1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ኢትዮ-ኤይድ፤ የኢትዮጵያ ለአደጋ ስጋት ምላሽ

ሥዩም ጌቱ
ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 7 2017

በቅርቡ ለዝርዝር ዕይታ ለፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ የተመራው ረቂቅ አዋጁ፤ የመንግስት እና የግል ተቋማት ከሚሰጧዋቸው የተለያዩ አገልግሎቶች “ለአደጋ ስጋት ምላሽ ፈንድ” የሚውል ገቢ እንዲሰበስቡ ያስገድድዳል።

የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) ሕንፃ
የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) ሕንፃ።አዲስ አበባ።ምክር ቤቱ አዲስ የቀረበለትን የአደጋ ጊዜ የሚዉል ገንዘብ ማሰባሰቢያ ረቂቅ ደንብ ያጠድቃል ተብሎ ይጠበቃል።ምስል፦ Solomon Muchie/DW

ኢትዮ-ኤይድ፤ የኢትዮጵያ ለአደጋ ስጋት ምላሽ

This browser does not support the audio element.

ኢትዮጵያ ለአደጋ ጊዜ የሚውል ገቢ ከዜጎችዋ እንዲሰበሰብ የሚያስገድደውን ረቂቅ አዋጅ የሐገሪቱ ምክር ቤት ያፀድቀዋል ተብሎ እየተጠበቀ ነዉ።ለኢትዮጵያ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ረቂቅ አዋጅ ላይ የተካተተውና “ለአደጋ ስጋት ምላሽ” የሚውል ገንዘብ ከሁሉም ዜጋ አንዲሰበሰብ የሚያስገድድ ነው፡፡ገንዘቡ ከአገሪቱ ዓመታዊ በጀት ሶስት በመቶ የሚሸፍን ነው ተብሏል፡፡ “ኢትዮ-ኤይድ” በጀት በአሜሪካው እርዳታ ድርጅት USAID የተፈጠረውን የሰብዓዊ ድጋፍ ክፍተት ይሸፍን ይሆን፡፡ሥዩም ጌቱ

በቅርቡ ለዝርዝር ዕይታ ለፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ የተመራው ረቂቅ አዋጁ፤ የመንግስት እና የግል ተቋማት ከሚሰጧዋቸው የተለያዩ አገልግሎቶች “ለአደጋ ስጋት ምላሽ ፈንድ” የሚውል ገቢ እንዲሰበስቡ ያስገድድዳል። ከሀገር ውስጥ የገቢ ምንጭ ለመሰብሰብ በአዋጁ ከተዘረዘሩትም አገልግሎቶች መካከል “የመንግስት እና የግል ድርጅት ተቀጣሪ ሰራተኞች ከሚከፈላቸው የተጣራ ደመወዝ ላይ የሚታሰብ” ክፍያ ማዋጣት የሚለው ይገኝበታል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ከሰራተኞች ደመወዝ እና ከግለሰቦች የሚጠበቀው መዋጮ መጠን፤ ወደፊት ውይይት ከተካሄደበት በኋላ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣ ደንብ የሚወሰን መሆኑን ገልጿል።

ኢትዮጵያ ዉስጥ ድርቅ፣ረሐብና የዉኃ ሙላት በመሳሰሉ የተፈጥሮ አደጋዎችና በሰዉ ሰራጭ ግጭትና ጦርነቶች በየጊዜዉ በርካታ ሰዎች ለችግር ይጋለጡባታል።ምስል፦ Ed Ram/Getty Images

አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡት የኮሚሽኑ የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃ እና ኦፕሬሽን ማስተባበሪያ መሪ ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ፍራኦል በቀለ ‘የኢትዮ-ኤይድ’ ምስረታ ሃሳብ የመነጨው በኢትዮጵያ ሰፊ የድጋፍ ስራ ላይ ተሰማርቶ የነበረው የአሜሪካ ህዝብ ተራድኦ ድርጅት USAID የድጋፍ ስራውን ከማቋረጡም አስቀድሞ ነው፡፡ “ኢትዮጵያ ውስጥ ተደጋግሞ ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች ይከሰታሉ” ያሉን ዶ/ር ፍራኦል አደጋዎቹን ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት አጋር ያሏቸው ድርጅቶች ድጋፍ ሲያደርጉ እንደነበሩ አስታውሰው ይህ ግን ዘለቄታዊነቱ አጠራጥሯል በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ “በተለይም ከውጪ የሚገኙ እርዳታዎችን መፍትሄ አድርገን አንመለከተውም” ያሉት ኃላፊው የውጪ ረጂ ተቋማት አንድም ቅድሚያ የሚሰጡት ነገር ካለ፤ አለበለዚያ ደግሞ በነሱ የፖለቲካ አመለካከል መጓዝ ካልተቻለ እርዳተው በየትኛውም ጊዜ ስለሚቋረጥ በዚህ ላይ መደገፍ አስፈላጊ ሆኖ አልተገኘም ነው ያሉት፡፡ እርዳታ የፖለቲካ ማስፈጸሚያ ማስፈራሪያም ሆኗል በማለት የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ስራውን ከማቆሙም አስቀድሞ በኢትዮጵያ አደጋን መቋቋም የሚስችል እልባት አስቀድሞም በመፈለጉ ኢትዮ-ኤይድ የእርዳታ ድርጅትን ለቋቋም ስራዎች ከተጀመሩ ዓመት መቆጠሩም ተብራርቷል፡፡

በህዝብና መንግስት አቅም እርዳታን በማሰባሰብ ለአደጋ ጊዜ ምላሽ እንዲሆን ማድረግ እንደሚቻልም እምነቱ አለ የሚሉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃ እና ኦፕሬሽን ማስተባበሪያ መሪው ዶ/ር ፍራኦል በቀለ፤ በምስረታ ላይ ያለው የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ምላሽ ድርጅቱ ቀዳሚ ትኩረት በአገር ውስጥ ችግሮች ላይ የሚያተኩር ቢሆንም በሂደት ድንበር ተሻጋሪ አቅምም ለመፍጠር እቅድ አለ ብለዋል፡፡ “አድማሱ እንግዲህ ቅድሚያ የምንሰተው የራሳችንን ዜጎች ቢሆንም በበቂ ሁኔታ ማደራጀት ከቻልን የሚገድበን ጉዳይ የለም” በማለት በጉዳዩ ላይ ከዚህ በፊት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እንደተወያዩበትና አሁንም የሚመለከታቸው አካላት ሀሳቡን በውይይት በማዳበር ላይ ናቸው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ከዚህ በፊት በተለያዩ ጊዜያት በአገር ውስጥ ለሚፈጠሩ ሰውሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች ምላሽ ስሰጥ ቆይቷል፡፡ ለዚህም የመንግስት በጀትና ከአጋር ድርጅቶች የሚሰበሰቡትን ሃብት ተጠቅሟል፡፡ አሁን እየተደራጀ ነው የተባለው ኢትዮ-ኤይድ የአደጋ ስጋት ምላሽ፤ ሁሉም ዜጎችና በየትኛውም ዘርፍ የተሰማሩት ተቋማት ተሳታፊ የሚሆኑበትና ዘላቂ መፍትሄ እንዲሆን መታሰቡም ነው የተብራራው፡፡

የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጉባኤ ላይ።ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራርና “ለአደጋ ስጋት ምላሽ” የሚውል ገንዘብ ከሁሉም ዜጋ አንዲሰበሰብ የሚያስገድድ ረቂቅ አዋጅ ቀርቦለታልምስል፦ Solomon Muchie/DW

ባለፈው ሳምንት ሰኞ መጋቢት 29 ቀን 2017 ዓ.ም. ረቂቅ አዋጁ የተመራለት የኢትዮጵያ ፓርላማው የውጭ ግንኙነት እና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባዘጋጀው የባለድርሻ አካላት መድረክ፤ ከተለያዩ አገልግሎቶች ላይ የሚሰበሰበው ገቢ የግለሰቦችን የመክፈል አቅም ያገነዘበ ነው ወይ በሚል ጥያቄ ቀርቦበት ነበር። በዚህ ላይ አስተያየታቸውን የተጠየቁት የኮሚሽኑ ቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃ እና ኦፕሬሽን ማስተባበሪያ መሪው፤ “ይሄን ጉዳይ በኋላ አዋጁ ስፀድቅ የሚሰወን ቢሆንም አቅምን የሚፈታተን ግን አይሆንም” በማለት የዜጎች በዚህ የመሳተፉ ሁኔታ ግን ግዴታ ሊሆን እንደሚችል ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡

በቅርቡ የእርዳታ ስራውን የገታውን የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት የተውን ክፍተት አዲሱ ኢትዮ-ኤይድ የሞላ ይሆን ለተባለውም ጥያቄ ምናልባትም በተሻለም ደረጃ ምላሽ እንደሚሰጥ ተነግሮለታል፡፡

ስዩም ጌቱ

ነጋሽ መሐመድ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW