1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እስራኤል ከ200 በላይ የሚሆኑ ዜጎቿን ከአማራ ክልል አወጣች

ዓርብ፣ ነሐሴ 5 2015

እስራኤል ከአማራ ክልል ከ200 በላይ የሚሆኑ ዜጎቿን በተሳካ ሁኔታ ማውጣት መቻሏን አስታወቀች። ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልእክት «እነዚህ ሰዎች ከጎንደር እና ከባሕር ዳር ወደ አዲስ አበባ በመጓዝ ላይ ነበሩ። ከዚያ እስራኤል ይደርሳሉ» ብለዋል።

ቤንያሚን ኔታንያሁ
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ከጎንደር እና ከባሕር ዳር ከተሞች የወጡት እስራኤላውያን እና የእስራኤል ዜግነት የማግኘት ዕድል ያላቸው ሰዎች ወደ አዲስ አበባ እየተጓዙ መሆኑን ተናግረዋል። ምስል Abir Sultan/EPA POOL/AP/dpa/picture alliance

እስራኤል ከአማራ ክልል ከ200 በላይ የሚሆኑ ዜጎቿን በተሳካ ሁኔታ ማውጣት መቻሏን አስታወቀች። ከግጭቱ አካባቢ የማውጣቱ ጥረት 174 ዜጎችን እና ከጎንደርም የእስራኤልን ዜግነት መሰድ እንደሚችሉ የተረጋገጠ ኢትዮጵያውያንን ያካተተ መሆኑም ተገልጿል። በተጨማሪም 30 እስራኤላውያንንም ከአማራ ክልል ዋና ከተማ ባሕር ዳር ማውጣት መቻሉም ተመልክቷል። 
 

የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጽሕፈት ቤት ይፋ ባደረገው መግለጫ እስራኤል ከአማራ ክልል በአብዛኛው እስራኤላውያን የሆኑ 204 ሰዎች ማውጣቷን አስታውቋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልእክት «እነዚህ ሰዎች ከጎንደር እና ከባሕር ዳር ወደ አዲስ አበባ በመጓዝ ላይ ነበሩ። ከዚያ እስራኤል ይደርሳሉ» ብለዋል። 

ረቡዕ ዕለት የኢትዮጵያ መንግሥት በአማራ ክልል በመንግሥት ኃይሎች እና በታጣቂዎች መካከል ውጊያ የተካሄደባቸው ዋና ዋና ከተሞች ነጻ መሆናቸውን ይፋ አድርጓል። ባለፈው ሳምንትም ግጭት በተቀሰቀሰበት የአማራ ክልል ለስድስት ወራት የሚዘልቅ የአስቸኳይ ጊዜም ደንግጓል።

ጎንደር በአማራ ክልል የጸጥታ ቀውስ ከበረታባቸው ከተሞች አንዷ ናት።ምስል Alemnew Mekonnen/DW

የእስራኤል መንግሥት በጎርጎሪዮሳዊው የዘመን ቀመር 2021 ዓ,ም አብዛኞቹ ጎንደር ውስጥ የሚገኙ 3,000 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን በአስቸኳይ ወደ እስራኤል እንዲጓዙ መፍቀዱን አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ዘግቧል።

የቤተእስራኤላውያን አዲስ መንደር ምስረታ

እስራኤል በዚሁ የዘመን አቆጣጠር በ1980 እና በ1990ዎቹ መጀመሪያ ከኢትዮጵያ በርካታ ቤተ እስራኤላውያንን በዘመቻ መልክ ማውጣቷ ይታወሳል። በወቅቱ «ዘመቻ ሰሎሞን» የሚል ስያሜ በተሰጠው የእስራኤል መንግሥት ቤተ እስራኤላውያንን ከኢትዮጵያ በአውሮፕላን ያጓጓዘበት እርምጃ 15,000ዎቹን በ36 ሰዓታት ውስጥ ማውጣቱን አዣንስ ፍራንስ ፕረስ በዘገባው ጠቅሷል።  አሁንም ቁጥሩ አነስ ያለ የቤተ እስራኤላውያን ማኅበረሰብ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚገኙም ገልጿል።

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW