1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ውዝግቦችኢትዮጵያ

“ኢትዮጵያ የዲፕሎማሲውን መንገድ አሟጣ መጠቀም ይኖርባታል” ፖለቲከኞች

ሥዩም ጌቱ
ሰኞ፣ የካቲት 2 2018

ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በቃላት የሚያደርጉት ውዝግብ ወደ ጦርነት የመሔድ አዝማሚያ ቢያሳይም ዲፕሎማሲ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ተናግረዋል። አቶ ሙላቱ ገመቹ በበኩላቸው “ኢትዮጵያ ጥቅሟን ለማስከበር መስራቷ አስፈላጊ ቢሆንም የኃይል እርምጃው አስፈላጊነትን ግን ማስወገዱ ይጠቅማል” ብለዋል።

Thumbnail DONMOEthiopia
ምስል፦ DW

“ኢትዮጵያ የዲፕሎማሲውን መንገድ አሟጣ መጠቀም ይኖርባታል” ፖለቲከኞች

This browser does not support the audio element.

ኤርትራ ሠራዊት ተቆጣጣሯቸዋል ካለችው የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛቶች እንዲወጣና ለድርድር ዝግጁ እንዲሆን ኢትዮጵያ በይፋ መጠየቋ ሁለቱ አገራት መካከል ሊነሳ ይችላል ተብሎ ያሰጋውን ጦርነት ወደ ጫፍ እያወጣው ይገኛል።

የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቅዳሜ ጥር 30 ቀን 2018 ዓ.ም. ለኤርትራው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጻፈው ደብዳቤ ላይ ኤርትራ የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ድንበር በመጣስ በሰሜን ምሥራቅ አቅጣጫ የሚገኙ አካባቢዎችን ተቆጣጥራ እንደምትገኝ ገልጿል።

በዚህ ላይ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የቀድሞ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ከፍተኛ አመራር መምህርና ፖለቲከኛ አበበ አካሉ፤ በትግራዩ ጦርነት ተጠቅማ ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ዘልቃ የገባችው ኤርትራ የኢትዮጵያ ወሰኖችን እየገፋች ለመምጣቷ ብዙ ማሳያዎች አሉ ብለዋል፡፡ 

ሁለቱ አካላት በቅርብ ጊዜ ውስጥ ደግሞ እያፋፋሙ ካሉት የጦርነት ዛቻ ጋር ተያይዞ አሁን ላይ ከምን ጊዜውም በላይ ሁለቱ አገራት የመሳሪያ አፈሙዝ ለመሳብ ስለመቃረባቸው ግምት መኖሩን ጠቁመዋል፡፡

“ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በፓርላማ ላይ እንደጠቆሙት ኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ ግዛት እየሰፋች ለመምጣቷ ጥፋቱ የኛም ነው” የሚሉት አቶ አበበ፤ ይህ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት መደፈር ላሉት ተግባር የኢትዮጵያን መንግስት ተጠያቂ አድርገዋል፡፡ አሁን ላይ የኢትዮጵያ ግዛቶች እንዳይደፈሩ የማድረግ አስፈላጊነትም ላይ አጽእኖት የሰጡት ፖለቲከኛው፤ ነገር ግን ይህ መፍትሄው መፈለግ ያለበት የዲፕሎማሲው ስራ ተሟጦ እስኪያበቃ ነው ይላሉ፡፡

አቶ ሙላቱ ገመቹ “ኢትዮጵያ ጥቅሟን ለማስከበር መስራቷ አስፈላጊ ቢሆንም የኃይል እርምጃው አስፈላጊነትን ግን ማስወገዱ ይጠቅማል” ብለዋል። ምስል፦ DW/M. Yonas Bula

ሌላው አስተያየት ሰጪ ፖለቲከኛ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) ከፍተኛ ባለስልጣን አቶ ሙላቱ ገመቹ ናቸው፡፡ አቶ ሙላቱ እንደሚሉት “ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት የውስጥ ጉዳይ አኳያ በተቻለ መጠን በዲፕሎማሲው የአገሪቷን ጥቅም ማስከበር መቻል አስፈላጊ ነው” ብለዋል፡፡

ኢርትራ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ አማጺያንን ታደራጃለች መባሉና መዘዙ

በሰሜን ምሥራቃዊ የኢትዮጵያ ድንበር የኤርትራ ጦር ወታደሮች ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ዘልቀው መግባታቸው የኤርትራ ጦር ከአማፂ ቡድኖች ጋር እያደረገው ያለው የጋራ ወታደራዊ እርምጃ ጸብ ጫሪነት ብቻ ሳይሆን ፍፁም የሆነ ጥቃት ነው ሲል ድርጊቱን አውግዟል። ተቀባይነት የሌለው የተባለውን ይህን ተግባር ኤርትራ እንዲታቆምም ኢትዮጵያ በይፋ ጠይቃለች።

ፖለቲከኛ አበበ አካሉ ይህ የኤርትራ ተግባር ውሎ ያደረና የቆየ ነው ይላሉ፡፡ ኢትዮጵያ ምስራቅ አፍሪካ ላይ ያለውን አሁናዊውን የጂኦፖለቲካ እንቅስቃሴ ታሳቢ በማድረግ እንቅስቃሴዋን መማስላት አለባት ነው ያሉት፡፡ ፖለቲከኛው “ኤርታራ የኢትዮጵያ መንግስትን የሚቃወሙ አካላትን ስታደራጅና ስታስታጥቅ ቆይታለች” በማለትም፤ ቀጥታ ወደ ጦርነት መግባቱ አደጋው የከፋ ነው ይላሉ፡፡ ይህም ቀጣናው ብዙ ሃያላን ተዋንያን ኢላማቸው ያደረጉት በመሆኑ የመፋለሚያቸው ሜዳ ላለመሆን ጥንቃቄው አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

ፖለቲከኛ ሙላቱ በፊናቸው፤ “ኢትዮጵያ ጥቅሟን ለማስከበር መስራቷ አስፈላጊ ቢሆንም የኃይል እርምጃው አስፈላጊነትን ግን ማስወገዱ ይጠቅማል” የሚለውን አስተያየታቸውን ነው ያከሉት፡፡

ሥዩም ጌቱ 

እሸቴ በቀለ 

ጸሀይ ጫኔ 
 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW