1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምህዳር፣ ሰላማዊ ትግልና እሥር

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 4 2016

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር ሰላማዊነቱ እየቀዘቀዘ እና እየተዳከመ፣ በአንፃሩ የጫካ ትግል እያደገ መሄዱን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ትናገሩ ። የሰላማዊ ሰልፍ ጥሪውን ተከትሎ በርካታ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ለእስር ተዳርገዋል ።

Äthiopien Region Oromia
ምስል Seyoum Getu/DW

መልኩን እየቀየረ ነው የተባለው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር

This browser does not support the audio element.

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር ሰላማዊነቱ እየቀዘቀዘ እና እየተዳከመ፣ በአንፃሩ የጫካ ትግል እያደገ መሄዱን የኢትዮጵያ  የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ትናገሩ ። ሰሞኑን አዲስ አበባ ውስጥ ሊደረግ ታቅዶ በመንግሥት ክልከላ የተጣለበት የሰላማዊ ሰልፍ ጥሪን ተከትሎ በርካታ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ለእስር ተዳርገዋል ። የሰልፉ አስተባባሪ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ፣ አባላት፣ እና ሌሎችም መታሰራቸውን ፓርቲዎችም ሆኑ መንግሥት በየፊናቸው ዐስታውቀዋል ። የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በመንግስት የሚወሰደውን ርምጃ ኮንነው ተቃውመዋል ። በመንግሥት ክልከላ ስለተጣለበት የሰላማዊ ሰልፍ ጥሪን በተመለከተ የጋራ ምክር ቤቱ አቋሙን ገልጿል ። የአዲስ አበባ ወኪላችን ሰለሞን ሙጬ ዝርዝር ዘገባ አለው ።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ደስታ ዲንቃ «የእኛ ፖለቲካ ከጊዜ ወደ ጊዜ አሳሳቢነቱ እየጎላ፣ የሰላማዊ ሜዳው እየቀዘቀዘ እና እየተዳከመ የጫካ ትግሉ ደግሞ በተቃራኒው እያደገ የሄደበት ሁኔታን ነው የምናየው» ብለዋል።

መንግሥት «አዲስ አበባን የሁከትና የብጥብጥ ማዕከል ለማድረግ የሽብር ተልዕኮ ተቀብለው በህቡዕ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 97 ተጠርጣሪዎችን» መያዙንና የሰልፉ መከልከል ዓላማም ይሄው መሆኑን አስታውቆ ነበር።

ከሰልፍ ጥሪው ጋር ተያያዞ የታሠሩት የኢሕአፓ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ከቤተሰቦቻቸው እና ጠበቃ ጋር እንዳይገናኙ ከአዲስ አበባ ውጪ ተወስደው መታሰራቸውን ያስታወቀው ፓርቲው አካልን ነፃ የማውጣት ክስ መመስረቱን ገልጿል። ሰልፉን ሊያስተባብሩ ይችላሉ በሚል የታሠሩ ሌሎች የአዲስ አበባ ወጣቶችም እንዲለቀቁ ፓርቲው ጠይቋል ።

መልኩን እየቀየረ ነው የተባለው  የፖለቲካ ምህዳር

ባለፈው ሳምንት ሕዳር 30 ቀን 2016 ዓ. ም አዲስ አበባ ውስጥ ይደረጋል ተብሎ ነገር ግን በከተማ አስተዳደሩ ክልከላ ከተጣለበት ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ እቅድ ጋር ተያይዞ የሰልፉ አስተባባሪ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ፣ አባላት፣ እና ሌሎችም መታሰራቸውን ፓርቲዎችም ሆኑ መንግሥት በየፊናቸው አስታውቀዋል። 

ባለፈው ሳምንት ሕዳር 30 ቀን 2016 ዓ. ም አዲስ አበባ ውስጥ ሰልፍ ይደረጋል ተብሎ ነበርምስል Seyoum Getu/DW

ይህንኑ የሰልፍ ጥሪ ተከትሎ የተስተዋለውን እሥር በተመለከተ 60 ያህል ሀገር አቀፍ እና ክልላዊ የፖለቲካ ድርጅቶችን ያቀፈውንየኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጠይቀናል። የጋራ ምክር ቤቱ የወቅቱ ሰብሳቢ አቶ ደስታ ዲንቃ የዚህ መነሻ ከሰላማዊ ትግል ይልቅ የጫካ የትጥቅ ትግል እያደገ የመምጣቱ አዝማሚያ መሆኑን ጠቅሰዋል።

"የእኛ ፖለቲካ ከጊዜ ወደ ጊዜ አሳሳቢነቱ እየጎላ፣ የሰላማዊ ሜዳው እየቀዘቀዘ እና እየተዳከመ የጫካ ትግሉ ደግሞ በተቃራኒው እያደገ የሄደበት ሁኔታን ነው የምናየው"

ኹከት እና ብጥብጥ የመፍጠር እንቅስቃሴ ነበር ፣ መንግሥት

መንግሥት ሰላማዊ ሰልፉን የከለከለው በዚሁ ሽፋን "አዲስ አበባን የሁከትና የብጥብጥ ማዕከል ለማድረግ" እንቅስቃሴ መኖሩን ስለደረሰበት መሆኑን ገልጾ ለዚሁ ድርጊት የተንቀሳቀሱ ያላቸውን 97 ተጠርጣሪዎች መያዙንም አስታውቋል። ለእሥር ከተዳረጉት ሰዎች መካከል ሰልፉን ሲያስተባብሩ ከነበሩት አንዱ የኢሕአፓ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ይገኙበታል። ግለሰቡ የት እንደታሰሩና በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ የጠየቅናቸው የኢሕአፓ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ዝናቡ አበራ የሥራ ባልደረባቸው ከአዲስ አበ ውጪ መታሰራቸውን፣ ፍርድ ቤትም አለመቅረባቸውን ገልፀዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ምላሽ እነ ማሳሰቢያ

እናት ፓርቲ "ጦርነት፣ አፈና እና የጅምላ እስሮች" ይቁሙ ሲል በጠየቀበት መግለጫው "መንግሥት ሰላማዊ የመታገያ መንገዶችን እየዘጋ በአንጻሩ ጉልበትን የፖለቲካ መርህ አድርጎ መጠቀም ከጀመረ ሰነባብቷል" ሲል ከሷል።

"ጦርነት ይቁም ሰላም ይስፈን" በሚል ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ጥያቄ ያቀረቡ አካላትን "ምክንያትና ሽፋን በማድረግ በዜጎች ላይ እያከናወነ የሚገኘው" ያለው አፈና እና እሥር የዚህ መሳያ መሆኑንም ገልጿል።

የፓርቲ የቀድሞ ጠቅላይ ጸሐፊ እና የወቅቱ የሕግ እና ሥነ ሥርዓት ክፍል ኃላፊ ታስረውበት እንደነበር ያስታወቀው እናት ፓርቲ የአባላቱን እስር ጨምሮ በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ላይ የተደረገው "የጅምላ አፈሳ" መረጃና ማስረጃ ላይ ያልተመሠረተ፣ ግብታዊ እና ኢ-ሕገ መንግሥታዊ አሰራር ነው" ብሎታል። የፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ያየህ አስማረ ከታሰሩት አመራሮቻቸው አንደኛው መፈታታቸውን ገልፀዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ ከተካሔደው የታላቁ ሩጫ መርሐ ግብር ማግስት ጀምሮ "ዜጎች ላይ የጅምላ እሥር" እየተከናወነ እንደሚገኝ ሰሞኑን የገለፀው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ ( ኢዜማ ) የሰላማዊ ሰልፉን መከልከል አውግዞ አዲስ አበባ ውስጥ "ንጹሃን ዜጎች ላይ የሚፈጸም የጅምላ እስር መቀጠሉን ለመረዳት ችለናል" ሲል "ያለአግባብ ተጠርጥረው ለሥስር የተዳረጉ ንጹሃን ዜጎች በአፋጣኝ እንዲለቀቁ እና ነፃነታቸው እንዲረጋገጥ፣ ሕግና ሥርዓትም እንዲከበር" በማለት ጠይቋል። 

የአዲስ አበባ ከተማ ፊል ገጽታምስል Solomon Muchie/DW

የሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ጥሪዎች

ሰሞነኛውን እሥር ተከትሎ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ለጋራ ምክር ቤቱም ሆነ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አቤቱታዎች በቀጥታ ቀርበዋል ያሉት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ደስታ ዲንቃ እርምጃውን ኮንነዋል።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር ሰላማዊነቱ እየቀዘቀዘ እና እየተዳከመ የጫካ ትግል እያደገ የመሄዱን አሳሳቢነት የገለፀው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰላማዊ ትግል ቦታውን እንዲይዝ ሲጠይቅ ከሳምንት በፊት ጅግጅጋ ላይ በብሔር ብሔረሰቤች በዓል ላይ ንግግር ያደረጉት ርእሠ ብሔር ሣኅለ ወርቅ ዘውዴ፦ ኢትዮጵያ ውስጥ የተስተዋሉ የፖለቲካ ልዩነቶችን «በጠመንጃና በኃይል የመፍታት አማራጭ ማክተም አለበት» ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።

ሰለሞን ሙጬ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW