ኤርትራ ከኢጋድ አባልነት ራሷን ዳግም ማግለሏ ያለው እንደምታ ምን ይኾን?
ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 4 2018
ኤርትራ ከኢጋድ አባልነት ራሷን ዳግም ማግለሏ ያለው እንደምታ
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) ኤርትራ ከድርጅቱ አባልነት መውጣቷ እንዳሳዘነው ገለፀ።
ኢጋድ ኤርትራ ለቀጣናው ሰላም፣ መረጋጋት እና ልማት የጋራ ግቦችን ለማራመድ አቋሟን እንደገና እንድታጤን እና ሙሉ በሙሉ ወደ ድርጅቱ አባልነት እንድትመለስ እንደሚያበረታታ አስታውቋል።
የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኢጋድ በአባል ሀገራት ላይ በተለይም "ኤርትራን ለመቃወም መሳሪያ በመሆን ጎጂ ሚና ተጫውቷል" ፣ "ሕጋዊ ግዴታዎቹንም እየጣሰ ነው" በሚል ምክንያት ኤርትራ እዚህ ውሳኔ ላይ መድረሷን ገልጧል።
በጉዳዩ ላይ አስትያየት የሰጡ አንድ ኢትዮጵያዊ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያ የኤርትራ ከቡድኑ መውጣት "በተቋሙ ተክለ ቁማና ላይ ይህ ነው የሚባል ተጽዕኖ አይኖረውም" ብለዋል።
ሆኖምኢጋድን ለረጅም ጊዜ "ክፍለ አሕጉሩን ያልተረዳ እና ጥቅም ሲሰጥ ያልቆየ" ሲሉ ገልፀውታል።//
ኤርትራ ከኢጋድ አባልነት መውጣቷ አሳዝኖኛል - ኢጋድ
ኢጋድ ኤርትራ ወደ ድርጅቱ አባልነት በይፋ እንደገና ብትቀላቀልም ከዚያ በኋላ በድርጅቱ ስብሰባዎችም ሆነ ሌሎች ተግባራት ላይ የጎላ ተሳትፎ ውስጥ አለመቆየቷን፣ ይህንንም በትዕግሥት ይዞት መቆየቱን ገልጿል።
ሀገሪቱ በወቅቱ ወደ ኢጋድ አባልነቷ ስትመለስ "ለቀጣናዊ አንድነት እና ለታደሰ ትብብር" ያላት የጋራ ቁርጠኝነት ያታየበት ነው በሚል በበጎ ታይቶ እንደነበር የጠቀሰው ኢጋድ ከአባልነት የመውጣት ውሳኔው ተጨባጭ ሀሳቦች ሳያቀርቡ ወይም በተወሰኑ የተቋማዊ አልያም የፖሊሲ ማሻሻያዎች ላይ ተሳትፎ ሳያደርጉ የተደረገ መሆኑ የበለጠ እንዳሳዘነው በመግለጫው አመልክቷል። ጉዳዩ ሊኖረው የሚችለውን እንደምታ የጠየቅናቸው አንድ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያ ኢጋድ እዚህ ግባ የሚባል ተግባር በመሥራት የሚታወቅ ድርጅት አለመሆኑን ጠቅሰዋል።
ኢጋድ አሉኝ ባላቸው የተቋቋሙ የምክክር ዘዴዎች ያለማቋረጥ ለውይይት ክፍት ሆኖ መቆየቱን ቢገልጽም የኤርትራ መንግሥት ኢጋድ በ1993 እንደገና ሲቋቋም ኤርትራ "ወሳኝ" ያለችውን ሚና መጫወቷን በመጥቀስ ከሌሎች አባል ሀገራት ጋር በመተባበር ለለውጡ እና ለውጤታማነቱ መሥራቱን ጠቅሷል። ይህም ለቀጣናዊ "ሰላምና መረጋጋት ዋና ሞተር ሆኖ እንዲያገለግል በማድረግ "ለክልላዊ ኢኮኖሚያዊ ውህደት" መሰረት እንዲጣል የድርሻውን መወጣቱን ጠቅሷል። ሆኖም ኢጋድ ከ2005 ጀምሮ የአካባቢውን ሕዝቦች ምኞት ከማሳካት ይልቅ አባል ሀገራት ላይ በተለይም "ኤርትራን ለመቃወም መሳሪያ በመሆን ጎጂ ሚና ተጫውቷል" ሲል ከሷል። ድርጅቱ የኤርትራን የማሻሻያ ጥሪ ተቀብሎ ያለፉትን ታሪኮቹን እንደሚያስተካክል ተስፋ አድር ነበር ያለው የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር "በሚያሳዝን ሁኔታ ኢጋድ ሕጋዊ ግዴታዎቹን በመተው" ከአባልነቷ ዳግም መውጣቷን አሳውቋል።
ባለሙያው እንደሚሉት ኢጋድበፕሪቶሪያ ዘላቂ ግጭት የማቆም ስምምነት ላይ እና ሌሎች የፕሮጀክት ሥራዎች ላይ ከመሳተፍ በዘለለ ዓላማውን የተገበረ ሆኖ አልተገኘም።
የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር "ኤርትራ በኢጋድ ውስጥ ያለውን ሕጋዊ ሥልጣን ካጣ፣ ለቀጣናው ምንም አይነት ስትራቴጂካዊ ጥቅም የማያቀርብ እና ለአካባቢው መረጋጋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የማያደርግ ድርጅት ውስጥ አባልነቷን እንድታስወግድ ትገደዳለች።" ሲል ነው አቋሙን ይፋ ያደረገው። የዓለም አቀፍ ግንኙነት ተንታኙ ከኢጋድ ጥቅም ያገኙ አካላት ካሉ ሁለት ናቸው።
በአፍሪካ ሕብረት የኢትዮጵያ ምክትል ቋሚ መልዕክተኛ ምን አሉ?
በአፍሪካ ሕብረት የኢትዮጵያ ምክትል ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ነብዩ ተድላ የኤርትራን አቋን አጣጥለዋል። "የኤርትራ ከኢጋድ መውጣት ራስን ማግለል ሳይሆን ተሳትፎ አለማድረግ ነው" ብለዋል። አክለውም ኤርትራ "የኢጋድን አባልነት ወይም ዋና ዋና ፕሮቶኮሎቿን አጽድቃ አታውቅም፣ በገንዘብ አስተዋጽዖ አበርክታ ወይም ትርጉም ባለው መልኩ ተሳትፋ አታውቅም" ሲሉ ተችተዋል። ኤርትራ በትቋሙ ላይ ሥር የሰደደ ከሥራ የመቅረት ችግር ማሳየቷን የገለፁት አምባሳደር ነቢዩ ይህ በተቋሙ ላይ ወቀሳ ለማንሳንት አያስችልም ይልቅ "ተቋማት ኃላፊነትን የማይወጡ አባላትን ማገልገል አይችሉም" ሲሉ ወቅሰዋል።
በጉዳዩ ላይ ከኢጋድ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ወደ ድርጅቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወደ ጅቡቲ ብንደውልም ልናገኛቸው አልቻልንም።
የኢጋድ አባል ሀገራት
ኢትዮጵያን፣ ጅቡቲን፣ ሶማሊያን፣ ሱዳንን፣ ደቡብ ሱዳንን፣ ኬንያን እና ኡጋንዳ በአባልነት ያቀፈነው እና ዋና መሥሪያ ቤቱን ጅቡቲ ያደረገው ኢጋድ በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ በጋራ እርምጃ፣ በውይይት እና በክልላዊ ውህደት አማካኝነት ሰላምን፣ ደህንነትን እና ልማትን ለማስፈን አልሞ የተቋቋመ ነው። ኤርትራ ትናንት ታህሣሥ 3 ቀን 2018 ዓ.ም ከኢጋድ አባልነት መውጣቷን ተከትሎ የድርጅቱ አባል ሀገራት ወደ 7 ዝቅ ብሏል።
ሰለሞን ሙጬ
ታምራት ዲንሳ