ኢትዮጵያ ፌደራሊዝም እና ግጭት
ሰኞ፣ መስከረም 8 2010
የወልቃይት ጠገዴ ወይም ፀገዴ የአስተዳደር ጥያቄ በአደባባይ አሰልፎ፤ አጋጭቶ፤ሕይወት-አካል፤ ንብረት አጥፍቶ ጋብ ማለቱ ሲነገር፤ የቅማንት ሕዝብ የወደፊት አስተዳደር በሕዝብ ድምፅ እንዲወሰን ያስገደደዉ ጥያቄ ጋመ።የኮንሶ አስተዳደር ጥያቄ በጫረዉ ግጭት ያጠፋዉ ሕይወት፤ አካል ንብረት ተሰልቶ ሳያበቃ ለዓመታት ብልጭ ድርግም የሚለዉ የቡርጂ እና የጉጂ ኦሮሞ የአስተዳደር ዉዝግብ ዳግም ተቀጣጠለ።ኦሮሚያ፤ አማራ እና ደቡብ ኢትዮጵያን ያበጠዉ ተቃዉሞ እና ግጭት ቀዝቀዝ ማለቱ ሲነገር ለዓመታት የተዳፈነዉ የኦሮሚያ እና የኢትዮጵያ ሶማሌ መስተዳድሮች ዉዝግብ ደም ያፋስስ፤ ያበቃቅል፤ሕዝብ ያፈናቅል ገባ። ከእንግዲሕስ?
ኢትዮጵያ አስራ-አራተኛ ክፍለ ሐገሯን ኤርትራን ቀንሳ፤ በብሔር ወይም በቋንቋ ላይ በተመሠረተ በአስራ አራት የአስተዳደር ክልሎች እንድትዋቀር በ1983 ሲወሰን የኢትዮጵያ ተማሪዎች ከ1960ዎቹ ጀምሮ የታገሉ፤የሞቱ፤የታሰሩለት የብሔር ብሔረሰቦች ጥያቄ መልስ አገኘ አሰኝቶ ነበር። አወቃቀሩን ያጠናዉ ኮሚቴ ሰብሳቢ የኦሮሞ ነፃ አዉጪ ግንባር (ኦ,ኤል,ፍ) ከፍተኛ ባለሥልጣን ያኔ ለጋዜጠኞች በሰጡን መግለጫ አስተዳደሩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድ የተሻለዉ እና ብቸኛዉ አማራጭ እንደሆነ ማስረዳታቸዉን አስታዉሳለሁ።የያኔዉ የኦነግ ምክትል ዋና ፀሐፊ ሌንጮ ለታም አልዘነጉትም።
የኦሮሞ ነፃ አዉጪ ግንባር ዛሬ ለኢትዮጵያ መንግሥት አሸባሪ ድርጅት ነዉ።ድርጅቱ በበላይነት በመራዉ ጥናት ሥራ ላይ የዋለዉ የፌደራል ሥርዓት ግን ዛሬም ለኢትዮጵያ መንግስት የአስተዳደሩ አስኳል፤ የአመራሩ መሠረት ነዉ።የኢትዮጵያ መንግስትን የሚቃወሙ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በብሔር ላይ የተመሠረተዉን ፌደራላዊ ሥርዓት ይደግፋሉ።
ኢትዮጵያ ግን ያ ሥርዓት ከፀናባት ጊዜ ጀምሮ 26 ዓመታት የተጓዘችዉ፤ የመጤና የነባሮች ግጭት፤ የአማራና የኦሮሞ ግጭት፤ የአፋርና የኢሳ (ሶማሌ) ግጭት፤ የጉጂና ቡርጂ ግጭት፤ የሱማሌና የኦሮሞ ግጭት፤ የኑዌርና የአኝዋክ ግጭት ወዘተ እያለች፤ በግጭት ማግሥት ግጭቶን እያስተናገደች ነዉ። በየግጭቶቹ የተገደሉ ሰዎች አስከሬኖችን እየቆጠረች፤ የቆሰሉ እና የተፈናቀሉ ዜጎችዋን እያሰላች ነዉ።
የጉራጌና የስልጤ ዉዝግብ፤ የአማራና የትግሬ ዉዝግብ፤ የኮንሶ ጥያቄ፤ የቅማንት ጥያቄን ስታስማም ነዉ።ሰሞኑንም በኢትዮጵያ ሶማሌ እና በኦሮሚያ መስተዳድሮች አዋሳኝ ድንበሮች ላይ በተከሰተዉ ግጭት የዜጎችዋን ደም ጭዳ ማድረግ ግድ ብሏታል።ከጂጂጋ እስከ ሞያሌ፤ ከአወዳይ እስከ ባሌ በደረሰዉ ግጭት በትንሽ ግምት በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸዉ ተዘግቧል።ከሐምሳ ሺሕ በላይ ኦሮሞዎች ተፈናቅለዋል።
የኢትዮጵያ ሶማሌ እና የኦሮሚያ መስተዳድር ባለሥልጣኖች ለሕዝብ ጩኸት ተገቢዉን መልስ ከመስጠት ይልቅ እራሳቸዉም በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ የቃላት ጦርነት ገጥመዉ ነበር።በመሠረቱ ኦሮሚያን የሚያስተዳድረዉ የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕደዴ) የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ ኢሕአዴግ አባል ነዉ።የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልልን የሚያስተዳድረዉ የኢትዮጵያ ሶማሌ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶሕዴፓ) የኢሕአዴግ አጋር ፓርቲ ነዉ።
የአንድ ገዢ ፓርቲ አባልና አጋር ፓርቲዎችን የሚወክሉት የሁለቱ መስተዳድሮች ባለሥልጣናት የተለዋወጧቸዉን ቃላት ያነበበ የሕዝብ አስተዳዳሪ መሆናቸዉን ይጠራጠራል።ተፈናቃዩ ደግሞ ጠየቁ «መንግስት አለወይ» ብለዉ።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ መልስ ሰጡ ።ግን ዘገዩ። ለምን?ሌላ መልስ አልባ ጥያቄ። ጠቅላይ ሚንስትሩ እንዳሉት ግጭቱን የቀሰቀሱት «የተበላሹ» ያሏቸዉ ታጣቂዎች፤ፀረ ሕዝብ እና ፀረ ልማት ኃይሎች ናቸዉ።መሠረታዊዉ የሚባል ምክንያት ግን አልጠቀሱም።የቀድሞዉ የኦነግ መሪ እና ያሁኑ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ) መሥራች እና መሪ አቶ ሌንጮ ለታ እንደሚያምኑት ግን የግጭቱ ቀስቃሽና አራማጅ በኢትዮጵያ ሶማሌ መስተዳድር የሠፈረዉ ልዩ ፖሊስ የሚባለዉ ታጣቂ ኃይል ነዉ።
«አሰባሳቢ ማንነት በሐገር ልጅነት» የሚል መፅሐፍ ያሳተሙት የፖለቲካ ተንታኝ አቶ ዩሱፍ ያሲንም የአቶ ሌንጮን አስተያየት በከፊል ይጋራሉ።
ኢትዮጵያን በየጊዜዉ ግራ ቀኝ የሚያላጋዉ የጎሳ ግጭት፤ የአስተዳደር ዉዝግብ እና ጥያቄ ሐገሪቱ የምትከተለዉ በብሔር ላይ የተመሠረተ የፌደራዊ አስተዳደር ሥርዓት ዉጤት ነዉ የሚሉ አሉ።የፖለቲካ ተንታኝ ዩሱፍ ያሲን ለኢትዮጵያ ከፌደራዊ ሥርዓት ዉጪ የተሻለ አማራጭ የለም ባይ ናቸዉ።ያ ፌደራዊ ሥርዓት መመስረት ያለበት ግን በሳቸዉ አገላለፅ በዜግነት ላይ ነዉ።
አቶ ሌንጮ ለታ ግን ኢትዮጵያን ላለፉት 26 ዓመታት የሚያብጠዉ የጎሳ ግጭት፤የአስተዳደር ዉዝግብ እና የማንነት ጥያቄ በምትከተለዉ በብሔር ላይ የተመሠረተ የፌደራል ሥርዓት ምክንያት የመጣ አይደለም።በብሔር ላይ የተመሠረተዉ ፌደራዊ ሥርዓት ዴሞክራሲያዊ ባለመሆኑ እንጂ።
ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ እንዳሉት መንግሥታቸዉ በኢትዮጵያ ሶማሌ እና በኦሮሚያ መስተዳድሮች አዋሳኝ ድንበሮች ለተነሳዉ ግጭት ተጠያቂ ያላቸዉን ወገኖች ለፍርድ ያቀርባል።በሁለቱ አዋሳኝ ክልሎች የሚገኙ መንገዶችን የፌደራሉ ፀጥታ አስከባሪዎች ይቆጣጠራሉ።የተፈናቀሉትን ሰዎች ይረዳልም።
አቶ ዩሱፍ ያሲን ይሕን እንደ ጊዚያዊ እንጂ እንደ ዘላቂ መፍትሔ አያዩትም።
አቶ ሌንጮ ለታም ፖለቲከኞች ቆም ብለዉ ካላሰቡ እስካሁን ከታየዉ ግጭትና ዉዝግብ የከፋ መዘዝ ይከተላል ባይ ናቸዉ።
የኢትዮጵያ ፌደራዊ መንግስት ግጭቱን ለማስቆም ጣልቃ መግባቱን በይፋ ያስታወቀዉ ትናንት ነዉ።እስከ ትናንት የት ነበር የሚለዉ ጥያቄ መልስ አይታወቅም።የሚታወቀዉ ግጭት፤መበቃቀሉ ከኢትዮጵያ አልፎ ጅቡቲ፤ ከጅጅጋ ተሻግሮ ሐርጌሳ መቀጠሉ ነዉ።አቶ ዩሱፍ በዚሁ ከቀጠለ «ሁሉን የሚያቃጥል » ይሉታል። አቶ ሌንጮ ለታ ደግሞ «መፍረስ።»
ከዚሕ ይሰዉረን።
ነጋሽ መሐመድ
ሸዋዬ ለገሠ