1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሙዚቃ

ኤልያስ መልካ ሲታወስ

እሑድ፣ ጥቅምት 2 2012

ሰኞ መስከረም 26 ቀን 2012 ዓ. ም. ግብዓተ መሬቱ የተፈጸመው የሙዚቃ አቀናባሪው ኤልያስ መልካ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ የራሱን አሻራ ያኖረ እንደነበር ብዙዎች ይመሰክሩለታል። አንጋፋው የሙዚቃ ባለሙያ ዳዊት ይፍሩ “ኤልያስ ባለፉት 25 ዓመታት ውስጥ እንደ ኮኮብ ብልጭ ያለ እና በአጭር ጊዜ ብዙ ስራ ሰርቶ በሞት የተለየ” ሲሉ ገልጸውታል።

Äthiopien Musiker Elias Melka
ምስል Privat

ኤልያስ መልካ ሲታወስ

This browser does not support the audio element.

በአዲስ አበባ በተለምዶ አብነት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ታኅሳስ 1 ቀን 1970 ዓ.ም. የተወለደው ኤልያስ ባለፉት 18 ገደማ አመታት ከ400 በላይ ሙዚቃዎች በመስራት በኢትዮጵያ የሙዚቃ ጉዞ የራሱን ታሪክ በደማቁ የጻፈ ነው። በልጅነቱ እግር ኳስ መጫወት ይወድ የነበረው ኤልያስ የሙዚቃውን ዓለም የተቀላቀለው ገና በለጋ ዕድሜው ነበር። 

በ1987 ዓ.ም. የአስራ አንደኛ ክፍል ተማሪ እያለ ያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ከመግባቱ አስቀድሞ ሙዚቃን በፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያን ውስጥ ሲጫወት ቆይቷል። በያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ቼሎ ተብሎ የሚጠራውን የሙዚቃ መሳሪያ በዋናነት ቢያጠናም ክራር እና ፒያኖንም ተምሯል። ከልጅነቱ ጀምሮ አሳምሮ የሚጫወተው የጊታር መሳሪያ በብዙዎቹ የሙዚቃ ቅንብር ስራዎቹ ውስጥ በጉልህ የሚደመጥ ነው። ከያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ከተመረቀ በኋላ በተቀላቀለው “መዲና ባንድ” ውስጥም ሲጫወት የቆየው ጊታርን ነበር። 

ኤልያስ በብዙ ሙዚቃ አፍቃሪያን አይን ውስጥ የገባው “አቡጊዳ” የተሰኘውን የቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) የመጀመሪያ አልበም ቅንብር ከሰራ ወዲህ ነው። የእዚህን አልበም ስኬት ተከትሎ ባቋቋመው “በገና ስቱዲዮ” በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ የሆኑ የወጣት ድምጽውያንን ስራዎች አቀናብሯል። ከዘሪቱ ከበደ እስከ እዮብ መኮንን፣ ከትዕግስት በቀለ እስከ ሚካያ በኃይሉ፣ ከኃይልዬ ታደሰ እስከ ኃይሌ ሩትስ ያሉ ድምጻውያን የመጀመሪያ ተወዳጅ አልበሞቻቸው የተከሸኑት በኤልያስ ስቱዲዩ ነው። ወጣቱ የሙዚቃ አቀናባሪ መሐሙድ አህመድ፤ አረጋኸኝ ወራሽ እና ኩኩ ሰብስቤ ከመሰሉ አንጋፋ ባለሙያዎች ጋርም ሰርቷል።

ኤልያስ መልካ ላለፉት ሶስት ዓመታት ዮሐንስ በቀለ (ጆኒ ራጋ)፣ ኃይለሚካኤል ጌትነት (ኃይሌ ሩትስ) እና ዳዊት ንጉሴ ከተባሉ የሙዚቃ ባለሙያዎች ጋር በመሆን “አውታር” የተሰኘ የሙዚቃ መገበያያ ስርዓት ለመዘርጋት ሲደክም ቆይቷል። “የሙዚቃ ባለሙያዎች ከስራዎቻቸው ተገቢውን ጥቅም ማግኘት አለባቸው” የሚል አቋም የነበረው ኤልያስ መብቶቻቸውን ለማስከበር ከሌሎች ሙዚቀኞች ጋር ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። 

የኩላሊት እና የስኳር ሕመም የነበረበት ኤልያስ መስከረም 23 ቀን 2012 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። አንጋፋው የሙዚቃ ባለሙያ ዳዊት ይፍሩ ኤልያስ “በአዲስ መልክ ህብረተሰቡን [በስራዎቹ ያረካ]፣ ወጣት አርቲስቶችን ያስተዋወቀ እና ብቻውን ሆኖ ትልቅ ስራ የሰራ ሙያተኛ ነው” ሲሉ የወጣቱን የሙዚቃ አቀናባሪ አስተዋጽኦ መለስ ብለው ያስታውሳሉ። 

ሙሉ መሰናዶውን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ። 

ሰለሞን ሙጬ

ተስፋለም ወልደየስ 
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW