1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኤች አይቪ ተዘንግቷል?

ማክሰኞ፣ ኅዳር 18 2016

የተመድ መረጃ እንደሚያመላክተው በመላው ዓለም 30 ሚሊየን ገደማ ሕዝብ ኤችአይቪ ተሃዋሲ በደሙ ውስጥ አለ። ይኽ መረጃ የተጠናቀረው ባለፈው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት በ2022 ነው። ከእነዚህ መካከል ደግሞ 37,5 ሚሊየን የሚሆኑት አዋቂዎች ሲሆኑ 1,5 ሚሊየን ገደማ ሕጻናት መሆናቸው ነው የተገለጸው።

በየዓመቱ በጎርጎሪዮስ የዘመን ቀመር ታኅሣስ 1 ቀን የዓለም ኤችአይቪ ኤድስ ቀን ይታሰባል። ፎቶ ከማኅደር
በየዓመቱ በጎርጎሪዮስ የዘመን ቀመር ታኅሣስ 1 ቀን የዓለም ኤችአይቪ ኤድስ ቀን ይታሰባል። ፎቶ ከማኅደርምስል Debarchan Chatterjee/NurPhoto/picture alliance

ኤች አይቪ ተዘንግቷል?

This browser does not support the audio element.

የዓለም HIV/ኤድስ ቀን የፊታችን ዓርብ በጎርጎሪዮሳዊው የዘመን ቀመር ታኅሣስ 1 ይታሰባል። የዘንድሮው የዕለቱ መርህ «ማኅበረሰብ ይምራ» የሚል ሲሆን የኤችአይቪ ስርጭት እንዲገታ የኅብረተሰቡ ግንዛቤ ስለሚኖረው ሚና ያመላክታል። ባለፉት ዓመታት የኮሮና ተሐዋሲ ዓለምን አስጨንቆ በመክረሙ ኤችአይቪ የተዘነጋ የመሰላቸው ጥቂት አልነበሩም። በአንድ ወቀት መገናኛ ብዙሃን በየጊዜው ያወሱት የነበረው የኤችአይቪ ስርጭት ጉዳይ በተለያዩ ምክንያቶች የደበዘዘ ቢመስልም የጤና ችግሩ ግን ዛሬም የሁሉንም ትኩረት የሚሻ መሆኑ የሚያሳስቡ ጥቂት አይደሉም። ኢትዮጵያውስጥ ምንም እንኳን ነጻ የምርመራ እና የመድኃኒት አቅርቦት ቢኖርም ዛሬም ራሳቸውን የሚደብቁ መኖራቸው እየተነገረ ነው።

ባለፈው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2022 በመላው ዓለም ወደ 39 ሚሊየን ገደማ የሚሆን ሕዝብ ኤችአይቪ ተሀዋሲ በደሙ ውስጥ እንዳለ ዩኤን ኤይድስ ያወጣው መረጃ ያሳያል። እንደ መረጃው ከተጠቀሰው የሕዝብ ቁጥር 37,5 ሚሊየን የሚሆኑት አዋቂ ሰዎች ሲሆኑ 1,5ቱ ደግሞ ልጆች ናቸው። በያዝነው ሳምንት የፊታችን ዓርብ ዕለት በመላው ዓለም የሚታሰበውን የኤችአይቪ ዕለት ምክንያት በማድረግ የዩኤንኤድስ ዋና ዳይሬክተር ዊኒ ባያኒማ የዓለም HIV/ኤድስ ቀንን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልእክት በአሁኑ ጊዜ ኤችአይቪ በደማቸው ከሚገኝ ወገኖች 9,2 ሚሊየን የሚሆኑት መድኃኒት ማግኘት እንዳልቻሉ አመልክተዋል። እሳቸው እንደሚሉትም በየደቂቃው በዚሁ ሰበብ የሰው ሕይወት እያለፈ ነው። መከላከል ሲቻል የሚከሰተው የሰዎች ሞት የዕጣ ፈንታ ጉዳይ አይደለም ያሉት ዳይሬክተሯ፤ ይህን ማስቀረት እንደሚቻል፤ ስልቱም እንደሚታወቅ ተናግረዋል። ለዚህ ደግሞ ኅብረተሰቡን ማሳተፍ ተገቢ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል። የመንግሥታቱ ድርጅት በያዘው የዘላቂ ልማት ዕቅድ መሠረት በጎርጎሪዮሳዊው 2030 የኤችአይቪ ተሐዋሲ ስርጭትን ለመግታት ታልሟል።

በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ

በጎርጎሪዮሳዊው 2030 ዓ,ም ላይ በኤችአይቪ ተሀዋሲ ምክንያት የሚከሰተውን ሞት ለመቀነስ በታቀደመው መሠረት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠሉት የሚናገሩት በዘርፉ ለበርካታ ዓመታት የሠሩት በአዲስ አበባ የዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ባልደረባ ዶክተር አስቴር ሸዋአማረ እንደገለጹልን ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ከበፊቱ ሲነጻጸር የተሀዋሲው ስርጭት ቀንሷል ባይ ናቸው። ከጥንቃቄ ጉድለት እና የሰዎች ራሳቸውን ካለመጠበቅ ጋር በተገናኘ ዛሬም ለኤችአይቪ ተሐዋሲ የሚጋለጡ መኖራቸው ያመለከቱት ዶክተር አስቴር፤ ምርመራውም ሆነ መድኃኒቱ በሀኪም ቤቶችም ሆነ በየጤና ጣቢያው እያለም ሰዎች ተመርምረው እራሳቸውን ለማወቅ አለመፈለግ መኖሩን ነው የተናገሩት።

በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ የኤችአይቪ መድኃኒት በነጻ በየሃኪም ቤቱ እና ጤና ጣቢያው እንደሚሰጥ የህክምና ባለሙያዎች እና ተሐዋሲው በደማቸው የሚገኝ ወገኖች ይናገራሉ። ፎቶ ከማኅደር፤ የኤችአይቪ መድኃኒቶች ምስል Jens Kalaene/dpa/picture alliance

ከ25 ዓመታት በላይ ኢትዮጵያ ውስጥ የኤችአይምርምሩ የቀጠለው ኤችአይቪተሀዋሲ ስርጭትን ለመከላከል፤ ለመቆጣጠር እና ለማኅበረሰቡም አገልግሎትን ለማስፋት ከፍተኛ ሚና ከተጫወቱ ሀገር በቀል ማኅበራት መቅድም ኢትዮጵያ ብሔራዊ ማኅበር በግንባር ቀደምትነት ስማቸው ከሚጠቀሰው መካከል ነው። የመቅድም ኢትዮጵያ የኮሙኒኬሽን ባለሙያ የሆኑት አቶ ወንድወሰን እንዳለ ምንም እንኳን ማኅበረሰቡን የማንቃቱ ሥራ ቢከናወንም አሁንም አዲስ በተሐዋሲው የሚያዙ መኖራቸውን ይናገራሉ። አቶ ወንድወሰንም ያረጋገጡት ምርመራውም ሆነ መድኃኒቱ በአግባቡ መኖሩን ነው። እንዲያም ሆኖ አዲስ በተሀዋሲው የሚያዙ ሰዎችን ለማስቀረት የሁሉንም ጥረት ይጠይቃል ባይ ናቸው።

በሌላ በኩል ኤችአይቪ በደማቸው ያለ የአካል ጉዳት እንዲሁም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሕጻናትን ጭምሮ ሴቶችን አሰባስቦ በመደገፍ ላይ የሚገኘው «ከኤችአይቪ ጋር ለሚኖሩ ሴቶች እኩል ዕድል» የተሰኘው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት በድጋፍ እጥረት ምክንያት የወትሮ አገልግሎቱን ለመስጠት እየከበደው መምጣቱን ይገልጻል። ድርጅቱን በአሁኑ ጊዜ የሚመሩት አቶ ዮናስ አበበ እንደሚሉት ኤችአይቪ ተሀዋሲ በደማቸው የሚገኝ ወገኖች ምንም እንኳን የመድኃኒት አቅርቦቱ ባይታጎልባቸውም፤ ምግብ ማግኘት አሳሳቢው ችግራቸው ሆኗል።

በጎርጎሪዮሳዊው 2022 ዓም ይፋ የሆነው የተመድ መረጃ እንደሚያመላክተው በመላው ዓለም 30 ሚሊየን ገደማ ሕዝብ ኤችአይቪ ተሃዋሲ በደሙ ውስጥ አለ። ፎቶ ከማኅደርምስል Patrick Pleul/dpa/picture alliance

አቶ ወንድወሰን በአቶ ዮናስ የተነሳው ችግር መኖሩን ነው ያረጋገጡት። በአሁኑ ጊዜ ድጋፍ የሚያደርግላቸው ግሎባል ኤችአይቪ የተሰኘ አንድ ተቋም ብቻ መሆኑን የገለጹት አቶ ዮናስ የሌሎችን እርዳታ ቢያገኙ በድርጅታቸው የሚታገዙት ከአንድ ሺህ የሚበልጡ ወገኖችን ሕይወት ማቆየት እንደሚቻል ነው ያመለከቱት።

መዘናጋቶች መኖራቸውን የጠቆሙት እነዚህ ወገኖች የመከላከሉን ሥራ ለመሥራት በትምህርት ቤቶች ደረጃ አስፈላጊውን የግንዛቤ ቅስቀሳ ማካሄዱ መጠናከር እንደሚኖርበት ነው የመከሩት። በዚህ ላይ የማኅበረሰቡ ንቁ ተሳትፎ ቢታከልበት በተገኘው መድኃኒት ሰዎች ኤችአይቪ በደማቸው ውስጥ እያለም የተሻለ መኖር እንዲችሉ ከበፊቱ የተሻለ ሁኔታ መኖሩንም አመላክተዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ከ700 ሺህ በላይ ሰዎች ኤችአይቪ ተሐዋሲ በደማቸው ውስጥ እንደሚገኝ መረጃዎች ያመለክታሉ። የተሐዋሲው ስርጭት በተለይ በከተማዎች አካባቢ ከፍ እንደሚልም ይገለጻል።  ማብራሪያ ለመስጠት የተባበሩንን እናመሰግናለን።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW