1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኤርትራ ነፃነትና ጭቆና

ማክሰኞ፣ ግንቦት 23 2008

በ1941 ከኢጣሊያ የቅኝ አገዛዝ ነፃ የወጣችዉ ኤርትራ ከሐምሳ ዓመት በኋላ ግንቦት 1991 ከኢትዮጵያ ነፃ ወጣች።ታሪክ እራሱን ደገመ እንበል ይሆን።አልንም አላልንም የኤርትራ ሕዝብ ነፃ አዉጪ ግንባር ተዋጊዎች የኢትዮጵያን ጦር አሸንፈዉ አስመራን ሲቆጣጠሩ የኤርትራዊዉ ደስታ፤ ፌስታ፤ ፈንጠዝያ ያዩ እንደሚሉት ከ1941 የበለጠ ነበር።

ምስል Reuters/T. Mukoya

ኤርትራ ነፃነትና ጭቆና

This browser does not support the audio element.

ኤርትራ-በሐገሪቱ ገዢ ፓርቲ ሕግዴፍ- አገላለፅ ከኢትዮጵያ «ጨቋኝ አገዛዝ» ተላቅቃ ነፃነት ያወጀችበትን 25 ዓመት ባለፈዉ ሳምንት ማክሰኞ አከበረች።በዓሉ አስመራ ላይ በወታደራዊ ሠልፍ፤ በዕልልታ ጭፈራ፤ በቀረርቶ-ፉከራ በተከበረ ሳልስት አዉሮጳ ለመግባት የሜድትራኒያን ባሕርን ሲቀዝፉ የነበሩ በርካታ ኤርትራዉያን አለቁ።በዓል-ድግሱ፤ እልቂት፤ መከራ፤ ሐዘኑ በርግጥ አዲስ አይደለም።ላፍታ ዳግም እንዘክረዉ።

የኤርትራ ገዢ ፓርቲ ሕዝባዊ ግንባር ለዴሞክራሲ እና ለፍትሕ (ሕግዴፍ) ነዉ-ሥሙ።ኤርትራዊዉ የሕግ ምሁር ዶክተር ዳንኤል ረዘነ እንደሚሉት ግን ኤርትራ ሕዝባዊነትም፤ ዴሞክራሲም፤ ፍትሕም አታዉቅም።

እና ይጠይቃሉ-የዓለም አቀፍ ሕግ ምሑሩ።በርግጥ ኤርትራ ዉስጥ የመንግሥትነት ቅርፅ ባሕሪ ያለዉ ሥርዓት አለ ?እያሉ።የሠብአዊ መብትና የፖለቲካ አቀንቃኝ የአብድረሕማን ሰኢድ አስተያየት ደግሞ ጠንከር-ጠጠር፤ ገለጥ-ጨከንም ያለ ነዉ።

በ1941 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት በተባባሪዎቹ ሐገራት አሸናፊነት መደምደሙ እንደማይቀር በየአካባቢዉ ብዙ ምልክቶች ይታዩ ነበር።ኤርትራን የሚቆጣጠረዉን የኢጣሊ ቅኝ ገዢ ጦርን ለማደምሰስ የዘመተዉ የብሪታንያ ጦር በተለይ በየተራሮቹ ከመሸገዉ የኢጣሊያን ጦር ጋር የገጠመዉ ዉጊያ መራር፤ ከፍተኛ መስዋዕትነትም የተከፈለበት ነበር። ድል ግን እንደተጠበቀዉ የብሪታንያ ሆነ።

ምስል picture-alliance/dpa

ጋዜጠኛና ደራሲ ሚካኤላ ሮንግ እንደፃፈችዉ በኢጣሊያ አገዛዝ የተማረሩ ኤርትራዉያን በየአካባቢያቸዉ አደባባይ እየወጡ ድል አድራጊዉን የብሪታንያ ጦር አበባ ፈንዲሻ እየበተኑ፤ በፌስታ፤ ደስታ፤ እልልታ ይቀበሉት ገቡ።በዉጊያዉ የተሰላቸዉ፤ በርካታ ጓዶቹን ያጣዉ፤ወይም ከጦነቱ ጀርባ ያለዉ ፖለቲካዊ ሻጥር የገባዉ አንዱ ወታደር ግን እልል ባዮቹን ኤርትራዉያንን «ለናንተ ብዬ አላደረግሁትም (አልተዋጋሁም ) አላቸዉ» ትላለች ሮንግ።I didn`t do it for you-በየመፅፍዋ ርዕስ አደረገችዉ።

1941 ከኢጣሊያ የቅኝ አገዛዝ ነፃ የወጣችዉ ኤርትራ ከሐምሳ ዓመት በኋላ ግንቦት 1991 ከኢትዮጵያ ነፃ ወጣች።ታሪክ እራሱን ደገመ እንበል ይሆን።አልንም አላልንም የያኔዎቹ የኤርትራ ሕዝብ ነፃ አዉጪ ግንባር (EPLF) ተዋጊዎች የኢትዮጵያን ጦር አሸንፈዉ አስመራን ሲቆጣጠሩ የኤርትራዊዉ ደስታ፤ ፌስታ፤ ፈንጠዝያ ያዩ እንደሚሉት ከ1941 የበለጠ ነበር።

ጋዜጠኛ ጎይቶም ቢሆን።ዶክተር ዳንኤል ያኔ እግሯ ከተቆረዉ ወጣት ብዙም አይልቁም ነበር።የአስራ-ስምንት ዓመት ወጣት ነበሩ።አቶ አብዱረሕማን ሰዒድ ያኔ ከአስመራዋም ኮረዳ፤ አዲስ አበባ ከነበረዉ ወጣትም በእድሜ ከፍ ያሉ፤ ለዩኒቨርስቲ ጥናት የደረሱም ነበሩ።ደስታዉ፤ ተስፋ፤ ምኞቱ ግን ተመሳሳይ ነዉ።የሠላም፤ የዕድገት ብልፅግና ተስፋ።

የኤርትራ ሕዝብ ነፃ አዉጪ ግንባር ተዋጊዎች ወይም ባለሥልጣናት ያኔ የነፃነት ድል፤ የሠላም ብልፅግና ተስፋ ያስፈነደቀዉን ሕዝብ እንደ ብሪታንያዉ ወታደር ያደረግነዉን ያደረግ ነዉ ለናንተ አይደለም አላሉም።የዉጪም የዉስጥም ታዛቢዎች እንደሚሉት ግን ያ ተስፋ፤ምኞት ደስታ ዛሬ በንኗል።የፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ መንግስትም፤ ጋዜጠኛና ደራሲ ሚካኤላ ሮንግ እንደምትለዉ በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት እንደሌለዉ አዉቆታል።

ምስል DW/Yohannes G/Egziabher

«የኢሳያስ አፈወርቂ ሥርዓት ለረጅም ጊዜ ሥልጣን ላይ ቆይቷል።በሕዝቡ ዘንድ ብዙም ተቀባይነት እንደሌላቸዉ እየተሰማቸዉ ነዉ።የወደፊቱ ተስፋ ሊሆኑ የሚችሉ ወጣቶች ያለማቋረጥ ሲጎርፉ እያዩ ነዉ።መገለላቸዉን እያዩት ነዉ።ከዉጪም ብዙ የሚያዝንላቸዉ እንደሌለም ያዉቁታል።»

ኤርትራ 25 ዓመት የነፃነት በዓሏን ባከበረች በሳልስቱ ስደተኞችን አሳፍራ ከሊቢያ ወደ አዉሮጳ ትጓዝ የነበረች ጀልባ ሜድትራንያን ባሕር ዉስጥ ሰመጠች።አሶሽየትድ ፕሬስ ዘገባ እንደጠቆመዉ ከሟቾቹ መሐል ብዙኤርትራዉያን ነበሩ።ሐብቶም ተክሌ ግን ዳነ።ኤርትራ ነፃ ስትወጣ የሁለት ዓመት ሕፃን ነበር።ዘንድሮ 27 ዓመቱ።«ለዓለም መናገር እፈልጋለሁ።» አለ ወጣቱ ባስተርጓሚ። ይሕ አይነቱ ጉዞ አደገኛ ነዉ።----እባካችሁ በሐገራችን ዉስጥ ነፃነት እንዲነረን እርዱን።እዚሕም ይሁን ሌላ ሥፍራ መኖር አልፈልግም።ሐገሬን ከነፃነት ጋር እፈልጋታለሁ።

አንዳድ የምዕራባዉያን መገናኛ ዘዴዎች ኤርትራን ዝግ ይሏታል።ሌሎች የፖሊስ ወይም የጨቋኝ መንግሥት ሐገር።ብዙዎች ግን ስደተኞች አምራች፤።ዎል ስትሪት ጆርናል የተሰኘዉ የአሜሪካ ጋዜጣ ደግሞ «በፍትነጥ በመራቆት ላይ ያለች ሐገር» የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለዉ በየወሩ አምስት ሺሕ ኤርትራዊ ከሐገሩ ይሰደዳል።ባሕር፤ በረሐ፤ ጫካ የሚቀረዉን የቆጠረዉ የለም።

ይላሉ አቶ አብዱረሕማን።ዶክተር ዳንኤልም በዚሕ ይስማማሉ።የኤርትራ መንግስት ከዉጪም ከዉስጥም የሚሰነዘርበትን ወቀሳ አይቀበለዉም።ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂን ጨምሮ የኤርትራ ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ እንደሚሉት መንግሥታቸዉ የሚወቅስ፤ የሚተች፤ የሚወገዘዉ ለምዕራባዉያንና ኢትዮጵያን ለመሰሉ ጎረቤቶቹ ባለማጎብደዱ ነዉ።ኤርትራዉያን ሐገራቸዉን በገፍ ጥለዉ የሚሰደዱትም ምዕራባዉያን በተለይም ዩናይትድ ስቴትስ እና ኢትዮጵያን የመሳሰሉ መንግሥታት በሚያደርሱት ጫና፤ ሰበካና ጉትጎታ ነዉ-በማለት የኤርትራ መንግሥት ይከራከራል።

ምስል Sirak Bahlbi

ዶክተር ዳንኤል በተለይ የኢትዮ-ኤርትራን የድንበር ግጭትና ጠብ በተመለከተ የአዲስ አበባም የአስመራም መንግሥታት «ስሕተት ፈፅመዋል ባይ ናቸዉ።ይሁንና በኤርትራ ሕዝብ ላይ ለሚደርሰዉ ግፍ፤ በገፍ ለመሰደዱም ከኤርትራ መንግሥት እኩል ተጠያቂ ሊኖር አይችልም ባይ ናቸዉ።

ከእንግዲስ? ዶክተር ዳንኤል ጥያቄዉን «ተገቢ፤ መልሱ ግን «ከባድ» ይሉታል። አብዱረሕማንስ? የኤርትራ ሕዝብ ያለዉ አማራጭ አንድ ነዉ ባይ ናቸዉ-እሳቸዉ።ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ደግሞ እንደ ሁለተኛ የሚታየዉን ድጋፍ ሳያደርግ አይቀርም።

ባለፈዉ ሳምንት ከሰባት መቶ በላይ ስደተኞች ሜድትራኒያን ባሕር ላይ ሲያልቁ ከተረፉት ኤርትራዉያን ስደተኞች ሁለተኛዉ ፊሊሞን ሠለሞን ይባላል።ሰወስት ሰዓት ከተጓዝን በኋላ ዉሐ ወደ ጀልባዋ ይሰርግ ገባ።» ይላል።ዉሐዉን ከጀልባዋ ላይ ለመርጨት ሞከርን።ግን ዉሐዉ ከሁሉም አቅጣጫ ይመጣ ያዘ።» ከስድስት ሰዓት ሙከራ በኋላ ፊሊሞን ተስፋ ቆረጠ።ዘለለ ወደ ባሕሩ።ዋኘ።ሌሎች ሲያልቁ እሱና ብጤዎቹ ዋነተኞች ዳኑ።ፊሊሞን 21 ዓመቱ ነዉ።የኤርትራ ነፃነት 25 ዓመቱ።እንደ ፊሊሞን ዋኝቶ ይድን ይሆን? ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ

 

 

 

 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW