1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ የድርድር ፖለቲካ የናፈቃት ሐገር

ሰኞ፣ መስከረም 30 2015

ሕወሓት ይባል ብልፅግና፤ ኢሐዴግ ይሁን ደርግ፣ ገዢ ፓርቲ ሆነ ተቃዋሚ፣ አማፂ ይሁን ሰላማዊ ታጋይ ጠብ ልዩነትን በድርድር ለመፍታት ፈቃደኛነኝ የማይል የለም።አንዳቸዉም አንድም ጊዜ የትኛዉንም ልዩነት በድርድር ፈተዉ ግን አያዉቁም።ለምን

Äthiopien  | Bürgerkrieg
ምስል Amanuel Sileshi/AFP/Getty Images

የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ድርድር ያዉቃሉ?

This browser does not support the audio element.

ሰሜን ኢትዮጵያን የሚያወድመዉ ጦርነት እንዲቆም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣የአፍሪቃ ሕብረት፣የአዉሮጳ ሕብረትና ዩናይትድ ስቴትስ እየጠየቁ ነዉ።የዩናይትድ ስቴትሱ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር ከዋሽግተን አዲስ አበባ፣ ከናይሮቢ ፕሪቶሪያ እየባተሉ ነዉ።ድርድር ግን እስካሁን ከደብዳቤ፣ ቲዊተር  መግለጫ ሌላ በገቢር የለም።ለሳምንቱ ማብቂያ ተቀጥሮ የነበረዉም-ያዉ በቀጠሮ ቀርቷል።ተፋላሚ ኃይላት በየዉጊያዉ ለሚማግዱት ሕዝብ ስለድርድሩ እንዴትነት ስለመሰርዝ መቀጠሉ፣በግልፅ መናገሩን እስካሁን አልፈቀዱም።ጦርነቱ፣ የክተት ጥሪ፣ መወነጃጀሉም ቀጥሏል።ለምን? ሁለት ተንታኞችን ጋብዘናል ላፍታ አብረን እንጠይቅ።
ሑለት ዓመት ሊደፍን ሳምንታት የቀረዉን ጦርነትና ሰበቡን የሚያጠናዉ የቤልጂጉ የግንት ዩኒቨርስቲ አጥኚ ቡድን እንደሚለዉ ጦርነቱና ዳፋዉ በብዙ መቶ ሺሕ የሚቆጠር ሰዉ ሳይፈጅ አልቀረም።ዘ ጋርዲያን የተባለዉ ጋዜጣ የጠቀሳቸዉ የአጥኚዉ ቡድን ባልደረባ ፕሮፌሰር ያን ንይሰን «ጦርነቱ  የአፍሪቃ በመሆኑ (እስከፊ መዘዙ) ይረሳል» ይላሉ።አላበሉም።ከአፍሪቃም በጦርነት የደመቀ ታሪካ ያላት የኢትዮጵያ ነዉ ጦርነቱ።
ባለፉት 50 ዓመታት ከናቅፋ ተራሮች እስከ ቀብሪ ዳሐር ሜዳዎች፣ ከሽሬ እንደ ስላሴ ሸለቆዎች እስከ መዘዞ ዋሻዎች፣ ከአይጋ ኮረብቶች እስከ ገዛ ገረስላሴ ጉብታዎች የረገፈዉን ወጣት የሚዘክረዉ የለም።እኒያ «የረሱ» ብዙ መቶ ሺዎች የከፈሉት መስዋዕትነት የየዘመኑን ገዢዎች የገዢነት ዕድሜ ከማራዘም፣ ወይም አዳዲስ ገዢዎችን ቤተ መንግስት ከመዶል ባለፍ በየዘመኑ እንደሚባለዉ ለሐገር አንድነት፣ለሕዝብ ነፃነት፣ ለሰላም ብልፅግና ቢሆን ኖሩ የመከፋፈል ስጋት፣ የዉጊያ፣ ግጭት እልቂት የረሐብ በሽታ መቅሰፍት ዛሬ የኢትዮጵያዉያን ርዕስ ባልሆነ ነበር።
ኢትዮጵያ ዛሬም በድሕነት፣ ረሐብ፣ በሽታ፣ ስደት፣ ተመፅዋችነት ከሁሉም በላይ በጦርነት እልቂት የዓለም ርዕስ ናት።ከተባበሩት መንግስት ድርጅት እስከ ዩናይትድ ስቴትስ ከአፍሪቃ እስከ አዉሮጳ ሕብረቶች ካንጀትም ሆነ ካንገት የሰሜኑ ጦርነት በድርድር እንዲቆም ሲጎተጉቱ ነበር።ባለፈዉ ሳምንት ማብቂያ ደቡብ አፍሪቃ ዉስጥ ይደረጋል ተብሎ የነበረዉ ድርድር ጉትጎታ፣ግፊት ጥረቱ ለዉጤት የመብቃቱ ምልክት፣በጦርነቱ ለተጎዳዉ ኢትዮጵያዊ ደግሞ የሰላም ተስፋ ጭላንጭል መስሎ ነበር።ከመምሰል አለማለፉ እንጂ ቁጭቱ።ቃለ መጠይቅ፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ቀዉስና ድርድር
የኢትዮጵያ መንግስት እና ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት)ያደርጉታል የተባለዉ ድርድር ላልተወሰነ ጊዜ ለመራዘሙ ከሁለቱ ወገኖች በይፋ የተሰጠ ምክንያት የለም። ስለጉዳዩ እናዉቃለን የሚሉ ዲፕሎማቶች እንዳሉት ግን ምክንያቱ «የሎጅስቲክስ ችግር» ነዉ።
ተደራዳሪና  አደራዳሪዎች ምክንያቱን  በግልፅ አለመናገራቸዉ መገናኛ ዘዴዎችንና ተንታኞችን ግራ ያጋባ፣ ለግምትና ለስሚ ስሚ ትንታኔ የዳረገም ነዉ።
የቀድሞዉ ኢሕአፓ ታጋይ፣የኢሕዲን መስራችና የፖለቲካ ተንታኝ ያሬድ ጥበቡ የአደራዳሪዎች በተለይም የአፍሪቃ ሕብረት ስንፈት ይሉታል።የቀድሞዉ ፖለቲከኛ፣ ያሁኑ የፖለቲካ ተንታኝና ደራሲ አንዳርጋቸዉ ፅጌም ዝርዝር መረጃ የላቸዉም ይሁንና «ሎጂስቲክስ» ምክንያት ሊሆን አይችልም ባይናቸዉ።
ከእንግዲሕም ቢሆን አቶ ያሬድ እንደሚሉት ድርድር እንጂ ጦርነት አማራጭ አይደለም።አቶ አዳርጋቸዉም ድርድሩ አስፈላጊ ነዉ ባይ ናቸዉ።
ደቡብ አፍሪቃ ላይ ተቀጥሮ የነበረዉ ድርድር መሰረዙ በተነገረ ማግስት ትናንት ሕወሓት ሙሉ ክተት አዉጇል።ፓርቲዉ የሚቆጣጠረዉ የወያኔ ድምፅ  ባሰራጨዉ ዘገባ መሠረት ህወሓት «ወሳኝ ደረጃ ላይ ደርሷል» ላለዉ ጦርነት የትግራይ ሕዝብ በሙሉ እንዲከትት ጠይቋል።የክተት ጥሪዉን አቶ አንዳርጋቸዉ ለድርድሩ መፍረስ «ተጠያቂዉ ህወሓት ነዉ»ለማለታቸዉ ማረጋገጪያ ያደርጉታል።ኢትዮጵያ አዳኝ ያጣች ሐገር
                                  
አቶ አንዳርጋቸዉና አቶ ያሬድ ያንድ ዘመን ትዉልዶች፣ ያንድ ትምሕርት ቤት ተማሪዎች፣ ባንድ ወቅት ያንድ ፓርቲ ፖለቲከኞች ወይም ታጋዮች ነበሩ።ሕወሓትንም በየአጋጣሚዉ በቅርብ ያዉቁታል።ስለ ፓርቲዉ ፖለቲካዊ አቋም፣ስልትና ሴራ የሚሰጡት አስተያየት ግን ለየቅል ነዉ።
ድርድር በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ መፍትሔ ሆኖ ያዉቃል? ሕወሓት ይባል ብልፅግና፤ ኢሐዴግ ይሁን ደርግ፣ ገዢ ፓርቲ ሆነ ተቃዋሚ፣ አማፂ ይሁን ሰላማዊ ታጋይ ጠብ ልዩነትን በድርድር ለመፍታት ፈቃደኛነኝ የማይል የለም።አንዳቸዉም አንድም ጊዜ የትኛዉንም ልዩነት በድርድር ፈተዉ ግን አያዉቁም።ለምን? ሁለቱ የቀድሞ ፖለቲከኞች ባለፈዉ ታሪክ  ይስማማሉ።ባሁኑ ጦርነት መነሻና ምክንያት ግን ይቃረናሉ።
ምክንያቱ ምንም ሆነ ምን፣ ጠብ ጫሪዉ ማንም ሆነ ማን ተፋላሚዎች ጦርነቱን አሉት አሉትና እንደራደር አሉ።ድርድሩን አወሩ፣ ፃፉለትና እንደገና በጦርነቱ ቀጠሉ።ቢያንስ እስካሁን።እስከ መቼ? አናዉቅም።ኢትዮጵያዊዉ ግን ግራ ቀኝ ተሰልፈዉ ይረግፋል።
ነጋሽ መሐመድ

አቶ ያሬድ ጥበቡ፣ የቀድሞ ፖለቲከኛና የፖለቲካ ተንታኝምስል Government Communication Affairs Office/Kewot Woreda
አቶ አዳርጋቸዉ ፅጌ፣ የቀድሞ ፖለቲከኛ፣ የፖለቲካ ተንታኝና ደራሲምስል Andargachew Tsige
የአስከፊዉ ጦርነት ገፈት ቀማሾች ሴቶችና ሕፃናት ናቸዉ።ምስል Eduardo Soteras/AFP/Getty Images

ሸዋዬ ለገሰ
         


 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW