1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የምስራቅ ወለጋው ኪረሙ ወረዳ አለመረጋጋት

ሐሙስ፣ ኅዳር 15 2015

ተፈናቃዮች የቀናት እድሜ የሚወስዱ መንገዶችን በእግር በማቋረጥ ጫካ ለጫካ ለመጓዝ እንደሚገደዱ የሚያነሱት ሌላው በወረዳው የሀሮ ቀበሌ ነዋሪ በአንድ በኩል የፀጥታው መቃወስ በሌላ በኩል ደግሞ በድጋፍ እጦት ህዝቡ ለርሃብ እንደሚዳረግ ገልጸዋል፡፡

Äthiopien | Wahlen | Oromia

እልባት ያላገኘው የምስራቅ ወለጋው ኪረሙ ወረዳ አለመረጋጋት

This browser does not support the audio element.

ባለፈው ሳምንት ዓርብ በተፈጠረው ግጭት ብዙ ውድመት የደረሰባት የምስራቅ ወለጋ ዞንዋ ኪረሙ ወረዳ እስካሁንም መረጋጋት እንደተሳናት ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ በተለይም ከአከባቢው የተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆች በስፍራው ድጋፍ እንደማይደርስ እና በግጭት ከበባ ውስጥ በመሆን አስከፊ ህይወት እየገፉ መሆኑን ተናግረዋል። በዓርቡ ግጭት ከኪረሙ የተፈናቀሉ የኦሮሞ ተወላጆችና የአጎራባች ወረዳ ነዋሪዎች በአሁኑ ጊዜ ይ የከፋ የፀጥታ ሁኔታ ውስጥ መውደቃቸውን ነው የሚናገሩት፡፡

በምስራቅ ወለጋ ኪረሙ ወረዳ በተለይም ባለፈው ዓርብ በተቀሰቀሰው ግጭት በርካቶች ተፈናቅለው አለመረጋጋቱ መቀጠሉን ነው ከአከባቢው የአይን እማኖች ለዶቼ ቬለ አስተያየታቸውን የሰጡት፡፡ እስካሁን መረጋጋት አለመስፈኑን የሚያነሱት ስማቸው እንዳይጠቀስ ጠይቀው አስተያየታቸውን የሰጡን ነዋሪ በኪረሙ የአማራ ተወላጅ ነዋሪ ብሔር ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እንደሚፈጸምም ይናገራሉ፡፡ እንደ አስተያየት ሰጪው በመቶ ሺዎች የሚቆተሩ ነዋሪዎች በግጭቱ ተፈናቅለው ወደ ጎጃም እየተሻገሩም ነው፡፡

ተፈናቃዮች የቀናት እድሜ የሚወስዱ መንገዶችን በእግር በማቋረጥ ጫካ ለጫካ ለመጓዝ እንደሚገደዱ የሚያነሱት ሌላው በወረዳው የሀሮ ቀበሌ ነዋሪ በአንድ በኩል የፀጥታው መቃወስ በሌላ በኩል ደግሞ በድጋፍ እጦት ህዝቡ ለርሃብ እንደሚዳረግ ገልጸዋል፡፡

በኪረሙ ወረዳ ሰሞኑን ውድመትን ካስተናገደችው ኪረሙ ከተማ አስተያየታቸውን የሰጡን የኦሮሞ ተወላጅ ተፈናቃይ ደግሞ ከዚህ ጋር የሚቃረን አስተያየት ነው የሚሰጡት፡፡

“የዚህ ምስቅልቅል ሁሉ መነሻ የሆነው ባለፈው ሳምንት ዓርብ እለት በጠዋቱ በከብቶች ዘረፋ እና በሌሎችም ወንጀሎች የተጠረጠሩ የአማራ ተወላጆች እስረኞችን የመንግስት ሠራዊት ከዚሁ ከተማ ይዘው ሲወጡ ነበር፡፡ እኛ እንደ ተረዳነው እዚህ ተፈርዶባቸው ወደ ነቀምቴ እየወሰዱዋቸው ነበር፡፡ ከዚያን ተንካራ በሚባል ስፍራ የአማራ ታጣቂዎች ቀድሞ ቦታ ይዘው እስረኞቹን ይዘው በሚሄዱት ፖሊሶቹ ላይ ተኩስ ከፈቱ፡፡ 50 ያህል የኦሮሚያ ፖሊስ አባላትም ተገደሉ፡፡ ያንን ተከትሎም በዚሁ እለት ወደ ኪረሙ ከተማም ተመልሰው አስከ 100 የሚሆኑ ሰላማዊ ዜጎችን ገድለው በርካቶችን አፈናቅለዋል፡፡ አርሶአደር፣ መምህራን እና የመንግስት ሰራተኞች ከተገደሉት ውስጥ ይገኛሉ፡፡” ሲሉም አብራርተዋል፡፡

የአማራ ተወላጅ የኪረሙ ወረዳ ነዋሪው አስተያየት ሰጪው በፊናቸው እንደሚሉት፡ እስረኞቹ ተይዘው ወደ ነቀምቴ በመወሰዳቸው  ላይ እምነት አልነበረም፡፡

ስለዚህች ወረዳ አለመረጋጋት መንስኤ እና አሁናዊ ሁኔታ ከመንግስት አካላት ለማረጋገጥና ስለነዋሪዎቹ የከፋ የፀጥታ ስጋት ምላሽ ለመጠየቅ ለወረዳዋ አስተዳዳሪ አቶ ፍቃዱ ወልዴ እና ለወረዳው ፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ ተደጋጋሚ ጥያቄ ብናቀርብም አሁን ምላሽ መስጠት አንችልም ከማለት ውጭ ተጨማሪ አስተያየት አልሰጡንም፡፡

ሰሞኑን የመቶዎች ህይወት በቀጠፈው በኪረሙ ወረዳው ግጭት ምክኒያት ከዚህ ቀደምም አለመረጋጋት የተሳናቸው አጎራባች ወረዳዎች ስጋት ውስጥ ወድቀዋል፡፡ በወረዳው አጎራባች የምትገኘውና ከዚህ በፊት ተመሳሳይ የፀጥታ ቀውስ አስተናግዳ የነበረችው የአሙሩ ወረዳዋ አገምሳ ከተማ ውስጥ የሚኖሩ አስተያየት ሰጪ አስከፊ ጦርነት እንዳይከሰት ሁሉም በስጋት ውስጥ ወድቀዋል ነው የሚሉት፡፡

በምዕራብ ኦሮሚያ ዓመታትን እያስቆጠረ ባለው አለመረጋጋት በተደጋጋሚ ለሚፈጠሩ ግጭቶች የአማራ ተወላጆች በስፋት ሲፈናቀሉ መንግስት ሸነ ያለውና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ ሚጠራውን ኃይል ይወቅሳሉ፡፡ በሌላ በኩል ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለይም በሆሮ ጉዱሩ እና ምስራቅ ወለጋ ዞኖች ውስጥ ከሚገኙ ወረዳዎች በስፋት እየተፈናቀሉ ያሉ የኦሮሞ ተወላጅ ነዋሪዎች ደግሞ ከጎጃም ወደ ሁለቱ የወለጋ ዞኖች ታጥቆ ይገባሉ የሚሉት ፋኖ ያሏቸውን ታጣቂ አካላትን በማፈናቀል ይከሳሉ፡፡

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ በነዚህ በሁለቱ የወለጋ ዞኖች ውስጥ መንግስት ያስታጠቃቸው ያለው ፋኖ የተባሉ ታጣቂዎች ሰላማዊ ዜጎችን በመግደልና በማፈናቀል ግዛት የማስፋፋት ስራ ላይ ተጠምደዋል ብሏል፡፡

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በበኩሉ ፋኖ የሚባል ኃይል በወለጋ ላይ ገብቶ ጥቃት የሚፈፅምበት ምንም አይነት ሁኔታ ተፈጥሮ እንደማያውቅ በመግለጽ፤ የፌዴራሉ መንግስት የመከላከያ ሰራዊትን በአከባቢው እንዲያስፍር መጠየቁ ይታወሳል፡፡

ምዕራብ ኦሮሚያ ውስጥ በተደጋጋሚ በሚከሰቱ የታጣቂዎች ጥቃት በርካቶች ሲገደሉ፤ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉና የግጭቱ ሰለባማ የሆኑም ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡

ስዩም ጌቱ

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW