1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

«በአባላቶቼ ላይ ግድያ እና እሥር ተፈጽሟል» ኢዜማ

ረቡዕ፣ ጥቅምት 21 2016

የኢትዮጵያ ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ በጋሞ ዞን አርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ የሚገኙ አባሉ በፖሊስ ድብደባ ሕይወታቸው ማለፉን አስታወቀ። የአካባቢው ፖሊስ ሌሎች 28 የፓርቲው አባላትም በጅምላ ማሠሩንም ጠቅሷል። ዶቼ ቬለ በፓርቲው መግለጫ ዙሪያ ምላሽ እንዲሰጡ የጠየቃቸው በጋሞ ዞን የአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ የአባሉን መሞት አረጋግጠዋል።

ፎቶ ከማኅደር፤ የኢዜማ አርማ
የኢትዮጵያ ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ በአጭሩ ኢዜማ አባላቴ አርባ ምንጭ ውስጥ ግድያ እና እስር ተፈጸመባቸው በማለት መግለጫ አውጥቷል። ፎቶ ከማኅደር፤ የኢዜማ አርማ ምስል፦ Yohannes G/Egziabher/DW

«በአባላቶቼ ላይ ግድያ እና እሥር ተፈጽሟል» ኢዜማ  

This browser does not support the audio element.

«በአባላቶቼ ላይ ግድያ እና እሥር ተፈጽሟል» ኢዜማ  

የኢትዮጵያ ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ ኢዜማ በጋሞ ዞን አርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ውስጥ የሚገኙ አባሉ በፖሊስ ድብደባ ሕይወታቸው ማለፉን አስታወቀ። አቶ ጋሻው ላጼ የተባሉት አባሉ የተገደሉት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን አርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ውስጥ መሆኑን ፓርቲው ባወጣው መግለጫ ጠቅሷል። አቶ ጋሻው በወረዳው ዛይሴ ልዩ የምርጫ ክልል ውስጥ ከ2013 ዓ.ም.  ጀምሮ የፓርቲው አባል ሆነው በንቃት ሲሳተፉ መቆየታቸውን የፓርቲው የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ አቶ ዋስይሁን ተስፋዬ ገልጸዋል።

የፓርቲው አባል ከግለሰቦች ጋር በነበራቸው አለመግባባት የተነሳ ጉዳዩን እንዲያበርዱ ወደ አካባቢው ፖሊሶች መጠራታቸውን የጠቀሱት የድርጅት ጉዳይ ሃላፊው «ነገር ግን የፀጥታ አባላቱ ለተፈጠረው አለመግባባት መፍትሄ ከመሥጠት ይልቅ ቀጥታ አባሉን ወደ መደብደብ ነው የገቡት። በመጀመሪያ በመኖሪያ ቤቱ በመቀጠል በቀበሌ ጽሕፈት ቤት በመጨረሻም በአርባ ምንጭ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ በደረሰበት ድብደባ ሕይወቱ ሊያልፍ ችሏል። ቤተሰቦቹ  የሟችን አስክሬን መጥተው እንዲወስዱ በሥልክ ከተነገራቸው በኋላ ሥርዓተ ቀብሩ እንዲፈጸም ተደርጓል» ብለዋል።

«ሟች አቶ ጋሻው ላጼ በአካባቢው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ላይ በንቃት የሚሳተፉ ስለመሆናቸው በአካባቢው ማኅበረሰብም ሆነ በወረዳው አመራሮች የታወቀ ነው።» ያሉት አቶ ዋስይሁን የአባሉን  ህልፈት ተከትሎ በተቀሩት የኢዜማ ፓርቲ አባላት ላይ እሥር፣ ወከባ እና እንግልት እየተፈጸመ ይገኛል በማለት ተናግረዋል። እስካሁንም በወረዳው የሟችን ጉዳይ በትኩረት ሲከታተሉ ነበሩ ያሏቸው ሌሎች 28 የፓርቲው አባላት በአካባቢው የፀጥታ አባላት በጅምላ መታሠራቸውን አስረድተዋል።

በጋሞ ዞን የአርባ ምንጭ ከተማ፤ ፎቶ ከማኅደርምስል፦ Shewangizaw Wegayehu/DW

ዶቼ ቬለ ፓርቲው ያወጣውን መግለጫ አስመልክቶው ምላሽ እንዲሰጡ የጠየቃቸው በጋሞ ዞን የአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ክበበው አዳል የአባሉን መሞት አረጋግጠዋል። ሟች ከሌላ ግለሰብ ጋር እርስ በእርስ «በጦር ለመገዳደል» በእንቅስቃሴ ላይ እንዳሉ ፖሊስ በቦታው መድረሱን የጠቀሱት ኮማንደር ክበበው «ይሁን አንጂ ሟች ወደ ሕግ ለመሄድ እምቢተኝነት በማሳየታቸው  ድበደባ ተፈጽሞባቸዋል የሚል መረጃ አለ። በድብደባ ለሰው ሕይወት መጥፋት ምክንያት ሆነዋል ተብለው የተጠረጠሩ የፀጥታ አባላት በሕግ ተይዘው ምርመራ እየተደረገባቸው ይገኛል። የሆነው ሁሉ በግለሰቦች ግጭት መነሻነት እንጂ ፖለቲካዊ አይደለም።»“ ብለዋል።

ፓርቲው ታሰሩብኝ ያላቸው 28 ሰዎችን በተመለከተ ተጠርጣሪዎቹ የታሰሩት የግለሰቡን ሞት ምክንያት በማድረግ የቀበሌ ጽሕፈት ውስጥ በመግባት ንብረት በመሰባበራቸው ነው ብለዋል። አሁን ተጠርጣሪዎች እያንዳንዳቸው የ15 ሺህ ብር ዋስትና በማቅረብ ከእስር እንዲወጡ እየተደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW