1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ የጦርነት ምድር

ሰኞ፣ ጥቅምት 22 2014

ይኸ ሁሉ ሕዝብ አልቆ፣ይሕ ሁሉ ግፍ ተፈፅሞ፣ ይሕ ሁሉ ሕዝብ ተፈናቅሎ፣በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር የደኻይቱ ሐገር ጥሪት ወድሞ፣ ወንጀሎች እንደሚጠየቁ እየታወቀም የተፋላሚ ኃይላት መሪዎችና ደጋፊዎቻቸዉ ዛሬም የሰላም ጭላንጭል አላሳዩም።ይልቅዬ ሕዝቡን ለተጨማሪ ዉጊያ እየቀሰቀሱ፤ ለቀጣይ ዘመቻ እያደራጁ፣አንዱ የሌላዉ ዉድቅ መቃረቡንም እየነገሩን ነዉ

Äthiopien | Straßenszene in Dessie
ምስል Tiksa Negeri/REUTERS

የእልቂት፤ፍጅቱ አዙሪት ማብቂያ ይኖረዉ ይሆን?

This browser does not support the audio element.

 

ኢትዮጵያዉያን ያዉ መቼም እንደአብዛኛዉ ዓለም ሥለ ሠላም፣ ሥለ ፍትሕ፣ ሥለ እኩልነት አስፈላጊነት፣ ከሁሉም በላይ ስለግጭት ጦርነት መጥፎነት መስበክ-መሰበካቸዉ፣ መናገር-ማድመጣቸዉ፣ መፃፍ-ማንበባቸዉ፣መወያየታቸዉም አልቀረም።በኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ታሪክ የተፈራረቁ ገዢዎች ግን ሰለሳላም ከመስበክ ባለፍ ሐገር-ሕዝብ፣ ተከታያቸዉን ከእልቂት-ፍጅት፣ከረሐብ ድሕነት አላቃዉት አያዉቁም።ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ፍፃሜ ወዲሕ ኢትዮጵያ ከ30 የሚበልጡ ከፍተኛ ግጭቶችንና ጦርነቶችን አስተናግዳለች።ዛሬም የከፋ ጦርነት ላይ ናት።በረሐብተኞች ቁጥር፣ በተፈናቃይ ስደተኞች ብዛት በተደጋጋሚ የዓለምን ክብረ ወሰን ሰብራለች።ዛሬም ብዙ ሺዎች ያልቁ፣ ሚሊዮኖች ይራቡ፣ይፈናቀሉ ይሰቃዩባትል።የሰላም ጥላቻ፣ ፍርሐት፣ ጭካኔ፣ እልሕ፣ድንቁርና ወይስ መርገምት ይሆን?

የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግስታት ወታደሮች፣ የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሺያ ባንድ ወገን የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ና ተባባሪዎቹ በሌላ ወገን ሆነዉ ትግራይ ላይ የገጠሙት ጦርነት ዓመት ሊደፍን 3 ቀን ቀረዉ።በጦርነቱ የተገደለና የቆሰለዉን ሰዉ ብዛት እስካሁን በትክክል የቆጠረዉ የለም።

የሩቅ ገማቾች እንደሚሉት ግን በመቶ ሺሕ የሚቆጠር ሰዉ (ወታደርም ሰላማዊም) አልቋል።ከሟቹ ቁጥር የሚበልጥ ሰዉ ቆስሏል።የመብት ተሟጋቾች እንደሚሉት ከሟች-ቁስለኛዉ ቁጥር ማየል ሌላ ሕፃናትን በየዉጊያዉ ከመማገድ፣ ሴቶችን አስገድዶ በፈረቃ እስከ መድፈር፣ሠላማዊ ሰዎችን በጅምላ ከመረሸን፣ ግለሰቦችን እስከመሰወር፣ የሐይማኖት ተቋማትን ከማጥፋት ታሪካዊ ቅርስ፣ ሐብት ንብረትን እስከመዝረፍ የሚደርሱ ወንጀሎች በሁሉም ወገኖች ተፈፅመዋል።

ምስል private

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ምክር ቤትና የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በጋራ ያደረጉትን ጥናት ዉጤት የፊታችን ሮብ በይፋ ለማሳወቅ ቀጠሮ ይዘዋል፤ ጦርነቱ የተጀመረበት ሌሊት አንደኛ ዓመት ሊዘከር ሰዓታት ሲቀሩት ማለት ነዉ።

የጥናቱን ዉጤት የምናዉቀዉ ያዉ ዘገባዉ ይፋ ሲሆን ነዉ።የደረሰዉን የሰብአዊ መብት ጥሰት ከብዙዎቹ የመብት ተሟጋቾች ቀደም ብሎ የዘገበዉ አምንስቲ ኢንተርናሽናል ነዉ።የመብት ተሟጋቹ ድርጅት የምሥራቅ አፍሪቃ አጥኚ ፍሰሐ ተክሌ እንደሚሉት አንዳዶቹ በደሎች በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያስጠይቁ ናቸዉ።

የስደተኛ ተፈናቃዩ ቁጥር ከ3 እስከ 4 ሚሊዮን ይደርሳል።ዉጊያዉ ዛሬ ደሴ-ኮምቦልቻ፣ ከሚሴ መድረሱን የዓይን ምስክሮች እየተናገሩ ነዉ።ይኸ ሁሉ ሕዝብ አልቆ፣ይሕ ሁሉ ግፍ ተፈፅሞ፣ ይሕ ሁሉ ሕዝብ ተፈናቅሎ፣በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር የደኻይቱ ሐገር ጥሪት ወድሞ፣ ወንጀሎች እንደሚጠየቁ እየታወቀም የተፋላሚ ኃይላት መሪዎችና ደጋፊዎቻቸዉ ዛሬም የሰላም ጭላንጭል አላሳዩም።ይልቅዬ ሕዝቡን ለተጨማሪ ዉጊያ እየቀሰቀሱ፤ ለቀጣይ ዘመቻ እያደራጁ፣አንዱ የሌላዉ ዉድቅ መቃረቡንም በየመገናኛ ዘዴዎቻቸዉ እየነገሩን ነዉ።ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ትናንት አስተላለፉት ከተባለዉ መልዕክት ጥቂቱ።

የቀድሞዉ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ፃድቃን ገብረትንሳኤ ባንፃሩ «ድርድር የለም አሉ።» ትናንት።«ቢኖርስ ከማን ጋር?» ጠየቁ።

የጤና ይሆን?አናዉቅም።የምናዉቀዉ የጦርነቱ አዉድ እየሰፋ፣ የሚሞት፣የሚቆስል፣ የሚጎዳዉ ሕዝብ ቁጥር እየጨመረ፣ የሚጠፋዉ ሐብት ንብረት መጠን እየናረ መምጣቱን ነዉ።የምናዉቀዉ ተፋላሚ ኃይላት በተለይ ለሰላማዊ ሰዎችና ተቋማት ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የመብት ተሟጋቾች በተደጋጋሚ ያደረጉት ጥሪ ጆሮ-ዳባ ልበስ መባሉን ነዉ።ጥያቄዉ ዛሬም ቀጥሏል።

የመጠፋፋቱ ዉጊያ፣ፉከራ፣ዛቻ ቀረርቶዉም ያዉ እንደሰማነዉ አላባራም። የዉይይት ድርድር አማራጭም ተደፍልቋል። ኢትዮጵያዊዉ የሕግ ባለሙያና የቀድሞዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለስልጣን ባይሳ ዋቅ ወያ በቀደም «አዉሬነት» ብለዉት ነበር።

የሚገርመዉ የሐገር ሽማግሌ፣ አብዛኛዉ ምሁር፣ የሐይማኖት አባት የሚባሉ ወገኖችም አንድም ከየተፋላሚ ወገኖች ጋር መለጠፋቸዉ፣ አለያም የኃይለኞችን የመገዳደል፣መጠፋፋት ዛቻ ፉከራ፣የደካሞችን ዋይታ ለቅሶን እንደተራዉ ሰዉ ለማድመጥ-ተራ መያዛቸዉ ነዉ።

ምስል picture alliance/AP

ኢትዮጵያ በ1933 ከኢጣሊያ ወረራ ነፃ ከወጣች በኋላ በትንሽ ግምት የሶማሌ፣የሱዳን፣ኋላ የኤርትራ መንግሥታት በቀጥታ የተከፋሉበት፣ከ50 የሚበልጡ ሸማቂዎች የተሳተፉበት ከ30 በላይ ትላልቅ ግጭቶችን ወይም ጦርነቶችን አስተናግዳለች።የቀዳማይ ወያኔ አመፅ፣በ1955 የባሌ ኦሮሞዎች አመፅ፣በ1956 የኢትዮ-ሶማሊያ የድንበር ግጭት፣የኤርትራ ክፍለ ግዛት ጦርነት።

ከ1966 እስከ 1983 የኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት፣ የኢትዮጵጵያ መንግስት፣ጀበሐ፣ ሻዕቢያ፣ ኢሕአፓ፣ መኢሶን፣ ኢድሕ፣ሕወሓት፣ብአዴን፣ ምዕራብ ሶማሊያ፣ ኦነግ፣ አነግ፣ኦብነግ ወዘተ የተሳተፉባቸዉ ጦርነቶች ተደርገዋል።

በየጦርነቱ  ሺዎች ረግፈዋል።ሚሊዮኖች ተፈናቅለዋል፣ ተሰደዋል።ተርበዋል።እስከ 1980ዎቹ በነበረዉ ጊዜ በየአካባቢዎቻቸዉ የነበሩ ተቀናቃኞቻቸዉን በጦርነት ደፍልቀዉ ወይም በየአካባቢዎቻቸዉ አብጠዉ የኢትዮጵያ መንግስት ጠንካራ ተፋላሚዎች መሆናቸዉን ያረጋገጡት ሻዕቢያና ሕወሓት በ1983 የአስመራና የአዲስ አበባ አብያተ መንግስታት ሲቆጣጠሩ የዘመናት ጦርነት-እልቂት ፍጅት፣ ሶቆቃዉ ፍፃሜ መሆኑን አዉጀዉ ነበር።

የያኔዉ የሽግግር መንግሥት ፕሬዝደንትና የኢሕአዴግ ሊቀመንበር መለስ ዜናዊ።ሰኔ 1983።አሉ እንጂ በርግጥ አላደረጉትም ወይም ማድረግ አልቻሉም።አዲስ የመሰረቱት የሽግግር መንግስት ዓመት ሳይሞላዉ የሽግግር መንግስቱን ከመሰረቱት የፖለቲካ ቡድናት ሁለተኛዉና ትልቁ ከነበረዉ ከኦነግ ጋር አዲስ ዉጊያ ገጠመ።

ከጥቂት ዓመታት በኋላ ከሶማሊያዉ አል ኢትሐድ ጋር ሌላ ግጭት።በሰባተኛ ዓመቱ ደግሞ በ«ሕይወት-ደም ዉሁድ የተለሰነ» ወዳጆች ይባሉ የነበሩት የአዲስ አበባና የአስመራ አዳዲስ ገዢዎች የሁለቱን ሐገር ሕዝብ ከዘግናኛ ጦርነት ሞጀሩት።1990።

ኢትዮጵያ የባሕር በሯን፣ ሰሜናዊ ግዛትዋንም አጥታ፣እስከዚያ ዘመን በነበረዉ ጦርነት የተሰዋ ዜጋዋን ክብር ነፍጋ፣በሕይወት የተረፉትን ወታደሮቿን «የደርግ» እያሰኘች ሜዳላይ በትናም ካዲስ ጦርነት መዘፈቋ ለታዛቢዎች ሲበዛ ግራ፣ ለኢትዮጵያዉያን አሳዛኝ ነበር።

የኢትዮጵያና የኤርትራ መሪዎች ለጦርነቱ የሰጡት ምክንያት ግራ ያጋባዉ አንድ የጀርመን ዕዉቅ መፅሔት ያኔ ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂና ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊን የሚመስል ካርቱን ለጥፎ «ሁለቱ መላጦች ላንድ ሙሽጥ ይጣላሉ» ዓይነት ፃፈ።ድርድር ወይይትን እንቢኝ ማለታቸዉን ደግሞ «አንዱ የሌላዉን አናት ካልፈረከሰ---» እያለ ተሳለቀ።

አቶ ባይሳም በቀደም  በተለይ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ባሕል አንዱ ሌላዉን «ካላንበረከከ» በሚል ቃል ደገሙት በቀደደም።መፅሔቱ እንደገመተዉ፣የያኔዉ ዉጊያ በተጀመረ በሁለተኛ ዓመቱ አንዱ-የሌላዉን አናት «ሲፈረክስ» አበቃ።ጦርነቱ ግን ቂም-በቀል እያመረቀዘ መቀጠሉን አምና ትግራይ ላይ አረጋገጠ።እና ኢትዮጵያ ዛሬም ጦርነት ላይ ናት።

ምስል Million Haileselassie /DW

የጦርነቱ ሰበብ ምክንያት ከዚሕ ቀደም እንደነበሩት ጦርነቶች ሁሉ ብዙ ነዉ።ለቀድሞዎቹም ሆነ ላሁኑ ጦርነት መሰረታዊዉ ምክንያት ግን የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች  ለመነጋገር ፍቃደኛ አለመሆናቸዉ፣ ወይም  አለማወቃቸዉ፣ ወይም ለስልጣን ከሆነ ያለቀዉ ይለቅ የማለት ጅልነታቸዉ ማየሉ ነዉ።

ተፋላሚዎቹ ለጦርነት ተደራጅተዉ፣ በጦርነት ኖረዉ፣  በጦርነት ቤተ መንግስት ሲገቡ ጦርነት «አንገሸገሸን» ያሉት ግን በጦርነት የቀጠሉት ፖለቲከኞችና እነሱዉ የፖለቲካ ሐሁ፣ የዉጊያ «ግራ-ቀኝ» ያስቆጠሯቸዉ የቀድሞ ተከታዮቻቸዉ መሆናቸዉ ነዉ-ለሩቁ ታዛቢ ግራ አጋቢ፣ላንዳዱ ድንቁርና፣ ለቅርቡ አሳዛኝ፣ ተስፋ አስቆራጭ የመሆኑ ሐቅ።

እስከ አምና በነበሩት ግጭት ጦርነቶች ባንድ ወይም በሌላዉ ወገን በጎሳ የተደራጁ ኃይላት መሳተፋቸዉ አያነጋግርም።ያሁንን ያክል ጎሳን ከጎሳ ያናከሰ፣ አንዱን ወገን በሌላዉ ጎሳ ላይ እንዲዘምት በግልፅ የሚቀሰቀስበት ጦርነት ኢትዮጵያ ስታስተናግድ ግን በቅርብ ዘመን ታሪኳ ያሁኑ የመጀመሪያዉ ሳይሆን አይቀርም።

ብዙ ታዛቢዎች እንደሚሉት ተፋላሚን በየጎሳዉ ያሰለፈዉ ዉጊያ ባንዱ አሸናፊነት ቢጠናቀቅ እንኳ ጦርነቱ ባጭር ጊዜ መቆሙ ያጠራጥራል።ጥርጣሬዉ ያሰጋል።

የተፋላሚ ኃይላት መሪዎች የሚያፋጁትን ሕዝብ ለማደናቆር ዘንድሮ በ21ኛዉ ክፍለ-ዘመንም «ወደ ጦርነት የገባነዉ ተገደን ነዉ» ይላሉ።አታለዉ፣አስገድደዉ፣በጎሳ አነሳስተዉ በሚያፋጁት ሕዝብ ላይ ላደረሱት ግፍ-በደልም ተገደዉ ለፍርድ ካልቀረቡ አጠራጣሪዉ ስጋት ትዉልድ ቢቀያየርም  መቀጠሉ አይቀርም።

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶ ስለሺ

 

 

 

 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW