ኤርትራ ሰራዊቷን በአስቸኳይ ከሉአላዊ ግዛቶቿ እንድታስወጣ ኢትዮጵያ አሳሰበች
እሑድ፣ የካቲት 1 2018
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌድዮን ጤሞትዮስ ትናንት ቅዳሜ ለኤርትራው አቻቸው በላኩት ግልጽ ደብዳቤ “ባለፉት ጥቂት ቀናት የታዩት ክስተቶች የኤርትራ መንግሥት ተጨማሪ ግጭት የማባባስ መንገድ መምረጡን ያሳያሉ” ብለዋል። ጌድዮን በመልዕክታቸው አሥመራ “ወታደሮቿን ከኢትዮጵያ ግዛት እንድታስወጣና ከአማጽያን ጋር የምታደርገውን ማንኛውንም ዓይነት ትብብር እንድታቆም” ጠይቀዋል።
ድርጊቶቹ “ተራ ትንኮሳዎች ሳይሆኑ የቀጥታ ወረራ ተግባራት ናቸው” ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን “የጥልና ያለመተማመን አዙሪቱን” በዲፕሎማሲያዊ መንገድ መግታት እንደሚቻል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ደብዳቤው ተቀባይነት የሚያገኝ ከሆነም ኢትዮጵያ "የባሕር አገልግሎት ጉዳዮችን እና በአሰብ ወደብ በኩል የባሕር መዳረሻን ጉዳይ ጨምሮ ሁሉንም የጋራ ጥቅም ጉዳዮችን ለመፍታት በቅን ልቦና በድርድር ለመሳተፍ ፈቃደኛ" መሆኗን የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ገልጸዋል።
የ ኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ጌድዮን ለጻፉት ደብዳቤ የኤርትራ መንግሥት ወዲያው መልስ አለመስጠቱን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ዘግቧል።
ሁለቱ ሃገራት ከ2013 እስከ 2015 ዓ.ም በነበረው የትግራይ ጦርነት አንድ ላይ አብረው በትግራይ ኃይሎች ላይ ቢዘምቱም ኤርትራ ያልተሳተፈችበት የሰላም ስምምነት በፕሪቶሪያ ከተፈረመ በኋላ ግንኙነታቸው ተበላሽቶ ቆይቷል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ኤርትራ በአማራ ክልል ውስጥ ለሚንቀሳቀሱ የፋኖ ታጣቂዎች ወታደራዊ ድጋፍ ታደርጋለች ሲል ይከሳል። ባለፈው የጥር ወር የኢትዮጵያ የፌዴራል ፖሊስ ከኤርትራ በ ህወሃት በኩል የተላኩ በርካታ ተተኳሾችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቆ ነበር።
የኤርትራ መንግሥት ከኢትዮጵያ ሲቀርቡበት የነበሩ ክሶችን በማጣጣል ውድቅ ሲያደርገው ቆይቷል።