ድርጅት] አባል ብንሆንም ለዚያ ዝግጁ ነን ወይ? አንደኛ ሀገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ ጦርነቶች ይካሄዳሉ፤ በሁለተኛ ደረጃ የሙስና እና የሕገ-ወጥ ንግድ በጣም የተንሰራፋበት ኹኔታ ነው የሆነው።"

የዓለም ንግድ ድርጅት የገጠመው ወቅታው ፈተና 


የኃያላን ሀገራት የምጣኔ ሀብት ግብግብ እና ብርቱ ውድድር የተቋሙን ኅልውና እየተፈታተኑት መሆኑንም የጠቀሱት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ የአሜሪካ 'ርምጃዎች ድርጅቱን እንዳይጎዱት ሥጋታቸውን ገልፀዋል።
  
"አሁን የዓለም ንግድ ድርጅት ደብዛው ጠፍቷል። ዩናይትድ ስቴትስ እና ቻይና በሚያደርጉት ፉክክር በተለይ አሁን ፕሬዝዳንት ፕራምፕ በሚያደርጉት እንደፈለጉ ታሪፍ የመጣል ጉዳይ የዓለም ንግድ ድርጅትን ቀውስ ውስጥ ከቶታል።"


የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ ኢትዮጵያ በ2026 ካሜሮን ላይ በሚደረገው 14ኛው የዓለም ንግድ ድርጅት የሚኒስትሮች ስብሰባ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ልትሆን ትችላለች የሚል ተስፋ እንዳላቸው ሲገልፁ ከዚያ በፊት የሀገሪቱን ገቢ የማመንጨት አቅም በሚጎዳ መልኩ ድርድሮች እንደማይደረጉ ተናግረዋል። 

ኢትዮጵያ የድርጅቱ አባል ብትሆን በውጭ ምርቶች የመጥለቅለቅና ለሀገር ውስጥ ምርት መዳከም የከፋ ተጋላጭ አትሆንም ወይ ለሚለውም ምላሽ ሰጥተውበታል።

"በጣም እንጎዳለን የተባለው ጉዳይ፤ እስካሁንስ ዘግተን ምን ተጠቀምን የሚለውን ማየት ጠቃሚ ይሆናል"


የዓለም ንግድ ድርጅት አባል መሆን ያለው ጥቅም ምንድን ነው?


ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ብትሆን መንግሥት በሚገቡ ምርቶች ላይ እንዳሻው ታሪፍ እንዳይጭን ያግዛል፣ የውጭ ኩባንያዎችም እንዲገቡ እና ሥራ እንዲያስፋፉ ዕድል ይፈጥራል የሚለው በጠቃሚ ጎኑ የሚታይ መሆኑን ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ገልፀዋል።"ኢትዮጵያ አሁን የዓለምን የንግድ ሕግ ታከብራለች በሚል ኢንቨስተሮች በገፍ ሊመጡ ይችላሉ የሚል ነገር ነው።"
 
ከተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ቀጥሎ በዓለም ላይ ከፍተኛ ሥልጣን የነበረው ድርጅት ነበር የሚባልለት የዓለም የንግድ ድርጅት በምስረታው ሰሞን ያመለከተ ሀገር ሁሉ አባል የሚሆንበት ነበር። ኢትዮጵያ በወቅቱ የሸቀጥ መጣያ እንሆናለን በሚል ሥጋት የአባልነት ጥያቄውን ወደ ጎን ብትለውም፣ ድርጅቱ ሀገራትን አባል ለማድረግ ውስብስብ መስፈርቶችን እና የሁለትዮሽ እና የባለ ብዙ ወገን ድርድሮችን አሳምኖ ማለፍን የግድ ካደረገ በኋላ ጥያቄውን አቅርባለች።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሕንፃ።አዲስ አበባምስል፦ Seyoum Getu/DW

ሠለሞን ሙጪ 

ነጋሽ መሐመድ

ፀሐይ ጫኔ 

 

 

 

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW