እምቦጭን ጥቅም ላይ ማዋል
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 21 2011በተለይ ከጣና ላይ የማስወገዱ የአንድ ሰሞን ዘመቻ ሆኖ አሁን ይህ ነው የሚባል እንቅስቃሴ እንደሌለ ጉዳዩን በቅርበት ያስተዋሉ የሚሉትን ባለፈው ሳምንት ማቅረባችን ይታወሳል። ይህን የውኃ ላይ አረም ለተለያዩ ጥቅሞች ያዋሉ ሃገራት የመኖራቸውን መረጃ ጠቁመን ኢትዮጵያ ውስጥም በተደረገ ምርምር ውኃ እንዳያደርቅ የተፈራውን እምቦጭ ለጥቅም ማዋል እንደሚቻል አረጋግጧል።
እምቦጭን በሰው ኃይል በዘመቻ ከውኃው ላይ የማንሳቱ ጥረትም ሆነ በማሽን የሚደረገው ርብርብ ጊዜያዊ እፎይታ እንጂ ዘለቄታዊ መፍትሄ ሊሆን እንደማይችል የሚናገሩ የዘርፉ ባለሙያዎች ጥቂት አይደሉም። በእርግጥም ይህ እውነት ለመሆኑ የሌሎች ሃገራት ተሞክሮም ያሳያል። ለምሳሌ ሕንድ ከሦስት የማያንሱ ሐይቆቿን ያደረቀውን የውኃ ላይ አረም በኬሚካልም ሆነ በሰው ኃይል ለማስወገድ ያደረገችው ጥረት መና መቅረቱን ካስተዋለች በኋላ ሌላ ዘዴ መቀየሷን መረጃዎች ያመለክታሉ። ለምግብነት የሚውለውን እንጉዳይ ለማብቀያነት፣ ለተለያዩ የወረቀት ምርትነት እና ለመሳሰሉት ከፍተኛ ጥቅም እንዲሰጥ ማድረግ በመቻሏ ጉዳትነቱን ወደጥቅም መለወጥ መቻሏ ተዘግቦላታል።
የኢትዮጵያ የአካባቢ እና ደን ምርምር ተቋም እምቦጭ የወረሰው የውኃ አካል አካባቢ የሚገኘው ኅብረተሰብ ለጥቅም እንዲያውለው በሚል ያካሄደውን የምርምር ውጤት ማቅረቡን በተቋሙ የአካባቢ ብክለት አያያዝ ምርምር ክፍል ዳይሬክተር አቶ ያለምሰው አደላ ገልጸውልናል። እምቦጭ አማራጭ የኃይል ምንች መሆን ይችላል ይላሉ ተመራማሪው።
«እሞቦጩ መሰብሰቡ አይቀርም ተሰብስቦ ተከምሮ ከሚቀር ለምን ይሄ የኃይል ምንጭ አይሆንም? አንደኛ እዚያ አካባቢም ከፍተኛ የሆነ የደን መራቆት አለን እና የተወሰነ አማራጭ ኃይል ሊሆን ይችላል፤ ብለን መጀመሪያ የሠራነው ምንድነው፤ ሁሉ ባዮማስ ኃይል ሊሆን አይችልም። ስለዚህ ኃይል አለው ወይ ከሰል የመሆን የሚል የላቦራቶሪ ጥናት ነው ያደረግነው። በእሱም ጥሩ የሚባል የኃይል አማራጭ መሆን እንደሚችል የእምቅ ኃይሉን መጠን አወቅን ማለት ነው።»
እምቦጭ ከሰል መሆን መቻሉ ተረጋገጠ፤ እንዴት ነው ከሰሉ የሚዘጋጀው? አሁንም ተመራማሪው፤
«እንግዲ የከሰል አሰራር ሂደቱ ላይ የተሰበሰበው እምቦጭ መጀመሪያ ወደ ጥቁር ብናኝነት ይቀየራል።»
ይህ ለኅብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆን የእንቦጭ ቅጠሉን ሰብስቦ ማቃጠያውን ማሽን እና በተለመደው የከሰል መጠን እያስተካከለ የሚያወጣው ቅርፅ መሥሪያ በምርምር ተቋሙ ባለሙያዎች ተሠርቶ ተዘጋጅቷል። በዚህም አላበቃም እምቦጭ በሚገኝበት አካባቢ የሚገኘው ማኅበረሰብ ይህንን የውኃ ላይ አረም በሌላ መልክም ሊጠቀምበት ይችላል።
እናም ይላሉ ተመራማሪው ምንም እንኳን እምቦጭን ለተለያዩ ነገሮች መጠቀም እንደሚቻል ቢታወቅም በኢትዮጵያም አረሙ በሚገኝበት አካባቢ ለሚገኘው ኅብረተሰብ ችግሩን በዚህ መልክ በቀላሉ ለጥቅም ማዋሉ የሚያዋጣ መንገድ ነው። ለመሆኑ ይህ የምርምራቸው ውጤት ምን ያህል ተቀባይነት አግኝቷል? ኅብረተሰቡስ ከሰሉን የሚሞክርበት መንገድ ተዘጋጅቶ ይሆን?
«አዎ ከሰሉን ባለፈው ሰኔ ላይ 55 ተሳታፊዎች ያሉበት ሥልጠና ሰጥተናል። አሁን ምንድነው እኛ እንደተቋም በአዋጅ የተሰጠን ግዴታዎች አሉ። እነዚህን ቴክኒዎሎጆዎች ማውጣት ከችግሮች ተነስተን ማለት ነው። ከዚያ በኋላ ደግሞ እነዚህ ቴክኒዎሎጂዎች የተወሰነ ድረስ እንዲተዋወቁ ማድረግ። ይሄንን ተቀብለው የሚያስፋፉ አካላቶች ደግሞ ያስፈልጋሉ።»
የሚደረጉት ምርምሮች እና የሚገኙት ውጤቶች መነሻቸው ጣና ላይ ቢሆንም በዚህ የውኃ ላይ አረም የተጎዱ ሌሎች የውኃ አካላትንም ያዳረሰ ሊሆን እንደሚችልም ነው ተመራማሪው የገለፁት። የምርምር ውጤቱ ተግባራዊ መሆን እንደሚችል ያሳዩበትን የከሰል ማምረቻም ሌሎች እያሰሩ ሊጠቀሙበት ይችላሉ። እሳቸው እንደሚሉት ለአንድ ችግር በሌላ ሀገር የተገኘ መፍትሄ ለአንዱ ሀገር ይሆናል ብሎ እንዳለ መውሰድ አዳጋች ይሆናል። ለዚህም የሀገሩን ሰርዶ በሀገሩ በሬ የሚለውን ብሂል ይጠቅሳሉ።
ምርምራቸው በዚህ አላበቃም ከውኃ ከወጣ እንደ ዓሣ ሕይወት የማይኖረው እምቦጭ በሚንሳፈፍበት የውኃ አካል ላይ መገደቢያ በመሥራት እንዳይስፋፋ መከላከል ላይ ያተኮረ ሦስተኛ ጥናት በመካሄድ ላይ መሆኑንም ገልፀውልናል። ይህ ሙከራ ደግሞ በሌሎች ሃገራት ያልተደረገ የኢትዮጵያ የዘርፉ ምሁራን የሚያኪያሂዱት አዲስ ምርምር ነው። በነገራችን ላይ እምቦጭ እጅግ ረዥም ስሮች ያሉት በውኃ ዳርቻ ያሉ አካባቢዎችን ወርሶ በበዛ መጠን አካባቢውን እያደረቀ የሚሄድ አደገኛ አረም ነው። ለጌጥነት የሚጠቀሙበት ቢኖሩም ሰፊ የውኃ አካል ላይ ካረፈ በቀላሉ ሊያስወግዱት የማይቻል መሆኑን የሌሎች ሃገራት ተሞክሮም ያሳይል። እምቦጭ አይጠፋም ከተባለ እንግዲህ አማራጭ ማገዶ ሆኖ መቅረቡ ለኅብረተሰቡ ጠቃሚነቱ አያነጋግርም ቢያንስ ችግርን ዕድል ማድረግ ሳያወጣ አይቀርም። ተመራማሪውን ከልብ በማመስገን እምቦጭ ላይ ትኩረት አድርገን ያጠናቀርነውን ተከታታይ ዝግጅት የመጨረሻ ክፍል በዚሁ አበቃን።
ሸዋዬ ለገሠ
